የሃሰት ፕሮፓጋንዳ - የቁጥር ቁልል - መሬት ላይ ያለው እውነት - ራዲዮ ፋና (ምንሊክ ሳልሳዊ)

Minilik Salsawi - የወያኔው ጉጅሌ አገዛዝ የፕሮፓጋንዳ ወፍጮ የሆነው ራዲዮ ፋና የአገሪቱ አጠቃላይ ምርት 1 ነጥብ 24 ትሪሊየን ብር ደረሰ የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ 691 የአሜሪካ ዶላር መድረሱን እየደሰኮረ ይገኛል::እኛ እስከምናውቀው ድረስ 1.24 ትሪሊዮን ብር የአገሪት አጠቃላይ ምርት ሳይሆን በአገሪቱ በፖሊሲ ድርቀት የተከሰተውን ረሃብ ለእርዳታ የተጠየቀው ገንዘብ ነው::አስልቶ መድረስ ይቻላል::የአንድ ዜጋ የነብስ ወከፍ ገቢ እንኳን 691 ዶላር ሊደርስ አይደለም በአለም ታይቶ የማይታወቅ የደሃ ደሃ ዜጋ የተፈጠረበት ብሄራዊ ውርደት ላይ ነን::የአለም ባንክ እና የአይኤምኤፍ ሪፖርቶች ያገጠጡ እውነቶችን አስቀምጠዋል:: ወያኔዎች ዘላለማቸውን አጣብቂኝ ውስጥ ሲገቡ ሕዝብን ለማደናበር እና ለማጭበርበር የቁጥር ቁልል ይጠቀማሉ::ሕዝቡ ከነሱ ቀድሞ መንቃቱን አለመገንዘባቸው የሚገርም ነው::

የዜጎች የነፍስ ወከፍ ገቢ 691 የአሜሪካ ዶላር የሚለው ወያኔ እየመራው የሚገኘው ኢኮኖሚ ተሽመድምዶ ሃገርን ረመጥ ላይ እየከተታት ሲሆን የወያኔ ሳቦታጅ ጥቂት ሰዎች በሃገር ሀብት በህዝብ ላይ እንዲፈነጩ አድርጓቸዋል::በሃገሪቱ ማንኛውም አይነት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ከበፊቱ በተለየ እና በባሰ ሁኔታ ተንኮታኩተው አፈር መልበሳቸው በይፋ ታውቋል::ለስርኣቱ ቅርበት አላቸው ያሉ ምንጮች ወያኔ ወገቡ እንደተሰበረ እየተናገሩ ነው::በፖለቲካው ረገድ የስርኣቱ ገዢ ፓርቲዎች እርስ በርስ አለመተማመን ደረጃ ላይ ከመድረሳቸውም በላይ አመራሮቹ አድፍጠው አንዱን አንዱን እየጠበቀ በፍራቻ አለም ውስጥ እየዋተቱ ይገኛሉ::አቤት የሚባልበት እየጠፋ ነው፡፡ የውሳኔ ሰጪ ያለህ ቢባል መልስ አይገኝም፡፡ ፋይሎች የሚያያቸውና የሚያነባቸው አጥተዋል፡፡ መልካም አስተዳደር ገደል ገብቷል::በአላማ ሳይሆን በጊዜያዊ የመኖር ሂደት ላይ የተመሰረተው የካድሬዎቹ ሩጫ ድካምን በመፍጠሩ ሁሉም በያለበት ቆም ብሎ እያሰበ ሲሆን አሳቡም የገፈፍኩትን ገፍፌ ሃገርን ድባቅ መትቼ ልሽሽ ሆኗል::
በድርቅ የተመታች አገር አገዛዝ በረሃብ የሚሰቃዩ ዜጎቿን መመገብ ያልቻለች አገር አገዛዝ ቁጥር እየቆለለ መጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የ10 ነጥብ 1 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ማስመዝገቧን በዚህም ኢንዱስትሪው የ20 ነጥብ 2 በመቶ፣ ግብርና የ6 ነጥብ 4 በመቶ እንዲሁም የአገልግሎት ዘርፍ የ10 ነጥብ 8 በመቶ ዕድገት ተመዝግቧባቸዋል ቢባል የሚሰማ ጆሮ የለንም::ኧረ እፍረት ይኑር::መሬት ላይ ያለው እውነት ሌላ ነው::ችግር ድህነት የደሃ ደሃ ሕዝብ የሚበላው ያጣ የተራቆተ ምስኪን ዜጋ::

ካመጡት ጊዜ ጀምሮ ያልተሳካው ጭራሽ ድህነትን ያስፋፋው የትራንስፎርሜሽናቸው እቅድ አቃጥለውት ስልጣን መልቀቅ ሲገባቸው ይባስ ብለው የነፍስ ወከፍ ገቢው መጨመር አገሪቱ እያስመዘገበችው ያለው ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት ከ10 ዓመት በኋላ መካከለኛ ገቢ ያላት አገር እንደምትሆን አመላካች ነው በማለት በውሸት ክምችት እውነትን ለመፍጠር እየተፍጨረጨሩ ነው::አገሪቱ እንኳን ፈጣን እድገት ልታስመዘግብ ይቅርና በብድር እና እዳ ተወጥራ በዜጎች ድህነት እና በኑሮ ውድነት ተከባ በድርቅ እና ረሃብ ተሸብባ የለጋሽ አገሮችን እርዳታ እየለመነች ሀገር ባለችበት በዚህ ወቅት ላይ ያሌለ አለ እያሉ ማውራት በሕዝብ ላይ ማሾፍ ሲሆን የተጭበረበረ አፋኝ ፖለቲካ ያስከተለው የኢኮኖሚ መንኮታኮት የአገሪቱን የፖለቲካ አናቶች ለውጥ እንዳያመጡ በመተብተብ ቀውስ ውስጥ የከተታቸው መሆኑን ከስብሰባዎች እና ከጭብጨባዎች ብዛት እየታዘብን ነው::በሌላ በኩል ሚዲያዎች ህዝብን መዋሸታቸው እና ለፖለቲካ ፍጆታ ብቻ መዋላቸው አገሪቷ እንድትንኮታኮት በር የከፈተ ሲሆን የዚህ መፍትሄ ስልጣን መልቀቅ ነው::‪#‎ምንሊክሳልሳዊ‬