ደራሲ ጋዜጠኛ እና ዲፕሎማት አምባሳደር ዘውዴ ረታ አጭር የሕይወት ታሪክ (1927 - 2008) እና መጽሃፎቻቸው


የኤርትራ ጉዳይ
በዚህ ርዕስ ተጽፎ የቀረበው ታሪክ በሶስት ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ የተመረኮዘ ነው፡፡
1ኛ. አብዛኛው የኤርትራ ሕዝብ ፣ ከባዕድ አገዛዝ ለመላቀቅና ወደ መሠረት አገሩ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ኢትዮጵያ ወይ ሞት ብሎ በመታገል ምን ያህል መከራና ፈተና እንደተቀበለ
2ኛ. የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ኤርትራን ከኢትዮጵያ ጋር ለማዋኃድ በአራቱ ኃያላን መንግሥታት ዳንነትና ቀጥሎ በተባበሩት መንግሥታት ሸንጎ ላይ ለብዙ ዓመታት ያደረገው ፋታ የሌለው ሙግት ምን ውጤት እንደሰጡ
3ኛ. በተባበሩ መንግሥታት ሸንጎ ላይ ኤርትራ በፌዴሬሽን ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቀላቀል ፣ ፍርዱ እንዴት እንደተወሰነና፣ ከዚያም ለአሥር ዓመታት የተካሄደው የፌዴሬሽን አስተዳደር በምን መልክ ይሠራበት እንደነበረና በኃላም በምን አኳኋን እንደፈረሰ
እውነተኛውን ታሪክ የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች እንዲያውቁት በዝርዝር የተዘጋጀና ከፍ ያለ ጥረት የተደረገበት ነው፡፡

======================================================================


ተፈሪ መኰንን ረዥሙ የሥልጣን ጉዞ
በሚል ርዕስ እንደ አ.አ. በሐምሌ 1905 ዓ.ም. ለአንባቢዎች የቀረበው መጽሐፍ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ንጉሠ-ነገሥት ሆነው ኢትዮጵያን መምራት ከመጀመራቸው በፊት ደጃዝማች ተፈራ መኰንን ከሐረር ጠቅላይ ገዥነት ተነስተው በምን አኳኋን ባለሙሉ ሥልጣን አልጋወራሽ ለመሆን አንደበቁና ዘውድ እስከጫኑበት ጊዜ ድረስ የኢትዮጵያን መንግሥት ሲመሩ እንደቆዮ የሚያስረዳ ነው፡፡
ብዚዎች አንባቢዎች አንደሚያውቁት ከአፄ ምኒልክ ሕየወት ፍጻሜ በኋላ በአገራችን በያለበት እየተቀመመ የሚሠራጨው የአፈ ታሪክ ተፈሪ መኮንን የኢትዮጵያ መሪ ለመሆን የበቁት ልጅ ኢያሱን በኩዴታ ጥለው ንግሥት ዘውዲቱን በሐኪም መርፌ አስገድለው ነው የሚል ነው፡፡
ደራሲው በዚያን ዘመን የተካሄደውን የኢትዮጵያን ታሪክ ለረዥም ጊዜ ምርምርና ጥናት በማካሄድ
1ኛ. ልጅ ኢያሱ ከሥልጣን እንዴት እንደወረዱ ፣ ወይዘሮ ዘውዲቱ ምኒልክ ንግሥተ ነገሥታት ተብለው ዘውድ ለመጫን እንደበቁ
2ኛ. ለመንግሥቱ ሥራ አመራር የራስ መኰንን ልጅ ተፈሪ መኰንን ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴና አልጋ ወራሽ ሆነው እንደተመረጡ
3ኛ. ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ ከዚህ ዓለም በሞት እንደተለዩ ትክክለኛውን ታሪክ ለአንባቢዎች ለማቅረብ ደራሲው ብርቱ ጥረት አድርጓል፡፡
====================================================================


የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት
ርዕሱ እንደሚያስረዳው ኢትዮጵያን ለአርባ አምስት ዓመታት ያህል በንጉሠ ነገሥትነት ሲያስተዳድሯት የኖሩት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የመጀመሪያዎቹን የሃያ አምስት ዓመታት የመንግሥታቸውን አመራር ታሪክ ይህ መጽሐፍ ተንንትኖ አቅርቧል፡፡
በዚህ በሃያ አምስት ዓመታት ዘመነ መንግሥት ውስጥ
1ኛ . የፋሽስት ጣሊያን ወረራ አመጣጥ
2ኛ. የኢትዮጵያን ነጻነት ለማዳን ንጉሠ ነገሥቱ በዤኔቭ የመንግሥታት ማህበር ሸንጎ ላይ ያደረጉት ሙግትና በመጨረሻም ሊግ ኦፍ ኔሽን ያደረገው አሳዛኝ ውሳኔ
3ኛ. ሙሶሊኒ ከሂትለር ጋር ተሰልፎ የአውሮፓን መንግሥት በጦር ሲወጋ ፣ እንግሊዞች የኢትዮጵያን ነፃነት ለማስመለስ አገራችንን ከያዙ በኋላ የጫኑብን የሞግዚት አስተዳደር እንዴት እንደነበረ
4ኛ. ነፃነታችን ከፋሽስት እጅ ከተመለሰ በኋላ ከእንግሊዞች የሞግዚት አስተዳደር ለመላቀቅ ምን ያህል ድካም እደጠየቀ
5ኛ. ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በምሥጡር ወደ ስዌዝ ካናል ተጉዘው ከአሜሪካው መሪ ከፕሬዚዳንት ሩዝቬልት ጋር ያደረጉት ንግግር
6ኛ. የኢትዮጵያ ከእንግሊዞች የሞግዚት አስተዳደር ከተላቀቀች በኋላ በአገር ውስጥ የሁለት ሰዎች (መኮንን ሀብተወልድና ወልደ ጊዮርጊስ ወልደ ዮሐንስ) የሥልጣን አነሳስና ትብብር ንጉሠ ነገሥቱን ምን ያህል እንደአሳሰባቸው
7ኛ. ከእነዚህ ከሁለቱ ሰዎች መካከል የሥልጣን ኃይላቸው አስጊ ሆኖ የተገመተውን ፣ ጸሐፊ ትዕዛዝ ወልደ ጊዮርጊስን በሽረት ከካቢኒያቸው ለማራቅ ንጉሠ ነገሥቱ የወሰዱት እርምጃ
በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በዝርዝር ስለተገለጸ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህንን እውነተኛ ታሪክ አንብቦ ለመረዳት ይችላል፡፡
http://zewderetta.com/

 
ታዋቂው ዲፕሎማት የታሪክ ምሁር ደራሲ እና ጋዜጠኛ አምባሳደር ዘውዴ ረታ በ81 አመታቸው በለንደን አረፉ::የአምባሳደር ዘውዴ ረታን (1935 – 2015) ነፍስ ይማር! ለቤተሰቦቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸውም መጽናናትን ይስጥ! ስላበረከቱልንና ስላስተማሩን መልካም ነገር ሁሉ እናመሰግናለን!
የአምባሳደር ዘውዴ ረታ አጭር የሕይወት ታሪክ
ዘውዴ ረታ በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ነሐሴ 7 ቀን 1927 ዓ.ም አዲስ አበባ ተወለደ
ከ1033 እስከ 1945 ዓ.ም ቀድሞ ደጃዝማች ገብረ ማርያም ይባል በነበረውና ኋላ ሊሴ ገብረማርያም ተብሎ በተሰየመው የፈረንሣይ ትምህርት ቤት የመጀመሪያውንና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አከናውኗል፡፡
ከ1945 እስከ 1948 ዓ.ም በጋዜጣና ማስታወቂያ መሥሪያ ቤት የቤተመንግሥት ዜና ጋዜጠኛና በራዲዮ ዜና አቅራቢ
ከ1948 እስከ 1952 ዓ.ም በፓሪስ የጋዜጠኝነት ሞያ በማጥናት በዲፕሎማ ተመረቀ
ከ1952 እስከ 1954 ዓ.ም የኢትዮጵያ ድምፅ ጋዜጣና የመነን መጽሔት ዲሬክተር
ከ1954 እስከ 1955 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሬዲዮ የብሔራዊ ፕሮግራም ዲሬክተር
ከ1955 እስከ 1958 ዓ.ም የኢትዮጵያ ወሬ ምንጭ ዋና ዲሬክተር
ከ1958 እስከ 1960 ዓ.ም የማስታወቂያ ሚኒስቴር ረዳት ሚኒስትር
ከ1960 እስከ 1962 ዓ.ም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ
ከ1956 እስከ 1962 ዓ.ም የፓን አፍሪካ ኒውስ ኤጀንሲ ማኅበር ፕሬዚዳንት
ከ1962 እስከ 1967 ዓ.ም ወደ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ተዛውሮ
በፓሪስ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሚኒስትር ካውንስር
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ም/ሚኒስቴር
በሮም እና በቱኒዚያ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት አምባሳደር ሆኖ ሠርቷል
በጠቅላላው በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት የሀያ ሁለት ዓመታት አገልግሎት ካበረከተ በኋላ በደርግ ዘመን ከ1967 ዓ.ም ጀምሮ ስደተኛ ሆኖ በአውሮፓ በቆየበት ዘመን በሮም የኢንተርናሽናል ድርጅት ውስጥ (IFAD) ለአሥራ ሦስት ዓመታት በፕሮቶኮልና በመንግሥታት ግንኙነት ጉዳይ ኃላፊ ሆኖ ሠርቷል፡፡
በ1959 ዓ.ም ጋብቻውን መሥርቶ ከሕግ ባለቤቱ ከወይዘሮ ገሊላ ተፈራ ጋር ሦስት ልጆች አፍርተው ኖረዋል፡፡ ከንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት የምኒልክ የመኮንን ደረጃና የኢትዮጵያ የክብር ኮከብ አዛዥ መኮንን ኒሻን ተሸልሟል፡፡ እንዲሁም ከአፍሪካ ፣ ከእስያና ከአውሮፓ በድምሩ ከሀያ ሁለት አገሮች የታላቅ መኮንን ደረጃ ኒሻኖች ተሸልሟል፡፡ ከዚህ ቀደም በ1945 እና በ1946 ዓ.ም ካዘጋጃቸው አራት ቲያትሮች ሌላ ፤ በ1992 ዓ.ም የኤርትራ ጉዳይ በ1997 ዓ.ም ተፈሪ መኮንን በቅርቡም የቀድሞ ኃይለሥላሴ መንግሥት የተሰኙትን መጻሕፍቶች ጽፏል፡፡
ምንጭ፦ http://zewderetta.com/
ነፍስ ይማር!!