የኢትዮጵያውያንን ድምጽ እንደመጋዝ ማየት የህዝብን ችግር ቸል ማለት ለማይፈታ አጣብቂኝ ይዳርጋል::


Minilik Salsawi የህዝብን የልብ ትርታ፣ የሀገር ወዳዶችንና ውጪ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ድምጽ እንደመጋዝ ሳይሆን እንደ አጋዥ በማየት ማግባባት፣ ማስማማት፣ለሃገር ስኬት እና እድገት ለህዝብ ነጻነት እና መብት መከበር ለዜጎች ከእስር እና ስደት መዳን የሚረዳ እና ከመሪ የሚጠበቅ የብልህ እርምጃ ነው፡፡እርግጥ በኢትዮጵያ ያለው ወያኔ መራሹ አምባገነን ቡድን ማግባባትን እና መስማማትን አሊያም መደራደርን የሚጠቀመው ለመበላላት ሃገር ወዳዶችን ለማቀጨጭ አሊያም ለማጥፋት በመሆኑ በሃገሪቱ ላይ ከፍተኛ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ችግር በመፍጠሩ የሕዝብ ችግሮች አግጥጠው ከመውጣታቸውም በላይ ሃግሪቷን እርቃኗን አስቀርቷታል::

የወያኔ ሰራሹ አምባገነን መንግስት ለሃገሪቱ የኢኮኖሚ ችግሮች መፍትሔ ሳይሰጥ ወደ ውስብስብና ግዙፍ ችግርነት እንዲያድጉ በቸልተኝነት በመፍቀዱ ያለ ጥርጥር ወደ ፖለቲካዊ ችግርነት አድጓል ፡፡ የወሎ ረሃብ እንደተነናቀ ወደ አብታዊ ማዕበልነት ተለወጠ፡፡ የሚሊተሪ ዲክታተራዊ አገዛዝ መናጠጥ፣ የቢሮክራሲያዊ በደል ማጠጥ፣ የሥልጣን መባለግና ያላግባብ መበልፀግ የአማጽያንን መፈልፈልና የተቃዋሚን ቁርጠኝነት መውለዱን ወለደ፡፡በአሁኑ ወቅትን ከባለፈው በባሰ መልኩ ሕዝባዊ የለውጥ አብዮቶች በውስጥ እና በውጪ እየተቀጣጠሉ መሆኑ የማይካድ ሃቅ ነው::ይህ የሕዝብን ጥያቄ አለመመለስ የወለደው ሌላ ጥያዌ ወያኔን አጣብቂኝ ውስጥ ከቶታል::

ዛሬም የህዝብን ኑሮና የሀገርን ውስብስብ ችግሮች በወቅቱ የመፍታት ቅን ልቦና ከሌለ ስልጣንን ለህዝብ ለማስረከብ ፍዋደኝነት ካልታየ በሃገሪቱ የተዘጋው የፖለቲካ ምህዳር ህግን ጥላ ባደረገ መልኩ ካልተከፈተ የፍትህ አካላት ከአምባገነን ባለስልጣናት መዳፍ ስር ካልወጡ እና ተመሳሳይ የሆኑ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ችግሮች በኢትዮጵያውያን የጋራ ተሳትፎ ካልተፈቱ ዕጣ- ፈንታ ወዳዘዘው ውድቀት ማምራት ግድ ይሆናል፡፡ በዚህ ጉዳይ ስልጣኑን ይዣለሁ የሚለው አካል ዋንኛ ትኩረት በጠበንጃ የመተማመን የበላይነቱን ድርሻ ይውሰድ እንጂ የተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማህበራትና ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጐች ወዘተ የነገዋ አገራችን ዕጣ-ፈንታ ይመለከተናል ማለት ኤጭ የማይባል ነገር መሆኑን ልብ ማለት ደግ ነው!ገዢ ነኝ የሚለውም ወያኔ ሃገር ወዳዶችን ስለሃገራችን ያገባናል የሚሉ ዜጎችን ሁሉ ከማግለል ከማሰር እና ከማሳደድ የማይቆጠብ ከሆነ ከገባበት አጣብቂኝ መውጣት ካለመቻሉም በተጨማሪ ወደ ማይወጣው ጥልቅ ጉድጓድ እንደሚወረወር ማወቅ ግድ ይላል::

ዕጣ-ፈንታችንን አናመልጥም፡፡ የዕጣ-ፈንታችን አካል ነን፡፡ የምንለው፣ የምናቅደው፣ የምንራዕየው ሁሉ የእኛው አካል ነው፡፡ በተናገርነው እንነገርበታለን፡፡ በደነገግነው እንቀጣበታለን፡፡ በደሰኮርነው እናፍርበታለን ወይም እንኮራበታለን፡፡ በተለይ መንግስት ስንሆን ባወጣነው ህግ እከሌ ከእከሌ ሳንል፣ ወገናዊና ኢፍትሐዊ ባልሆነ መንገድ መተዳደርና መቀጣት አለብን፡፡የመንግሥትነታችን ትልቅ ቁም ነገር የህዝብን ደህንነትና የሀገርን ህልውና መታደግ ነው፡፡ ይህ ዋና ኃላፊነት ነው፡፡ ህዝብ እንዳይሸበር፣ እንዳይጠራጠር፣ ዕምነት እንዳያጣ ማድረግ፤ በአገሩ፣ በመንግሥቱና በኃላፊዎቹ ላይ የመተማመን ስሜት እንዲያድርበት ያደርገዋል፡፡የአስተዳደር ብስለታችን፣ የዲፕሎማሲያችን ጥራት፣ ስለፓርቲና ስለ ሀገር ያለን ግንዛቤ፤ የምንመራውን ህዝብ አመኔታና ተቀባይነት የሚያስገኘው ቁልፍ ነገር መሆኑን መቼም ቢሆን መቼም እንወቅ፡፡ የህዝብን የልብ ትርታ፣ የሀገር ወዳዶችንና ውጪ ያሉ ኢትዮጵያውያንን ድምጽ እንደመጋዝ ሳይሆን እንደ አጋዥ በማየት ማግባባት፣ ማስማማት፣ ለሃገር ስኬት እና እድገት ለህዝብ ነጻነት እና መብት መከበር ለዜጎች ከእስር እና ስደት መዳን የሚረዳ እና ከመሪ የሚጠበቅ የብልህ እርምጃ ነው፡፡