የመዲናችን ጉድ ወሲብ፣ የእራቁት ዳንስ፣ ግብረሰዶማዊነት፣ የአደገኛ ዕፆች ንግድና ዝውውር! በመስከረም አያሌው

የመዲናችን ጉድ
ወሲብ፣ የእራቁት ዳንስ፣ ግብረሰዶማዊነት፣ የአደገኛ ዕፆች ንግድና ዝውውር!
በመስከረም አያሌው
ሁልጊዜም አዳዲስ ነገሮችን ለመቀበል ፈጣን የሆነችው መዲናችን አዲስ አበባ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ከኢትዮጵያዊነት ባፈነገጡ የባእድ ባህሎችና ልማዶች እየተናጠች መሆኑን አንድ ጥናት ከሰሞኑ አስነብቧል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሴቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ቢሮ ‘‘መጤ ባህሎችና ልማዳዊ ድርጊቶች በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በተለይም በወጣቶችና ሴቶች ላይ እያስከተሉት ያለው አሉታዊ ተፅእኖ’’ በሚል ርእስ ያካሄደው ጥናት እንደሚያመለክተው ከሆነ መዲናችን በአሁኑ ወቅት አስደንጋጭ በሆነ ባእድ ልማዳዊ ድርጊቶች ተጥለቅልቃለች።
ከአጠቃላይ የአዲስ አበባ ነዋሪ (2ሚሊዮን 739 ሺ 551) መካከል 1ሚሊዮን 434 ሺህ 164 (52.4 በመቶ)ዎቹ ሴቶች፣1ሚሊዮን 305ሺ 387ቱ (47.6 በመቶ)ዎቹ ደግሞ ወንዶች መሆናቸውን የገለፀው ጥናቱ፤ ከዚህ ውስጥም 1ሚሊዮን 972 ሺህ 476 (77በመቶ)ዎቹ ሴቶችና ወጣቶች እንደሆኑ አስቀምጧል። ይህን ያህል ቁጥር ካላቸው ሴቶች እና ወጣቶች መካከልም አብዛኞቹ ለእነዚህ መጤ ባህሎችና ልማዳዊ ድርጊቶች የተጋለጡ እንደሆኑ ጥናቱ አመልክቷል። ሴቶቹ እና ወጣቶቹ አውቀውም ይሁን ሳያውቁ የገቡባቸው እነዚህ ከኢትዮጵያዊነት ያፈነገጡ ድርጊቶች አይነተ ብዙ ከመሆናቸውም በላይ፣ ከግለሰብ አልፈው በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅእኖ እየፈጠሩ እንደሆነ ተገልጿል።

የቀን፣ የሌሊትና የእርቃን ጭፈራ ቤቶች
ጥናቱ በተለያየ ዘዴ ከአዲስ አበባ ነዋሪዎች አገኘሁት ባለው መረጃ፣ በአዲስ አበባ ውስጥ ከተለመደው ድርጊት ባፈነገጠ መልኩ የግለሰባዊ ስብእናና ክብርን የሚፈታተኑ፣ እንዲሁም የኢትዮጵያዊነትን እሴቶች የሚያዋርዱ የእርቃን ጭፈራ ቤቶች በአዲስ አበባ ውስጥ በመስፋፋት ላይ ናቸው። የእነዚህ ቤቶች ተጠቃሚዎችም ከልጅ እስከ አዋቂ የሚደርሱ ሲሆን፣ ወደ እርቃን ጭፈራ ቤቶቹ የሚመጡትም በቡድን በመሆን እንደሆነ ተገልጿል። በእነዚህ የእርቃን ጭፈራ ቤቶቹ ውስጥ ከእርቃን ዳንስ በተጨማሪም ጫትና ሌሎች እፆች ጥቅም ላይ እንደሚውሉ የተገለፀ ሲሆን፤ እነዚህን እፆች የሚጠቀሙትም አዋቂ ወንዶች ከታዳጊ ሴት ልጆች ጋር እንደሆነ፤ ይህን የእርቃን ጭፈራ ቤት እንደ መዝናኛነት የሚጠቀሙ 102 ተሳታፊዎች ገልፀዋል። በእነዚህ ቤቶች ውስጥ የሚሰሩ የመድረክ ተወዛዋዦችም በአብዛኛው ለውዝዋዜ የሚጠቀሙባቸው አልባሳት ባህልን ያልጠበቁ እና ወሲብ ቀስቃሽ በመሆናቸው ወንዶችን ለወሲብ እንደሚገፋፉ ነው ተሳታፊዎች የገለፁት።
በእነዚህ የእርቃን ጭፈራ ቤቶች የሚታደሙ ሰዎችን በተመለከተም ጥናቱ አንድ ያልተጠበቀ ነገር ይፋ አድርጓል። በጭፈራ ቤቶቹ አካባቢ ከቆሙ ተሽከርካሪዎች በተገኘ መረጃ ብቻ ተሽከርካሪዎቹ የለጠፉት ታርጋ የዲፕሎማት እና የእርዳታ ድርጅት ሲሆኑ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዙት ግን የግል፣ የመንግስትና የንግድ ታርጋ ያላቸው አውቶሞቢሎች ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም ወደ ቦታው መጥተው ‘‘መዝናናት’’ ያልቻሉ አሊያም ያልፈለጉ ታዋቂ ግለሰቦች፣ መንግስታዊ የሆነ እና መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ሰራተኛ እና ኃላፊዎች፣ በንግድ ስራ የተሰማሩ ግለሰቦች እና የውጭ ዲፕሎማቶች ጨፋሪዎቹን ቤታቸው ድረስ በማስጠራት አገልግሎቱን እንደሚያገኙ ዳናሾቹ ከሰጡት መረጃ ለመረዳት ተችሏል። በአጠቃላይ ሲታይም በመንግሥት የኃላፊነት ቦታ ላይ የሚገኙ እና በማኀበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው ባለሥልጣናት እንዲሁም በኢኮኖሚው ውስጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያላቸው ባለሞያዎችና የንግድ ሰዎች የዚህ የእርቃን ዳንስ ታዳሚዎች ናቸው።
አንዲት በዚህ የእርቃን ጭፈራ ቤት ውስጥ የምትሰራ ደናሽ ክፍያ ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞችን ሳይጨምር ከ3ሺ እስከ 14ሺ ብር እንደሚደርስ ነው የተገለፀው። በአብዛኛው ወደዚህ ‘‘ስራ’’ የሚገቡት ወጣት ሴቶችም የኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅ ያለና መልካም የሰውነት አቋም ያላቸው ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም የሁለተኛ ደረጃ፣ የኮሌጅና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ትምህርታቸውን መቀጠል ሲያቅታቸው ወደዚህ ድርጊት እንደሚገቡ የተጠቀሰ ሲሆን፤ ከሞዴሊንግ ማሰልጠኛ ተቋማት የሚመረቁ ወጣቶች እና የምሽት መጠጥ ቤት አስተናጋጆችም እንዳሉበት ተገልጿል።
ከእርቃን ጭፈራው በተጓዳኝ የሚከናወኑ ወሲብ ቀስቃሽ እንቅስቃሴዎች፣ የሚጠቀሟቸው መጠጦች እና እፆች በሚሰጧቸው ድፍረት በጭፈራ ቤቶች ውስጥ የሚዝናኑ ህፃናትና ወጣቶች ለማይገቡ የወሲብ ግንኙነት እየተጋለጡ መሆኑንም ጥናቱ ገልጿል።
የተመሳሳይ ፆታ የወሲብ ግንኙት (ግብረ ሰዶማዊነት)
ይህ አይነቱ መጤ ባህል ማንኛውም የከተማው ነዋሪ ከሚገምተውና ከሚያስበው በላይ እጅግ እየተስፋፋ መምጣቱን የገለጸው ጥናቱ፤ የደርጊቱ መስፋፋትም በማህበረሰቡ ላይ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን እያስከተለ መምጣቱን ጠቅሷል። በዚህ መጤ ድርጊት ውስጥ የሚሳተፉትም እድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት ተማሪዎች፣ የሁለተኛና ከፍተኛ ተቋማት ተማሪዎች፣ በወሲብ ንግድ ሥራ የተሰማሩ ሰዎች እንዲሁም በማረሚያ ቤት የሚገኙ የህግ ታራሚዎች ከፍተኛውን ቁጥር ይይዛሉ።
ግብረሰዶማዊነት በከተማዋ እጅግ በመስፋፋቱ እና እየተለመደ ከመምጣቱ የተነሳ ከተመሳሳይ ፆታ ጋር በመሄድ በወሲብ ስራ የሚተዳደሩ ሰዎች እየተበራከቱ መሆኑን የድርጊቱ ተሳታፊ የሆኑ ግለሰቦች አስረድተዋል። ይህ አይነቱ ከመደበኛው እና ከተለመደው አይነት ፆታዊ ግንኙነት ወጣ ያለ ተግባር በማህበረሰቡ ላይ ስነ-ልቦናዊና ማኀበራዊ ጫና የሚፈጥር፤ እንዲሁም ተግባሩ ከእምነት፣ ከባህልና ከስነ-ምግባር አንፃር ድጋፍ የሌለው ነው።
ለየት ያሉ ተግባራት የሚፈፀሙባቸው መታሻ /ማሳጅ/ ቤቶች
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በመዲናችን እዚያም እዚህም ብቅ ብቅ ማለት የጀመሩት መታሻ /ማሳጅ/ ቤቶችም የተነሱበትን አላማ ስተው ከኢትዮጵያዊነት ያፈነገጠ ስራ በመስራት ላይ መሆናቸው በዚህ ጥናት ተደርሶበታል። እነዚህ መታሻ ቤቶችም ለመለየት በሚያስቸግር መልኩ መገኛቸው በመኖሪያ ቤቶች አካባቢ እንደሆነ ተደርሶበታል። አብዛኞቹ እንዲህ አይነቱን አስነዋሪ ድርጊቶች የሚፈፅሙ መታሻ ቤቶች የሚገኙት ደረጃቸውን በጠበቁ ትላልቅ የመኖሪያ ቤቶች ውስጥ ሲሆን፤ ሌሎቹ ደግሞ በትላልቅ የንግድ ህንፃዎች ላይ መሆኑ ተገልጿል። ከሁሉም በላይ የሚያስገርመው ደግሞ እነዚህ ቤቶች እንደ ማንኛውም ሥራ ፈቃድ ያላቸውና አንዳንዶቹም 24 ሰዓት የሚሰሩ መሆናቸው ነው። እነዚህ ቤቶች ታዲያ በመታሻ /ማሳጅ/ ስም ያልተገባ ወሲብና ወሲብ ነክ ድርጊቶች እንደሚፈፀምባቸው ተደርሶበታል።
ሱስ አስያዥ እፆች እና አልኮል
በእነዚህ ሱስ አስያዥ እፆች ስር ከተቀመጡት መካከል ዋና ዋናዎቹ ጫት፣ ሲጋራ፣ ሀሺሽ፣ ሺሻ እና ሄሮይን ተጠቃሽ ናቸው። ይህን እፅ እና አልኮል መጠቀም ልማዳዊ ባህል ያደረጉት በተለይ እድሜያቸው 16 እና 17 አመት በታች የሆናቸው ታዳጊ ህፃናት ሲሆኑ፣ እድሜያቸው በ25 እና 30 መካከል የሚገኙ ወጣቶች ደግሞ የማሪዋና ወይም የካናቢስ ተጠቃሚዎች ተገኝተዋል። በጥናቱ ከተሳተፉት ውስጥም 61 በመቶዎቹ የአልኮል መጠጦችን፣ 28.4 በመቶዎቹ ደግሞ አነቃቂ እፆችን ይጠቀማሉ። ከአእምሮ ህመም ጋር በተያያዘም ወደ አማኑኤል ሆስፒታል ከሚሄዱ በሽተኞች አብዛኛው ከአልኮል፣ ጫትና ሺሻ ጋር የተያያዘ መሆኑን መረጃዎች ያመለክታሉ።
ይህን መጤ ተግባር ለማጥናት 2ሺ 529 ሰዎች የተሳተፉ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 1ሺ 535 61በመቶ የአልኮል መጠጥ 717 (28.4%)ቱ ደግሞ የአነቃቂ እፅ ተጠቃሚ ሆነው ተገኝተዋል። በዚህ ችግር ከፍተኛ ተጠቂ የሆኑ እድሜያቸው ከ12 እስከ 14 የሆነ ህፃናት እና ከ15 እስከ 29 ዓመት የሆነ ወጣቶች ናቸው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህም እድሜያቸው ከ29 ዓመት በላይ የሆኑ ሴቶችም የዚህ ሱስ ተጠቂዎች እየሆኑ መጥተዋል። እነዚህ ህፃናትና ወጣቶችም ከታክሲ ተራ አስከባሪ እስከ አስመጪና ላኪ ነጋዴ፣ ከፖሊስ እስከ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን ያሉ ናቸው።
ሱስ አስያዥ እፆችን የሚጠቀሙ ሴቶችና ወጣቶችም በተፈጥሮ እና በሂደት ካዳበሩት ባህሪ ለየት ባለ መልኩ እነርሱነታቸውን በመቀየር በማህበረሰቡ የማይፈለጉ ነውር ባህሪያትን ያሳያሉ። መጠጥ የሚጠቀሙ ወጣቶች ባህሪም ዱለኛነት፣ ተደባዳቢነት፡ አጉራ ዘለልነት እንዲሁም አስገድዶ ደፋሪነት እና ህገ-ወጥ ወሲብ ፈፃሚነት እንዲሁም አዋኪነት ናቸው። በጥናቱ መሰረትም 49 በመቶዎች በቡድን ድብድብ የሚሳተፉ፣ 35.4 በመቶዎቹ በአስገድዶ መድፈር ድርጊቶች ተሳታፊዎች፣ 58.2 በመቶዎቹ በስርቆት ላይ ተሳታፊ፣ 54.2 በመቶዎች አካባቢን በማወክ ስራ ላይ ተሳታፊዎች ናቸው።
ወጣቶችና ሴቶችን ወደ መጤ ባህልና ልማዳዊ ድርጊት
የሚገፋፉ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?
ወጣቶችና ሴቶች ወደ እነዚህ መጤ ባህልና ልማዳዊ ድርጊት ለምን ይገፋፋሉ? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ በተደረገ ጥናትም፣ ራሱን የቻለ ምክንያት ተቀምጧል። ከእነዚህ ምክንያቶች ውስጥም የወጣቶች የስራ ሁኔታ፣ የጓደኞቻቸው ብዛትና ባህሪይ፣ ለኢንተርኔት ያላቸው ቅርበት፣ ለብዙና ሰፊ ባህል ያላቸው ተጋላጭነት የሚሉት በአለም አቀፋዊነት ስር ተጠቃለዋል። ከዚህ በተጨማሪም የመገናኛ ብዙሃን የሚያስተላልፏቸው የሙዚቃ ፊልሞች፣ የታዋቂ ሰዎች ስብእና፣ አለባበስ፣ ባህሪ እና የአኗኗር ዘይቤም ሌላኛው ምክንያት ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በኢንተርኔት፣ በስልክና በቪዲዮ ጨዋታዎችና በሌሎችም የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ የሚተላለፉ የብጥብጥ ፕሮግራሞች፣ የፋሽን፣ የውበትና የተቃራኒ ፆታ ፍቅር ላይ የሚለቀቁ ፅሁፎች እና መረጃዎች ለወጣቶች ወዳልተፈለገ ልማድ መግባት እንደ ምክንያት ተቀምጠዋል።
በየሀገራቱ ያለው የእፅና የአልኮል ነፃ ዝውውርም ለወጣቶችና ሴቶች ወዳልተፈለገ መንገድ መግባት ከፍተኛውን ሚና እንደሚጫወት ነው የጥናቱ ውጤት ያመለከተው። የተባበሩት መንግስታት የአደገኛ እፅ ቁጥጥር ክፍል ባደረገው ጥናት አረጋግጫለሁ እንዳለውም፤ እድሜያቸው ከ15 እስከ 29 አመት ያሉ ወጣቶች ጫት፣ ካናቢስ (ዕፀፋሪስ) እና ተዛማጅ እፆችን በማሰራጨትና በመጠቀም ዋና ተዋናይ ናቸው። በዚህም ሳቢያ ከእፅ ማዘዋወር፣ መጠቀምና ማምረት ጋር በተያያዘ የሚፈፀሙ ወንጀሎች እየተበራከቱ ይገኛሉ። በዚህም መሠረት 45.2 በመቶዎቹ የማህበረሰብ ድረ-ገፅ ተጠቃሚ በመሆናቸው፣ 21.1 በመቶዎቹ ወሲብ ነክ ምስል በመመልከት፣ 28 በመቶዎቹ በሞባይል በመላላክ እና 18 በመቶዎቹ ከኢንተርኔት እንደተመለከቱ ገልፀዋል።
ሌላው እንደምክንያት የተቀመጠው ነገር ቢኖር ኢኮኖሚያዊ ችግር ነው። ይህ ኢኮኖሚያዊ ምክንያትም ደሀ እና ሀብታም ሳይል ሁሉንም የማኀበረሰብ ክፍል ያካትታል። ከባለፀጋ ቤተሰቦች የተገኙ ወጣቶች ወደ እነዚህ ሱሶች የሚገቡት ለመዝናናት እንደሆነም ጥናቱ አመልክቷል። በዚህም መሠረት ብዙ ጊዜ የሚጠቁት አዝናኝ በሚሏቸው እፆችና ደባል ልማዳዊ ድርጊቶች ነው። በአንፃሩ ኢኮኖሚያቸው ዝቅተኛ ከሆነ ቤተሰብ የተገኙ ወጣቶች ወደ እነዚህ ሱሶች የሚገቡት በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት እንደሌላቸው በማሰብ ራሳቸውን ከማህበረሰቡ ለማግለል በመፈለግ እንደሆነ ተቀምጧል። በጥናቱ እንደተረጋገጠውም ከተሳታፊዎቹ 68 በመቶዎቹ በገቢ ምንጭ ማነስ ምክንያት፣ 47.1 በመቶዎቹ ስራ በማጣት፣ 68 በመቶዎቹ ደግሞ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ ለማግኘት ሲሉ ወደ እነዚህ አላስፈላጊ መጤ ልማዳዊ ድርጊቶች ይገባሉ።
በመዲናችን አላስፈላጊ ድርጊቶች መፈፀሚያ ቦታዎች መስፋፋታቸውም ሌላው ምክንያት ነው። በጥናቱ የተሳተፉ ግለሰቦች እንደገለፁትም፤ 31.4 በመቶዎቹ ከጫትና ሺሻ ቤቶች፣ 50.3 በመቶዎቹ በራቁት ጭፈራ ቤቶች፣ 5.9 በመቶዎቹ የፊልም ማሳያ ቤቶች እንዲሁም 5.4 በመቶዎቹ በማሳጅ ቤቶች አማካኝነት ወደ አልባሌ ድርጊት የተገፉ ናቸው።
ሌላው ወጣቶች እና ሴቶችን ወደ መጤ ልማዳዊ ድርጊቶች ይገፋፋል ተብሎ የተቀመጠው ምክንያት ደግሞ ማህበራዊ ምክንያት ነው። በዚህ ምክንያት ውስጥ የተካተቱት የወጣቶች አለመማር፣ ስራ ማጣት፣ የቤተሰብ ቁጥጥር መላላት እና ማህበራዊ መስተጋብር አለመመጣጠን ናቸው። በመሆኑም ወደዚህ አላስፈላጊ ድርጊት ከገቡት ውስጥ 80.1 በመቶ የሚሆኑን ከአቻ ጓደኛ ግፊት፣ 52.5 በመቶዎቹ በቤተሰብ መፍረስ፣ 46.3 በመቶዎቹ በቤተሰብ የእፅና አልኮል ተጠቃሚነት ምክንያት ወደ ተግባሩ ገብተዋል።
(ይህ ጹሑፍ በሰንደቅ ጋዜጣ ታትሞ ለንባብ የበቃ ነው)