ለእኛ የሚበጀን በትግላችን ነጻነታችንን ማረጋገጥ እንጂ የኦባማ መግባት እና መውጣት አይደለም::
Minilik Salsawi የባራክ ኦባማ ምስራቅ አፍሪካ ላይ ኬንያን እና ኢትዮጵያን መጎብኘት የሰሞነኛ አዲስ ዜና ሲሆን ባራክ ኦባማ የሃያላኗ አገር መሪ በመሆናቸው የጉዞው ዜና ሰፊ ሽፋን አግኝቶ አለምን እያስተጋባ ይገኛል::ባራክ ኦባማ በርግጥ ከአፍሪካዊ አባት መገኘታቸው እንዲሁም የሃያላኗ አሜሪካ የመጀመሪያው ጥቁር መሪ መሆናቸው ለየት ሊያደርጋቸው የሚችል ቢሆንም የሚከተሉት የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ በተለይ አፍሪካን በተመለከት የሚያራምዱት አቋም አምባገነኖችን ፈልፍሎ ከማበረታታት ውጪ ምንም የፈየደው ነገር የለም::

ኦባማ ወደ ስልጣን ሲመጡ እንደማንኛውም ተወዳዳሪ ለመመረጥ የሚያስችላቸውን ድምጽ ለማግነት አፍሪካን በተመለከተ ቃልኪዳኖችን በማሽጎድጎዳቸው በተለይ ለውጥ ፈላጊ ሃይሎች የሆኑ ኢትዮጵያውያን በአሜሪካ ምድር ለመመረጣቸው ስኬት ጉልህ ሚና ተጫውተዋል::ኦባማ ግን ወደ ስልጣን ወንበሩ ከተዋሃዱ በኋላ የአፍሪካ አምባገነኖችን በነጩ ቤተመንግስታቸው ሰብስበው በከፍተኛ ማበረታታት የአሜሪካንን ጥቅም በልዩ መልኩ በሚጠብቅ ሁኔታ ደም መጣጭ የአፍሪካ አምባገነን መሪዎችን አጓጉል በማሞገስ ለአፍሪካውያን ትልቅ አደጋ የሆኑ ወንጀሎች እንዲሰሩ እና መንግስታዊ ሽብርተኝነት እንዲስፋፋ አድርገዋል::

በርግጥ ምእራባውያን አፍሪካ ውስጥ ለብሄራዊ ጥቅማቸው እንደሚሰሩ የታወቀ ነው:: የሃይል ሚዛንም ባለበት ሆነው ጥቅማቸው እስካልተነካ ድረስ አምባገነኖችን በመደገፍ እንደሚያበረታቱ ሃቅ ነው::ኦባማ የውጪ ፖሊሲያቸው እንደሚያሳየው የአሜሪካን ጥቅሞች እስካልተነኩ ድረስ ማንኛውም አፍሪካዊ መሪ በሃገሩ ውስጥ የሚፈጽመውን የፖለቲካ ግፍ እንደማይመለከታቸው እና ጣልቃ መግባት እንደማይፈልጉ በተለያዩ ጊዜያት አጋጣሚዎችን ተጠቅመው ተናግረዋል::ሕዝቦች በኑሮ ውድነት መግቢያ መውጫ እንዳጡ በርካታ ድሆች ጥቂት በሙስና የከበሩ ቱጃሮች እንዳሉ በገሃድ እየታየ በዋጋ ግሽበት እና በተለያዩ የኢኮኖሚ ውድቀቶች ሃገራት እየሞቱ እያዩ በሃሰት የቁጥር ቁልሎች የኢኮኖሚ እድገት እየታየ እንደሆነ በመጥቀስ ከባልደረቦቻቸው እና ተቋሞቻቸው ጋር እየተቀባበሉ ሲናገሩ ተሰምቷል::ለዚህም በሞት አፋፍ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ አገራችንን ገነት እያደረጉ በመሳል ስህተቶች ሲፈጥሩ ማየት የተለመደ ተግባር ነው::ወታደሮቹን በሽብርተኝነት መዋጋት ሰበብ እየሸተ የሚገነውን ወያኔ መራሹን መንግስት በማቆለጳጰስ መንግስታዊ ሽብርተኝነት ኢትዮጵያን እንዲወር በሩን ከፍተዋል::

ባራክ ኦባማ ለአሜሪካ እና ለአሜሪካውያን ምናልባት ጥሩ መሪ ሊሆኑ ይችሉ ይሆናል::እርሳቸው ወደ ስልጣን ክመጡ በኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት ግድያ እስር እና የሰብአዊ መብት ጥሰት መፈጸሙ እንዲሁም አለምን ያስደመመ እና ያሳዘነ ስደት መከሰቱ እሙን ነው::እርግጥ ነጻነታችንን እና መብታችን የሚያስከብሩልን ኦባማ አይደሉም::እኛ ራሳችን መሆናችንን መዘንጋት የለብንም::የኦባማ የምስራቅ አፍሪካ ጉብኝት ለኛ ምም የሚጠቅመን ነገር የለም::ለሽፋን ጥቂት እስረኞች ቢፈቱ በርካቶች መታሰራቸው እና መገደላቸው ቀጥሏል::ይህንን ልንፈታ የምንችለው በጋራ ቆመን በመታገል በአንድነት ሃይላችንን አጠናክረን የወያኔን ማፊያ መንግስት ስንደመሥ ብቻ እና ብቻ ነው::ምናልባት ኦባማ እንደተለመደው ፍሪደም ኦፍ ምናም የሚል የአንደበት አየር ባየር ንግግሮች ቢናገሩም በዋናነት የሚመለከቱት ግን የሃይል ሚዛኑን እና የሃገራቸውን ጥቅም እንደሆነ ጠንቅቀን ልናውቅ ይገባል::ለኛ የሚበጀን በትግላችን ነጻነታችንን ማረጋገጥ እንጂ የኦባማ መግባት እና መውጣት አይደለም::ድል በሕዝብ ለሕዝብ የሕዝብ ነው::‪#‎ምንሊክሳልሳዊ‬