ሊቆም የሚገባው ጥላቻ ምቀኝነት ቅናት ክፋት እና ግለኝነት የተጠናወተው ፖለቲካ

Minilik Salsawi መልካም እና ጽኑ ታጋዮች እንደተጠበቁ ሆነው በስለናል የትግል ልምድ አለን ከሚሉ ፖለቲከኞች ጀምሮ እዚህ ግቡ የማይባሉ ገደል ማሚቱዎች ድረስ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ቦርቅቀው ለማተራመስ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም::ከኛ በላይ ላሳር የሚሉ እንጭጭ ፖለቲከኛ ነን ባዮች ጥቂቶች ሰፊዉን ሜዳ በተግባር ኣልባ ፕሮፓጋንዳ ብቻ አጣበዉት ሌላው እጁን አጣጥፎ ሲያይ መመልከትም ግርምትን ይፈጥራል::የኢትዮጵያ ፖለቲካ የሰከረ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ይህን ያህል ተተራምሷል ለማለት ግን አያስደፍርም::የሕዝብ ማንዴት ያሌላቸው ፖለቲከኞች ራሳቸውን የሕዝብ ወኪል አሊያም በሕዝብ የተቀቡ አድርገው ሲያቀርቡም የፖለቲካ እብደቶች እየገነኑ ይመጣሉ::በሃገራችን ፖለቲካ ውስጥ የሚታዩ የፖለቲካ ጥላቻ ምቀኝነት ግለኝነት ቅናት የመሳሰሉት ለውጡ በእንብርክክ እያስኬዱ የሚገኙ ሲሆን ሂደቶን ሁሉ ባለህበት እርገጥ ሆነዋል:: እንደኔ እምነት ጥላቻ ምቀኝነት ቅናት ክፋት እና ግለኝነት የጎሳ እና ከፋፋይ ፖለቲካ የሚከተለ እንደ ሕወሓት ያሉ ድርጅቶች ያነገቡት አርማ ነው::
በየሄድንበት በጎራ ተከፍሎ ጥላቻ ሲሰበክ በያረፍንበት ለለውጥ ሰራን የሚሉ ሰዎች ግለሰቦችን አሊያም የፖለቲካ መሪዎችን በጥቅሉ የለውጥ ሃይሎችን ሲያብጠለጥሉ ማየት ያማል::ይህ በግለሰብ ደረጃ ተንከባሉ የፖለቲካ ሰዎችን አሊያም የለውጥ ሃይሎችን መዘርጠጥ ይሁን ማብጠልጠል የወረደ ፖለቲካ ነው::ያዉም ክፉ የፖለቲካ ሃሜት::ተሽሎ የተገኘ የዳበረ ሃሳብ ባልቤት የሆነ የፖለቲካ ሰው ከተገኘ የደጋፊዎቹን ያህል የፖለቲካ ምቀኞቹም ይበረክቱበታል::በፖለቲካው አለም ሃሳብን በሃሳብ ማሸነፍ እየተቻለ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ግን የፖለቲካ ሰዎችን ማብጠልጠል ከተቻለ ማስመታት ካልተቻለ በወረደ ቋንቋ ስማቸውን ማጠልሸት ስራ ሆኖ ተይዟል::አለም ከዘር ከሃይማኖት ከቀለም እና የተለያዩ ልዩነቶች ተገላግሎ በአንድነት ስር ለመጠለል በሚያደርገው የቴክኖሎጂ እድገት ሩጫ ውስጥ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ግን በጎሳ ታጥሮ በግፍ ተከቦ እርስ በእርሱ ሲጠባጠብ ይስተዋላል::

ከገዢው ፓርቲ ጀምሮ የለውጥ ሃይል ነን እስከሚሉ ድረስ ከፍተኛ የሆነ የክፋት የጥላቻ የምቀኝነት የቅናት እና ግለኝነት ፖለቲካ ሲያራምዱ በገሃድ እናያለን::ድርጅቶቻችንን ደግፈን ለሕዝብ እየሰራን ነን ከሚሉ እስከ ድርጅታቸው እስከከዱ ሰዎች ድረስ በምቀኝነት እና ቅናት ተሞልተው የፖለቲካ ሰዎችን ሲያብጠለጥሉ ሲሰድቡ የለውጥ ሃይሎችን ሲያንቋሽሹ ውለው ያድራሉ::ይህ ደግሞ አውቀናል ተምረናል ከሚሉ ጀምሮ እስከ ገደል ማሚቱዎቻቸው ድረስ እየታዘብናቸው ነው::ስለ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ሂደት ምንም እውቀት ከሌለው የመኖሪያ ፍቃድ ለማግኘት ሲል ከድርጅቶች እንከሚታከከው ድረስ ፖለቲካውን/የለውጥ ትግሉን ሳያውቁት በተላላኪነት ብቻ ጥልአሸት ሲቀቡት ይስተዋላል::

የአንድ ድርጅት አባላት የሆኑ ወጥ ካድሬዎች ለኢትዮጵያ እነሱ ብቻ የተፈጠሩ አድርግ ሲያዩ ሌላውን እንደ እንጀራ ልጅ አድርገው ሲገፉ ማየት ያማል::ይህ ብቻ አይደለም ስህተታቸውን ስትነግራቸው የሚያብጠለጥሉ ካለስም ስም ሰጥተው ጥላሸት የሚቀቡ በገዢ መደብ በርካቶች ቢሆኑም በለውጥ ሃይሉም ውስጥ ተሰግስገው እያፏጩ ይገኛል::አሁን አሁን ደሞ የለውጥ ሃይል ነን በሚሉ ከሃዲዎች እና የገደል ማሚቱኦች እንዲሁም ስሜት እና ፕሮፓጋንዳ በተደበላለቀባቸው ሰዎች ላይ የፖለቲካ ክፋት ምቀኝነት እና ቅናት ብሶ ተገኝቷል ይህ ደግሞ ለለውጥ በሚድረገው ሂደት ላይ ችግር እና አለመተማመን ስለሚፈጥር በጊዜ ሊታረም የሚገባው ጉዳይ ነው::ጊዜው የለውጥ ነው:;ሕዝብ ለውጥ ይፈልጋል እስካልን ድረስ የሕወሓት የፖለቲካ ውጤቶች የሆኑት ጥላቻ ምቀኝነት ቅናት ክፋት እና ግለኝነት የተጠናወተው ፖለቲካ ሊቆም ይገባል:: ‪#‎ምንሊክሳልሳዊ‬