በጭፍን ስሜት የመነዳት ልማድ ለስህተት ይዳርጋል::

የዘንድሮ ፖለቲካ፣ ብዙዎች ከሚገምቱት ውጭ፣... በግራ በኩል ሲጠብቁት በቀኝ በኩል የሚነጉደው ለምንድነው? “ግራ መጋባት” ይሉሃል ይሄ ነው። እንዲህ የምንሆነው፣ ሳናስተውል ስለቀረን ወይም ሚዛን ስለጠፋብን ይሆን? እንደዚያ ከሆነ፣ ጥፋቱ የኛ ነው። ግን፣  ሌላውስ ዓለም መች ከግራ መጋባት ዳነ! “ለየትኛውም አገር ቢሆን፣ የዘመኑ ፖለቲካ መላ የለውም’ኮ” ሊባል ይችላል። በእርግጥም፣ ብዙ ሰዎች ከሚጠብቁት ውጭ፣ ዓለማችን ከዳር ዳር እየተናጠች ነው። ግራ መጋባት የተበራከተው፣ በኢትዮጵያውያን ላይ ብቻ አይደለም። ቢሆንም ግን፣ ኢትዮጵያ ላይ በዛ፣ ተደጋገመ፣ ተደራረበ።በተለይ በተለይ፣ ኢትዮጵያን በሚመለከት፣ የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ አቋምና ጉብኝት በፍፁም ድንገተኛ ሊሆንብን አይገባም፡፡ “የአሜሪካ እጅ ረዝሟል፤ ማሳጠር አለብን” ብለው የሚያምኑት ባራክ ኦባማ፤ አሜሪካ በየአገሩ ጣልቃ ገብታ “የግለሰብ መብት አክብሩ፤ የፖለቲካ ምርጫ አካሂዱ፤ የነፃ ገበያ አሰራር አስፋፉ” እያለች ተፅእኖ ማሳረፍ እንደሌለባት ደጋግመው ተናግረዋል። ይሄ፣ ከዋና ዋና የኦባማ መርሆች መካከል አንዱ ነው። ሳይመረጡ በፊትም ሲናገሩት የነበረ፣ ከተመረጡ በኋላም በተግባር የገፉበት የውጭ ግንኙነት መርህ ነው። ከስድስት ዓመት በላይ ካላንቀላፋን በስተቀር፣ የኦባማ አስተሳሰብና አዝማሚያ ገና ድሮ ፍንትው ብሎ ሊታየን ይገባ ነበር። ለምን?

አውሮፓና አሜሪካ “በአለም ዙሪያ የግለሰብ ነፃነትን፣ የፖለቲካ ምርጫዎችንና የነፃ ገበያ አሰራርን የሚያስፋፋ የፖለቲካ ለውጥ ለማምጣት፣ ተፅእኖ ማድረግ ዋጋ የለውም። እንዲያውም ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል” ወደሚል አስተሳሰብ አዘንብለዋል።እንደ አፍሪካ ቀንድ በመሳሰሉ የውጥረት አገራት ውስጥ፣ የተረጋጋ መንግስትና የኢኮኖሚ እድገት ከተገኘ በቂ ነው” ወደሚል ተስፋ ቢስነት እየወረዱ ነው።አውሮፓና አሜሪካ፣ በኢትዮጵያ ለሚካሄድ የፖለቲካ ምርጫ ሲሰጡት የነበረ ትኩረት ምን ያህል እንደቀነሰ በዘንድሮው ምርጫ በግልፅ ታይቶ የለ!!የኢትዮጵያ መንግስት፣ ለአካባቢው አገራት መረጋጋት እስካገዘ ድረስ፣ ከአውሮፓና ከአሜሪካ የወዳጅነት እርዳታ ማግኘቱ የማይቀር ነገር ነው - በዛሬ አለማቀፍ የትርምስና የሽብር ዘመን።ይህንን ማስተዋልና ማገናዘብ ከቻልን፣ የኦባማ ጉብኝት በጭራሽ ድንገተኛ ተዓምር ወይም ዱብዳ አይሆንብንም፡፡

ባራክ ኦባማ፣ ለኢትዮጵያ መንግስት የሚያሳዩት የወዳጅነት አቋም ግን፣ ከዚህም ያለፈ፣ ከዚህም የቀደመ ነው። ገና ሳይመረጡ በፊት የያዙት አቋም ነው።“የአሜሪካ እጅ ረዝሟል፤ ማሳጠር አለብን” ብለው የሚያምኑት ባራክ ኦባማ፤ አሜሪካ በየአገሩ ጣልቃ ገብታ “የግለሰብ መብት አክብሩ፤ የፖለቲካ ምርጫ አካሂዱ፤ የነፃ ገበያ አሰራር አስፋፉ” እያለች ተፅእኖ ማሳረፍ እንደሌለባት ደጋግመው ተናግረዋል። ይሄ፣ ከዋና ዋና የኦባማ መርሆች መካከል አንዱ ነው። ሳይመረጡ በፊትም ሲናገሩት የነበረ፣ ከተመረጡ በኋላም በተግባር የገፉበት የውጭ ግንኙነት መርህ ነው።“ከሁሉም ከሁሉም በፊት፣ የኢኮኖሚ ጉዳይ ይቀድማል” ማለትም የአሜሪካ ድርሻ፣ “የግለሰብ መብት፣ የፖለቲካ ምርጫና ነፃ ገበያ” የሚሉ ቅድመ ሁኔታዎችን ትታ፣ እርዳታ መስጠት ብቻ ይሆናል። ኦባማ ይህንን በተደጋጋሚ ተናግረዋል፤ በተግባርም እየሰሩበት ይሄውና ስድስት አመታት ተቆጥረዋል።ታዲያ፣ ይህንን ሁሉ ሰምተንና አይተን፣ ባራክ ኦባማ በኢትዮጵያ ላይ ምን አይነት አቋም እንደሚከተሉ መገመት ያቅተናል? ቢያንስ ቢያንስ፣ ፖለቲካን እንጀራቸው ወይም ፖለቲካን ሙያቸው ያደረጉ ሰዎች፣ ይህንን መሳት አልነበረባቸውም።ግን ስተውታል፤ በረዥም ርቀት ስተውታል። በቃ፣ የባራክ ኦባማ አቋምና የኢትዮጵያ ጉብኝት፣ ለአገራችን ፖለቲከኞች ግራ የሚያጋባ ድንገተኛ ተዓምር ወይም ዱብዳ ሆኖባቸዋል።በአንድ በኩል፣ ኢህአዴግ፣ በተለመደው የሶሻሊስቶች ፈሊጥ “ኒዮሊበራል” እያለ ከሚያጣጥላት አገር... ካልጠበቀው አቅጣጫ... ከአሜሪካ፣ ለዚያውም ዝነኛው ባራክ ኦባማን የመሰለ አድናቂ ማግኘቱ ያስገርመዋል። 

ያኔ በ2001 ዓ.ም፣ “ባራክ ኦባማ ከተመረጡ፣ በኢህአዴግ ላይ ጫና በማሳረፍ የፖለቲካ ለውጥ እንዲመጣ ይረዱናል” በማለት፣ ኮሚቴ አቋቋመው ቅስቀሳ ሲያካሂዱ የነበሩ የዲያስፖራ ፖለቲከኞችስ? በነሱ ቅስቀሳ ባይሆንም፣ ኦባማ ተመርጠው በፕሬዚዳንትነት ሲሰሩ ስድስት ዓመታት ተቆጥረዋል። ይሄን ሁሉ አመት የኦባማን አስተሳሰብና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሳይገነዘቡ የቆዩ የአገራችን የዲያስፖራ ፖለቲከኞች፣ በኦባማ አቋም ተበሳጭተው ለተቃውሞ ሰልፍ የወጡት አሁን ነው - የኦባማ ጉብኝት፣ ድንገተኛ ክህደት ሆኖባቸው።
ላለፉት ስድስት አመታት፣ ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች፣ የባራክ ኦባማን የውጭ ፖሊሲ ለማወቅ ትንሽ ጥረት ቢያደርጉ ኖሮ፣ ይሄ ሁሉ ግራ መጋባት ባልተፈጠረ ነበር። ለኢህአዴግ፣ ድንገተኛ አድናቆት አይሆንበትም ነበር። ለዳያስፖራ ተቃዋሚዎችም፣ የኦባማ ጉብኝት ድንገተኛ ክህደት ሆኖ ባልታያቸው!

ኢህአዴግና የዲያስፖራ ተቃዋሚዎች ለአመታት ያህል እንዲህ ግራ የተጋቡት ለምንድነው?በእርግጥ፣ ነገሩ ከተፈፀመ በኋላ፤ የጉብኝት ዜናው ከዳርዳር ከተወራ በኋላ… “ነገሩን መሳት አልነበረባችሁም፣ ኦባማ ለኢህአዴግ እንደሚመቹ ማወቅ ነበረባችሁ፤ መገመት ነበረባችሁ” ብሎ መናገር ቀላል ነው። የአገራችን ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ተጨባጭ መረጃን በማገናዘብ፣ ያኔ ድሮ የኦባማ አስተሳሰብንና አዝማሚያን ማወቅ ይችሉ እንደነበር ለማሳየት ነው የፈለግኩት። ለማወቅ ያልቻሉት፣ ነገሩ ከባድ ስለሆነ አይደለም። በጭፍን ስሜት የመነዳት ልማድ ነው እንዲህ ለስህተት የሚዳርጋቸው።