ወያኔ/ኢሕአዴግ በውይይት ያምናል ብሎ ማሰብ መርዝ እንደመጠጣት ይቆጠራል::

Minilik Salsawi (ምንሊክ ሳልሳዊ)  የኢትዮጵያ ፖለቲካ ሰከን ያለ እና ረጋ ያለው ወዳጅ ይፈልጋል::በፈላ ሰአት ሁሉ በስሜት መነዳት በፕሮፓጋንዳ መደበላለቅ ትልቅ አደጋ ያስከትላል::እኛ የለውጥ ሃይሎች ማለት ከራሳችን እና ከባለፈው ሂደቶቻችን መማር ያልቻልን የራሳችን ጠላቶች እንደሆንን እዚህ ደርሰናል::የወያኔ ጉጅሌ አገዛዝ ምርጫውን አሸነፍኩ ባለ ማግስት ተቃዋሚዎችን በምመሰርተው መንግስት ውስጥ ሃሳባቸውን አሳትፋለው ብሎ ሲያቅራራ ነበር::መወያየት መመካከር ልዩነትን አቻችሎ በሃገራዊ አጀንዳ ዙሪያ መስራት ታላቅነት ነው ይህ ግን ወያኔ ጋር የለም ወያኔ መሰሪ ነው እባብ እንደወዳጅ እያጫወተ ከጀርባ የሚያርድህ ነው::ኑ እንወያይ ኑ እንመካከር ብሎ ስንቱን ፓርቲ አክስሟል…ስንቱን አድክሟል…ስንቱን ታጋይ ከጨዋታ ውጪ አድርጓል..ኧረ ስንቱን ?
 
በአሁኑ ወቅት እስር ቤት ያሉ እንደ አንዱአለም እና ሃብታሙ ያሉ በሳሎች የዚሁ የእንወያያ ጥሪ ሰለባ ናቸው:;ጥርስ የተነከሰባቸው ወያን በጠራቸው የውይይት መድረኮች ላይ በተናገሩት ሕዝባዊ ጠንካራ ንግግሮቻቸው ነው::ወያኔ በውይይት እና በመመካከር የሚያምን ቢሆን ኖሮ ብርሃኑ ነጋን የሚያክል የስልጣን ጥም ያሌለበት ምሁር እና ለሃገር የሚጠቅሙ ሰዎች (ቢያዋጣም/ባያዋጣም) የትጥቅ ትግል እናደርጋለን አይሉም ነበር:;ወያኔ በውይይት እና በመመካከር ቢያምን ኖሮ ሃሳባቸውን በነጻነት የገለጹ ባለ ብዕር ኢትዮጵያውያንን ካለምንም ማስረጃ ወህኒ አያጉራቸውም ነበር:;ሌላም ምሳሌ አለ በወንድማችን አቡበከር አህመድ የሚመራው የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴያችን የሕዝበ ሙስሊሙን ጥያቄ ይዞ ሲነሳ ኑ ተወያዩ እንወያይ ብሎ ባስቀመጣቸው ቢሮ የተያዘው ቃለ ጉባዬ ቀለም ሳይደርቅ ነው ንጹሃኑን አሸባሪ ብሎ የፈረጃቸው:: ሌላም ሌላም ብዙ ማለት ይቻላል::ከአማራጭ ሃይሎች ምክር ቤት ጀምሮ እስከ ራሱ እስከጠራው አይሲስ ሰልፍ ድረስ ወያኔ በዜጎች ላይ መሰሪ ተግባሩን ተግብሯል::

ወያኔ ወይይት ማለት ለሱ በተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ለማሾፍ እና ለመዝናናት የሚጠቀምባት የፖለቲካ ማጭበርበር እንዲሁም የዋሃንን ለማታለል እና ምእራባውያንን ቀልብ ለመግዛት ብሎም የሚያፍናቸውን እና የማይፈልጋቸውን የፖለቲካ ሰዎች ለመለየት ይጠቀምበታል::በሃገር ቤት የሚገኙ በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች የወያኔን መሰሪ ፖለቲካ ጠንቅቀው ያውቁታል::ወያኔ ምንም የሚፈይደው ነገር እንደሌለም አሳምረው ያውቁታል::ወያኔ ኑና ላወያያቹ ያለው ላለፉት አስርተ አመታት ተወቅጦ ተወቅጦ ያልተሳካውን እና ሲንከባለል ለዛሬ የደረሰውን የከሰረውን የትራንስፎርሜሽን እና እድገት እቅድ እንጂ በሃገሪቱ ስላሉት ችግሮች አይደለም::ይህ ድህነትን እቀርፍበታለው ያለው እቅዱ እንኳን ድህነትን ሊቀርፍበት ይቅርና የደሃ ደሃ በመፍጠር መጪ ትውልዶች የማይከፍሉትን እዳ በመበደር ሃገሪቷን ለብሄራዊ ውርደት ሕዝብንም ለኑሮ ዝቅጠት ዳርጎታል::

ወያኔ ስለታሰሩ የፖለቲካ እስረኞች ስለ ሕሊና እስረኞች እና ስለ ሞተው ፍትህ በሙስና ተዘፍቆ ሕዝብን ስለሚያጉላላው አስተዳደር ስለ ኑሮው ውድነት ችግር አሊያም ስለ ሃገሪቱ አጠቃላይ መሰረታዊ ጉዳዮች እንወያይ ብሎ ተቃዋሚዎችን አልጠራም::ይህ ቢሆን ደግ ነበር:;ውይይቱን የጠራው አሁንም ልብ ማለት ያለብን ጉዳይ ቢኖር ስለተሽመደመደው እና ለሃገር ኪሳራ ስለሆነው የትራንስፎርሜሽን እቅድ እንወያይ ስላለ ይህ ደግሞ ምንም ፋይዳ የለውም::ወያኔ ስለታሰሩ ዜጎች ቅንጣት ያህል ሰብኣዊነት እና ርሕራሄ አይሰማውም:: ከስራ ከቀየ ስለተፈናቀሉ ይሁን ስለተሰደዱ ዜጎች ምንም ደንታ የለውም::ወያኔ ሲፈጥረው ቻሌንጅ መሆን የማይችል የማፊያ ቡድን ነው::እያወቅን እየተረዳን ካለፈው የማንማር ጨቅላ እና የዋህ ፖለቲከኞች ከሆንን በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ለማምጣት ያስቸግራል:: ጠንካራ እና የተቀናቃኝን የፖለቲካ ስትራቴጂ ለማክሸፍ የለውጥ ሃይሎች እርስ በእርስ መመካከር ያስፈልጋቸዋል::ከወያኔ ጋር ግን እደራደራለሁ እወያያለሁ አሊያም እመካከራለሁ ማለት መርዝ እንደመጠጣት ይቆጠራል::ተለጣፊ እና ታማኝ ተቃዋሚዎቹ ይሰብሰቡለት::አሁንም ንቃት ያስፈልገናል::እንንቃ!!!

Minilik Salsawi's photo.