በፍትህ እና በፍትህ አካላት ላይ የተጫኑ የፖለቲካ ደባዎች ይውረዱ::

Minilik Salsawi (ምንሊክ ሳልሳዊ) - የወያኔ ጉጅሌ አገዛዝ በሚያመቸው መንገድ ሃይማኖታዊ የፖለቲካ አደረጃጀት በመፍጠር ለዘመናት የቆየውን የሃይማኖት ቀኖና ትላንትና እንደ አይሁድ ባሉ መርዘኛ መንግስታት በተፈጠሩ ዘመን አመጣሽ የአሕበሽ እምነቶች ለመተካት እና የኢትዮጵያውያንን የሰላም እና የፍቅር ተምሳሌት የሆነውን እስልምናን ለማደፍረስ ደፋ ቀና በማለት ትላንት እውቅና ለሰጣቸው የሙስሊም ምሁራን ወገኖቻችን የአሸባሪነት ታርጋ በመለጠፍ በጠፍ ጨረቃ መኖሪያቸውን በመስበር በከፍተኛ ስቃይ እና እንግልት ወደ እስር ቤት አግዞ ካለምንም ማስረጃ እና ካለበቂ ሰነድ አግቶ በማንገላታት ላይ ነው።ወንጀለኞች በንፁሃን ላይ የሚፈርዱበት ችሎት ሊሰየም 2 ቀናት ቀርተውታል!

በአሁን ወቅት የወያኔ ጉጅሌ በፍትህ አካላት ክለላ የሚፈጸመው የፖለቲካ ደባ የሙስሊሙን ጉዳይ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ላይ የተደረገ ያለው ኢ ፍትሃዊ እና የዜግነት ንጽሕናቸውን የሻረ ፖለቲካዊ ብይን/ውሳኔ ማናችንም የማንቀበለው ከመሆኑም በላይ የትግሉን ብርታት እና ወኔ የማያጥፈው የበለጠ የሚያጠናክረው መሆኑ መዘንጋት የለበትም::የወንድሞቻችን የኮሜቴው ጉዳይ የሙስሊም ሃይማኖት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያውያን የፍትሕ ጉዳይ ነው::የወያኔ ስርአት ራሳቸውን አክብረው እና ሃይማኖታቸውን ጠብቀው ከፖለቲካ እድፍ ነጻ ነን ያሉ ምሁራንን እንደ ተቃዋሚ;ሕገመንግስታዊ ጥያቄ ያቀረቡ ዜጎችን እንደ አሸባሪ ;በነጻነት ማምለክ መጸለይ እንፈልጋለን ያሉ ትን እንደ አክራሪ ወዘተ ... በመፈርጅ የፍትሕ ስርአቱን ለፖለቲካ ግብኣት በማዋል የዜጎችን መብት ገፎ በየእስር ቤቱ በማጎር ኢትዮጵያ ለብዙሃን ሕዝቦቿ አንገት መድፊያ ለጥቂት ጉጀሌዎች መውደቂያቸው እስኪደርስ መንቀባረሪያ በማድረግ የፍትህ ስርአቱን ለፖለቲካ አላማቸው አውለው የሕግ የበላይነትን ቀብረውታል::

እጅግ አስደንጋጭ እና አሳዛኝ የሰው ልጆች በገዛ አገራቸው ዜጋ አይደለንም እንዲሉ በፍርሃት ተሸብበው እንዲኖሩ ለማድረግ የተቀናጁ አሰቃቂ ወንጀሎች በኢትዮጵያውያኑ ሙስሊም ምሁራኖች ላይ ተፈጽሟል። ታሪክ ይቅር የማይለው ከባድ መንግስታዊ ወንጀል ማንንም ከተጠያቂነት እንደማይመልስ ትውልድ በተግባር ያሳያል።ትግሉን እየመራ የሚገኘው "ድምጻችን ይሰማ" ባስተላለፈው መልእክት ህዝበ ሙስሊሙን ለረጅም ጊዜ መብቱን ገፍፎና ጨቁኖ በመያዝ እቅድና ሂደት ላይ መገኘቱ እኛም ዓመታትን አሻግረን ተመልክተን የትግላችንን አድማስ በማሳደግ ለመብታችን መከበር የምናደርገውን እንቅስቃሴአጠናክረን እንድንቀጥል ያስገድደናል፡፡ የትግላችንን ህዝባዊ መሰረት አጠናክረን የጀመርናቸውንና ሌሎች መሰል ግፊት የሚያሳድሩ የትግል አቅጣጫዎችን በመከተል ዘርፈ ብዙ ችግሮቻችን ለመፍታት በምንጥርበት መልኩ ተግባራዊ እናደርጋለን::

በውድ ኮሚቴዎቻችን ላይ የሚተላለፈው የግፍ ብይን በዳዮቻችን እንደሚያስቡት ወኔና ብርታታችንን የሚሰብር ሳይሆን እስካሁን ከከፈልነው በተጨማሪ መስዋእትነቶችን ለመክፈል የምንዘጋጅበትን ቁርጠኝነትን የሚለግሰን ይሆናል፤ የጥፋተኝነት ብይኑ በተላለፈበት ችሎት ውድ ኮሚቴዎቻችን ያሳዩት ጀግንነት ለዚህ ምስክር፣ ለእኛም የሞራል ስንቅ ነውና!እኛም ከድምጻችን ይሰማ ጎን በመቆም ከሕዝበ ሙስሊሙ የሕግ የበላይነት ይከበር ጥያቄዎች ጋር እጅ ለ እጅ ተያይዘን ‹‹የትግል ወኔ እና ብርታታችን በፖለቲካዊ ውሳኔ አይታጠፍም!›› በማለት የጋራነት የአብሮነት የወንድማማችነት ትግላችን እስከድል ደጃፎች ድረስ ይቀጥላል::የአብሮነታችን ተምሳሌት ለአለም ያስተማረውን የአያቶቻችንን የአንድነት ፍቅር ደግመን በዚህ ትውልድም ማሳየት አለብን ። አምባገነኖች ጠንክረን ከታገልናቸው ቀዳዳው ሁሉ ስለሚጠብባቸው ተፍረክርከው ይጠፋሉ። በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ላይ የደረሰው ግርፍት እና መከራ ቁስሉ የኔም ነው። ‪#‎ምንሊክሳልሳዊ‬