አሳስሮ አስገድሎ አሰድዶ ጩኸት ከዛ ዝም ... ግን ዝምታችን እስከመቼ ነው::ተቃዋሚ ሃይሎች ራሳችንን እንፈትሽ::

Minilik Salsawi (ምንሊክ ሳልሳዊ) - መለስ ብለን የተጓዝንበትን መንገድ እንቃኝ ::ለለውጥ እንታገላለን የሕዝብ ነጻነት እና መብት መረጋገጥ አለበት የሚሉ እና ተመሳሳይ ሕዝባዊ ጥያቄ የነገብን የለውጥ ሃይሎች እንሁን የተቃዋሚ ፓርቲ ፖለቲከኞች እና አባሎቻቸው ሁሉም የለውጥ ሃይል ራሳችንን ልንፈትሽ ይገባል::የያዘው መንገድ አያዋጣም በፕሮፓጋንዳ ይሁን በሌላ ስልት የቀን ስሜታዊ ጡዘትን ከመፍጠር ውጪ ምንም የተፈየደ የተሰራ ነገር የለም::ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጣቸውን ይፈትሹ፤ድክመታቸው ሲነገራቸው ለጥንካሬያቸው ስለሚበጅ በእጅጉ ያስቡበት፡፡ በኢትዮጵያ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ባለመኖሩ ጉዳት እየደረሰ ነው፡፡በግለሰብ ደረጃ የተወሰኑ አክቲቭኢስቶች ቢኖሩም የወያኔ አገዛዝ በአጭሩ ይቀጫቸዋል::ተቃዋሚ ነኝ የለውጥ ሃይል ነኝ የሚለው አካል እርስ በእርስ በመፈራረጅ በመወነጃጀል በመሰዳደብ ተወዳዳሪ አልተገኘለትም::የጋራ ጠላትን ወደ ጎን ትቶ እርስ በእርስ በመናቆር ትግል የለም::

ጠንካራ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ እውን ማድረግ አልተቻለም፡፡ ለዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አስፈላጊ የሆነው ጠንካራ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ በተግባር በኢትዮጵያ እውን መሆን አልቻለም፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጠንካራ መሆን ያልቻልነው ገዥው ፓርቲ እንዳንጠናከር ስላደረገን ነው የሚል መከራከሪያ ሊያቀርቡ ይችላሉ፡፡ ገዥው ፓርቲ ተቃዋሚዎች እንዳይጠናከሩ ከውስጣዊ ሰርጎ ገብነት ጀምሮ እስከ አደባባይ ግድያ አፈና እና እስር እንግልት ይፈጽምባቸዋል ይህ የማይካድ ሃቅ ነው።ይህንን ሰብሮ ለመግባት ከባድ መስዋትነትን ቢጠይቅም በፓርቲዎች ውስጥ ለውስጥ ሽሽት እና የፖለቲካ ድብብቆሽ ነግሷል::ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያልተጠናከሩበት ምክንያት ከአገዛዙ አውሬያዊ ጭካኔ በተጨማሪ በራሳቸው ድክመት፣ ጉድለትና የብቃት ማነስ ነው ማለትም ይቻላል ፡ ከማንም በፊት ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ላለመኖሩ ተጠያቂ የምናደርገው ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ራሳቸውን ነው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጠንካራ፣ ግልጽና፣ ይፋ የሆነ የትግል ስልት እና ስትራቴጂ የላቸውም ከውስጥ ይሁን ከውጪ ያለው የገንዘብ ድጋፍ ሃይል እንደፈለገ ያሾራቸዋል::እየሾሩ እየነፈሱ ጠንካራ ሐሳብ አለመኖር ብቻ ሳይሆን ጠንካራ አደረጃጀትና ጠንካራ እንቅስቀሴም አያሳዩም፡፡ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኙና እንዲከበሩ ስር ነቀል ለውጥ የሚያመጣ የፖለቲካ ስትራቴጂ አልተከተሉም::

ስለዚህ አንዱና ትልቁ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ድክመት ስር ነቀል የለውጥ የፖለቲካ ስትራቴጂ አማራጭ ሐሳብ፣ አማራጭ ፕሮግራምና አማራጭ ስትራቴጂ አለመከተላቸው ነው፡፡ ሁለተኛው ድክመታቸው አማራጭ አደረጃጀትና የእንቅስቃሴ ጥንካሬ አለማሳየታቸው ነው፡፡ ለመሆኑ ተቃዋሚ ድርጅቶች አባሎቻቸውና ደጋፊዎቻቸው ምን ያህል ይሆናሉ? ድንገት ካልሆነ ለመሆኑ ዓመታዊ ጉባዔ ያካሂዳሉ ወይ? ለመሆኑ በፓርቲያቸው ውስጥ ወቅቱን የጠበቀ ምርጫና ግምገማ ይካሄዳል ወይ? የውስጥ ኦዲት ይደረጋል ወይ? ግልጽነት አለ ወይ? ፓርቲውን ሁሌም የሚመራው አንድ ዓይነት ኃይል ነው? አባላት ይሁኑ የለውጥ ሃይል አክቲቭኢስቶች ከታሰሩ በኋላ ምን ጠንካራ እርምጃ ይውሰዳል? በቂ የሆነ የደህነት እና የስለላ መዋቅር አላቸው ወይ ? ወዘተ የሚለው መታየት አለበት፡፡ሌላው ትልቁ ድክመት ይህ ነው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በውስጣቸው ጥንካሬ አይታይም፡፡ ዲሞክራሲያዊ ሕይወት አይንፀባረቅም፡፡ ይህ የሚያሳየን አማራጭ ሐሳብ መኖሩ ብቻ ሳይሆን፣ አማራጭ ሐሳብ ተይዞም ወደ ድርጅታዊ እንቅስቃሴና ጥንካሬ ካልተቀየረ በተስፈኛ ሚዲያዎች በሲዲና በወረቀት በፕሮፓጋንዳ ብቻ ማሳየት አቅም አለመኖሩን ማሳያ ነው፡፡

በአጠቃላይ ሲታይ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን መሆንና ጥንካሬ ሲባል ተቃዋሚ ፓርቲዎች እንዲጠናከሩ ያስፈልጋል፡፡ በኢትዮጵያ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ባለመኖሩ ጉዳት እየደረሰ ነው፡፡ በኢሕአዴግ ላይ ቅሬታ ያለው ወገን በግራም በቀኝም ሲያይ ጠንካራ ተቃዋሚ ስለማያገኝ፣ ኢሕአዴግን የሚተካ ኃይል ይኖራል ብሎ መተማመን አልቻለም፡፡ ምን ተቃዋሚ አለና እያለ ተስፋ እየቆረጠ ነው፡፡ በመሆኑም ተቃዋሚ ፓርቲዎች በሌላ ወገን ሳያሳብቡ መጀመሪያ ውስጣቸውን ይፈትሹ፤ ድክመታቸውን ይመኑ፡፡ ብቁ ተቃዋሚ ለመሆን ይጣሩ፡፡ ድክመታቸው ሲነገራቸው ለጥንካሬያቸው ስለሚበጅ በእጅጉ ያስቡበት፡፡ የብቁ ተቃዋሚ የጥበብ መጀመሪያም አማራጭ ሐሳብና አማራጭ ጥንካሬ ያለው ስር ነቀል ለውጥ የሚያመጣ የፖለቲካ ስትራቴጂ እስከ መስዋትነት መከተል ነው፡፡አሳስሮ አስገድሎ አሰድዶ ጩኸት ከዛ ዝም ... ግን ዝምታችን እስከመቼ ነው::ራሳችንን እንፈትሽ:: ‪#‎ምንሊክሳልሳዊ‬