መንግስታዊ ውዥንብር - የአረና ሰዎች ሽርጉድ - የመንደርተኝነት አጀንዳ ድምዳሜው

Minilik Salsawi :- የደምሕት ታጋይ ሞላ አስገዶምን ተከትሎ ብዙ የኮካዎች ውሮሸባ የቀወሱ ሃሳቦች የስም ማጥፋቶች የተበሳጩ ኪሳራዎች የደቀቁ የተልፈሰፈሱ ዲያስፖራዎች የእርስ በእርስ ግልምጫዎች እና ዘለፋዎች አሳፋሪ ዘመቻዎች እና ፍረጃዎች ወዘተ ያላነበብነው ነገር የለም::እውነት ከማይዋጥላቸው ድንጉጥ ያልበሰሉ ፖለቲከኞች ጀምሮ ኪሳራ የተከናነቡ ያህል የለፈለፉ የገደል ማሚቱዎች እና በራሳቸው ኢጎ እስከሚጦዙ ሃይሎች ድረስ ሁሉንም አየን ታዘብን::ይሁን እኔን ግን የገረመኝ ካለው እውነት የወጡ በመግለጫ ስም የተለቀቁ መንግስታዊ ውዥንብሮች እና የካድሬዎቹ መደነባበር እንዲሁም የተቃዋሚ የአረና ፓርቲ አባላት በሞላ ዙሪያ እየተሽከረከሩ አሸንዳ መጨፈር እና ሽር ጉድ ማለት ብሎም የአቶ ሞላ አስገዶም የመንደርተኝነት አጀንዳ ድምዳሜ ብቻ ነው::

ክወያኔ ጉጅሌ አገዛዝ መግለጫ ብንጀምር መግልጫ ሳይሆን በኔ እይታ መንግስታዊ ውዥንብር ነው::ምንም ተጨባጭ ያሌለው መግለጫ እና ተከርብቶ እጁ የገባውን ሞላን የወያኔ ሰላይ ነበር አሊያም የስለላ ጥበባችን እንዲህ ነው የሚል የሃሰት ፕሮፕጋንዳ ለመርጨት ካልሆነ በስተቀር በድል ሽሚያ መሃል የገባው ወያኔ ከባድ ኪሳራ በመግለጫው አግኝቶታል:: ያልተገናኘውን ለማገናኘት ሲውተረተር የሚታየው ከደርግ በባሰ መልኩ በትምክህት እና በጦረኝነት ዘለፋ የተሞላው አምባገነናዊ ውዥንብር ሕዝብን ለማታለል ያደረጉት ቢሆንም ራሳቸውን እንዳታለሉ ሕወሓቶች አልተረዱትም::አጉል ራስን ከፍ አድርጎ በሕዝብ መሃል እኛ እንዲህ ነን የሚል ፍርሃት ለመልቀቅ ቢሞከርም ከነካድሬዎቻቸው መደነባበር ውስጥ መግባታቸውን አጋልጠዋል:: ወያኔ ለሞላ የስለላ ተልእኮ ከሰጠችው ከሞላ ጋር የገቡት ወታደሮቹ ለአገር ጉዳይ ሲሰሩ ነበር ካለች ታዲያ ለምን አሸባሪ እያለች የምትወነጅላቸው በደምህት ሜዳ ሲንሸራሸሩ ዶጋ አመድ አታደርጋቸውም ነበር? የመግለጫው ሃሰትነት እና ግንዛቤ የጎደለው ድክመት አንዱ ይህ ነው!!!የማይመስል ውዥንብር ነው::ምንም ግዜ ከአምባገነኖች የሚጠበቀው ይህ የዘቀጠ መግለጫ የወያኔን ሽንፈት ገሃድ አውጥቶ ምነው አማካሪ የላቸውም ወይ እስከማሰኘት መሳቂያ አድርጓቸዋል::ራስን ለኪሳራ አቀባብሎ መስጠት ማለት እንዲህ ነው::ካድሬዎችን መግለጫውን ደጋግማቹ ስሙት::

ሌላው ገራሚ ነገር የአረናዎች ሽር ጉድ ነው::አረና ፓርቲ በወንድሞቻችን በነአብርሃ ደስታ እስከ አምዶም ገብረስላሴ ድረስ የሚከበር ፓርቲ ነበር ሆኖም የአንድን ግለሰብ ያዉም (ለነጻነት እና ለመብት ?)እታገላለሁ ብሎ ረዥም አመታት በረሃ የከረመ ግልሰብ ተንሸራቶ ሲገኝ እንደ አረና ያሉ ለመብት እና ነጻነት እንታገላለን የሚሉ የድርጅት አባላት ጥያቄ ማንሳት አሊያም ነገሩን አጥንቶ ያለውን ሁኔታ በመገንዘብ መናገር ሲገባቸው ከሕወሓት ካድሬዎች በበለጠ መልኩ በሞላ መመለስ ላይ ሃይሎጋ ማለታቸው አንድም ፖለቲካ አያውቁም አሊያም የድርጅታቸውን የትግል ስልት ገና አላጣጣሙትም/አላወቁትም:: የግለሰቡ በረሃ መግባት ይሁን ተንሸራቶ ከተማ መድረስ ምናልባት ከዘር ጋር ተያይዞ ከሆነ በሕወሓት የላላውን ገመድ የባሰ ከማላላት ውጪ ምንም አይፈይድም::ፖለቲካ በስሜት በጥቅም በብሄር እና በፕሮፓጋንዳ ከታጀበ እንደሚበላሽ ማወቅ አለብን::ተላላኪነትን ባልበሰሉ ዲያስፖራዎች እና ስደተኞች ላይም እያየነው ነው::

ሶስተኛው የታጋይ ሞላ አስገዶም ኩርፊያ እና የመንደርተኝነት አጀንዳ ድምዳሜው ነው::ታጋዩ ሞላ ከጅምሩ የፖለቲካ አኩራፊ ነው ለማለት ያስችላል የመንደርተኝነት አባዜ የተጠናወተው በጅምሩ በሕወሓት መርሃግብር የታሸው ሞላ ከድሮም ከበረሃው የወያኔ ትግል ጀምሮ አኩራፊ ነበር:: በማኩረፍ ሲንከባለል እዚህ ደርሷል::ሞላ በወያኔ ላይ ጦርነት መጀመር የፈለገው ለስልጣኑ እንጂ ለኢትዮጵያ አልነበረም::ይህ ደሞ ከአመጥቱ ጀምሮ የተገራበት ፖለቲካ እና ኩርፊያው ምስክር ነው::ታጋይ ሞላ በሕወሓት ቆይታው ዘሎ ከኤርትራ በረሃ ያስገባው በሕወሓት ውስጥ የነበረው የአድዋ እና የተምቤን የመንደርተኝነት የስልጣን ትንቅንቅ እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግፍ በዝቶበታል የሚል የነጻ አውጪ ጥያቄ አንግቦ አይደለም::የደምሕት መሪዎች ይሁኑ ወታደሮች የነጻነት ትግል ያደርጉ ከነበረ ትግላቸው በመርህ በአላማና በእምነት ላይ የተመሰረተ አልነበረም የሚታገሉት በእምነት ሳይሆን ከኋላ ለሚገፋቸው ልዩ ሃይል ነበር ወደ ሚል የዘር ልጓም መስመር ላይ ተሳስበናል::በተለያዩ ጊዜያት ከወያኔ መዋጋት አለብኝ ብሎ ይጠይቅ የነበረው ታጋይ ሞላ ከፍተኛ (የስልጣን ጥም?) እንዳለበት በዚህ ሰሞን የሚወጡ መረጃዎች ጠቁመዋል::እርግጥ በቂ ሃይል ቢኖረዉም ከወያኔ የማይዋጋበት ምክንያቱ አሊያም መዋጋት አለብን የሚለው ጥያቄው ያልተመለሰበት ምክንያት ማወቅ አስፈላጊ ባይሆንም በሞላ የትግል ሂደት ዙሪያ የሚያጠነጥኑ መረጃዎች ግን እንደሚያመለክቱት ሞላ የተንቤንን አጀንዳ ይዞ አሊያም በሌላ አነጋገር የመንደርተኝነት አጀንዳ ይዞ ይዋልል እንደነበር ድምዳሜው ያስረዳል ያሳየናል:: እወነት እና ንጋት እያደር ይጠራል::ከአቋም መልፈስፈስ መንሸራተት ይሰውረን:: ለተሳዳቢዎች እና ለወመቴ እመጫት ፖለቲከኞች ልብ ይስጥልን::‪#‎ምንሊክሳልሳዊ‬