በጭፍን ስሜት የመነዳት ልማድ ለስህተት ይዳርጋል::

የዘንድሮ ፖለቲካ፣ ብዙዎች ከሚገምቱት ውጭ፣... በግራ በኩል ሲጠብቁት በቀኝ በኩል የሚነጉደው ለምንድነው? “ግራ መጋባት” ይሉሃል ይሄ ነው። እንዲህ የምንሆነው፣ ሳናስተውል ስለቀረን ወይም ሚዛን ስለጠፋብን ይሆን? እንደዚያ ከሆነ፣ ጥፋቱ የኛ ነው። ግን፣  ሌላውስ ዓለም መች ከግራ መጋባት ዳነ! “ለየትኛውም አገር ቢሆን፣ የዘመኑ ፖለቲካ መላ የለውም’ኮ” ሊባል ይችላል። በእርግጥም፣ ብዙ ሰዎች ከሚጠብቁት ውጭ፣ ዓለማችን ከዳር ዳር እየተናጠች ነው። ግራ መጋባት የተበራከተው፣ በኢትዮጵያውያን ላይ ብቻ አይደለም። ቢሆንም ግን፣ ኢትዮጵያ ላይ በዛ፣ ተደጋገመ፣ ተደራረበ።በተለይ በተለይ፣ ኢትዮጵያን በሚመለከት፣ የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ አቋምና ጉብኝት በፍፁም ድንገተኛ ሊሆንብን አይገባም፡፡ “የአሜሪካ እጅ ረዝሟል፤ ማሳጠር አለብን” ብለው የሚያምኑት ባራክ ኦባማ፤ አሜሪካ በየአገሩ ጣልቃ ገብታ “የግለሰብ መብት አክብሩ፤ የፖለቲካ ምርጫ አካሂዱ፤ የነፃ ገበያ አሰራር አስፋፉ” እያለች ተፅእኖ ማሳረፍ እንደሌለባት ደጋግመው ተናግረዋል። ይሄ፣ ከዋና ዋና የኦባማ መርሆች መካከል አንዱ ነው። ሳይመረጡ በፊትም ሲናገሩት የነበረ፣ ከተመረጡ በኋላም በተግባር የገፉበት የውጭ ግንኙነት መርህ ነው። ከስድስት ዓመት በላይ ካላንቀላፋን በስተቀር፣ የኦባማ አስተሳሰብና አዝማሚያ ገና ድሮ ፍንትው ብሎ ሊታየን ይገባ ነበር። ለምን?

አውሮፓና አሜሪካ “በአለም ዙሪያ የግለሰብ ነፃነትን፣ የፖለቲካ ምርጫዎችንና የነፃ ገበያ አሰራርን የሚያስፋፋ የፖለቲካ ለውጥ ለማምጣት፣ ተፅእኖ ማድረግ ዋጋ የለውም። እንዲያውም ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል” ወደሚል አስተሳሰብ አዘንብለዋል።እንደ አፍሪካ ቀንድ በመሳሰሉ የውጥረት አገራት ውስጥ፣ የተረጋጋ መንግስትና የኢኮኖሚ እድገት ከተገኘ በቂ ነው” ወደሚል ተስፋ ቢስነት እየወረዱ ነው።አውሮፓና አሜሪካ፣ በኢትዮጵያ ለሚካሄድ የፖለቲካ ምርጫ ሲሰጡት የነበረ ትኩረት ምን ያህል እንደቀነሰ በዘንድሮው ምርጫ በግልፅ ታይቶ የለ!!የኢትዮጵያ መንግስት፣ ለአካባቢው አገራት መረጋጋት እስካገዘ ድረስ፣ ከአውሮፓና ከአሜሪካ የወዳጅነት እርዳታ ማግኘቱ የማይቀር ነገር ነው - በዛሬ አለማቀፍ የትርምስና የሽብር ዘመን።ይህንን ማስተዋልና ማገናዘብ ከቻልን፣ የኦባማ ጉብኝት በጭራሽ ድንገተኛ ተዓምር ወይም ዱብዳ አይሆንብንም፡፡

ባራክ ኦባማ፣ ለኢትዮጵያ መንግስት የሚያሳዩት የወዳጅነት አቋም ግን፣ ከዚህም ያለፈ፣ ከዚህም የቀደመ ነው። ገና ሳይመረጡ በፊት የያዙት አቋም ነው።“የአሜሪካ እጅ ረዝሟል፤ ማሳጠር አለብን” ብለው የሚያምኑት ባራክ ኦባማ፤ አሜሪካ በየአገሩ ጣልቃ ገብታ “የግለሰብ መብት አክብሩ፤ የፖለቲካ ምርጫ አካሂዱ፤ የነፃ ገበያ አሰራር አስፋፉ” እያለች ተፅእኖ ማሳረፍ እንደሌለባት ደጋግመው ተናግረዋል። ይሄ፣ ከዋና ዋና የኦባማ መርሆች መካከል አንዱ ነው። ሳይመረጡ በፊትም ሲናገሩት የነበረ፣ ከተመረጡ በኋላም በተግባር የገፉበት የውጭ ግንኙነት መርህ ነው።“ከሁሉም ከሁሉም በፊት፣ የኢኮኖሚ ጉዳይ ይቀድማል” ማለትም የአሜሪካ ድርሻ፣ “የግለሰብ መብት፣ የፖለቲካ ምርጫና ነፃ ገበያ” የሚሉ ቅድመ ሁኔታዎችን ትታ፣ እርዳታ መስጠት ብቻ ይሆናል። ኦባማ ይህንን በተደጋጋሚ ተናግረዋል፤ በተግባርም እየሰሩበት ይሄውና ስድስት አመታት ተቆጥረዋል።ታዲያ፣ ይህንን ሁሉ ሰምተንና አይተን፣ ባራክ ኦባማ በኢትዮጵያ ላይ ምን አይነት አቋም እንደሚከተሉ መገመት ያቅተናል? ቢያንስ ቢያንስ፣ ፖለቲካን እንጀራቸው ወይም ፖለቲካን ሙያቸው ያደረጉ ሰዎች፣ ይህንን መሳት አልነበረባቸውም።ግን ስተውታል፤ በረዥም ርቀት ስተውታል። በቃ፣ የባራክ ኦባማ አቋምና የኢትዮጵያ ጉብኝት፣ ለአገራችን ፖለቲከኞች ግራ የሚያጋባ ድንገተኛ ተዓምር ወይም ዱብዳ ሆኖባቸዋል።በአንድ በኩል፣ ኢህአዴግ፣ በተለመደው የሶሻሊስቶች ፈሊጥ “ኒዮሊበራል” እያለ ከሚያጣጥላት አገር... ካልጠበቀው አቅጣጫ... ከአሜሪካ፣ ለዚያውም ዝነኛው ባራክ ኦባማን የመሰለ አድናቂ ማግኘቱ ያስገርመዋል። 

ያኔ በ2001 ዓ.ም፣ “ባራክ ኦባማ ከተመረጡ፣ በኢህአዴግ ላይ ጫና በማሳረፍ የፖለቲካ ለውጥ እንዲመጣ ይረዱናል” በማለት፣ ኮሚቴ አቋቋመው ቅስቀሳ ሲያካሂዱ የነበሩ የዲያስፖራ ፖለቲከኞችስ? በነሱ ቅስቀሳ ባይሆንም፣ ኦባማ ተመርጠው በፕሬዚዳንትነት ሲሰሩ ስድስት ዓመታት ተቆጥረዋል። ይሄን ሁሉ አመት የኦባማን አስተሳሰብና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሳይገነዘቡ የቆዩ የአገራችን የዲያስፖራ ፖለቲከኞች፣ በኦባማ አቋም ተበሳጭተው ለተቃውሞ ሰልፍ የወጡት አሁን ነው - የኦባማ ጉብኝት፣ ድንገተኛ ክህደት ሆኖባቸው።
ላለፉት ስድስት አመታት፣ ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች፣ የባራክ ኦባማን የውጭ ፖሊሲ ለማወቅ ትንሽ ጥረት ቢያደርጉ ኖሮ፣ ይሄ ሁሉ ግራ መጋባት ባልተፈጠረ ነበር። ለኢህአዴግ፣ ድንገተኛ አድናቆት አይሆንበትም ነበር። ለዳያስፖራ ተቃዋሚዎችም፣ የኦባማ ጉብኝት ድንገተኛ ክህደት ሆኖ ባልታያቸው!

ኢህአዴግና የዲያስፖራ ተቃዋሚዎች ለአመታት ያህል እንዲህ ግራ የተጋቡት ለምንድነው?በእርግጥ፣ ነገሩ ከተፈፀመ በኋላ፤ የጉብኝት ዜናው ከዳርዳር ከተወራ በኋላ… “ነገሩን መሳት አልነበረባችሁም፣ ኦባማ ለኢህአዴግ እንደሚመቹ ማወቅ ነበረባችሁ፤ መገመት ነበረባችሁ” ብሎ መናገር ቀላል ነው። የአገራችን ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ተጨባጭ መረጃን በማገናዘብ፣ ያኔ ድሮ የኦባማ አስተሳሰብንና አዝማሚያን ማወቅ ይችሉ እንደነበር ለማሳየት ነው የፈለግኩት። ለማወቅ ያልቻሉት፣ ነገሩ ከባድ ስለሆነ አይደለም። በጭፍን ስሜት የመነዳት ልማድ ነው እንዲህ ለስህተት የሚዳርጋቸው።

ትኩረት ለሚገባቸው ጉዳዮች ትኩረት እንስጥ::መዘናጋት እና አቅጣጫ መሳት ይቁም::

Minilik Salsawi (ምንሊክ ሳልሳዊ) ለውጥ የሚጠላ ማንኛውም ሰው የለም:; ለውጥ የማይፈልግ ካለ አንድም ከአምባገነን ስርአቶች ይተዳቀለ አሊያም የጥቅሞችን ማግበስበስ የለመደ ስግብግብ የሕዝብ ጠላት ብቻ ነው::በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ያስፈልጋል;ይህ ደግሞ ሳይታለም የተፈታ ነው::በስልጣን ላይ ያለው አመራር አስተዳደሩ ይተበላሸ ስለሆነ ለውጥ ለማምጣት የማይችልበት ደረጃ ላይ ከመድረሱም አልፎ ተኮላሽቷል::ስለዚህ ለውጥ ማምጣት የሚቻለው ይህንን የተኮላሸ አምባገነን ስርአት በማስወገድ አዲስ ስርአት መፍጠር ሲቻል ብቻ ነው::ይህንን የማስወገድ እርምጃ መውሰድ የሚቻለው ደግሞ ትኩረት ለሚሰጣቸው ጉዳዮች ትኩረት ስንሰጥ ብቻ መሆኑን ማወቅ ያስፈልገናል::

እስካሁን ባለው የትግል ሂደት ውስጥ ራሳችን እያገዘፍን ራሳችን እያደባየን ከፍ ስንል እየተንቀባረርን ዝቅ ስንል ደሞ እየተኮማተርን ለአምባገነኡ እድሜ መርዘም ራሳችን አስታውጾ ማድረጋችን መካድ የለብንም::ጥፋቱን ያመነ መፍትሄ ስሌማያጣ ለትግሉ አትኩሮት ሰጥተን ከመታገል ይልቅ እርስ በርስ መጠላለፍ ጆሮ ዳባ ልበስ ማለት ያልበሰሉ ካድሬዎችን ተጠቅመን በስድብ እና በዝርጠጣ ስም በማጥፋት እና በትንኮሳ ላይ መሰማራት የወያኔ አቅጣጫ ማስቀየሻ ስልቶችን ተቀብሎ እንደ ገደል ማሚቶ ማስተጋባት ወያኔን ለመደምሰስ ከተነሱ የለውጥ ሃይሎች ላይ ተቻችሎ አለመቀጠል ወያኔ በሚሰጠ የቤት ስራ ላይ በጋራ ሆነን እየተቀባበልን ማዛጋት እና መዘናጋታችን ትኩርት ለሚገባቸው ጉዳዮች ትኩረት እንዳንሰጥ መንገዱን ቀርቅረን ይዘናል::

ወደ መፍትሄ እና እንደ ሕዝብ የውሳኔ ሰኚነት መስመር ውስጥ ለመግባት አንድነት ሰላም እና ፍቅር መቻቻል መመካከር እና መድማመጥ ይፈለግብናል::በአሁን ወቅት የሚያስፈልገው ምንድነው የሚለውን ማወቅ ያስፈልጋል::ወያኔን ለመደምሰስ ለትግሉ አትኩሮት መስጠት አስፈላጊ ወቅት ላይ ነውን::ለየትኛው ትግል? እያንዳንዳችን ላመንነበት ትግል አስፈላጊዉን ትብብር እና ድጋፍ ማድረግ ከቻልን ከሌሎች ወያኔን ለመደምሰስ ከተሰማሩ ሃይሎች ጋርአብሮ መስራት ባይሆንልን እንኳን በመቻቻል እያለፍን አስፈላጊውን የአቅም መስዋትነታችንን ወደ ተግባር ማሳደግ እችላለን::ሌላው ስድብ ስም ማጥፋተና ዝርጠጣ ሊቆሙ የሚገባቸው የትግል ስልቶች ናቸው::በስድብ ስም በማጥፋት እና በዝርጣጣ ምንም የምናመጣው ለውጥ የለም::ያልበሰሉ ካድሬዎች በባዶ ሜዳ ያወቁ መስሏቸው ሊፈራገጥኡ ይችሉ ይሆናል::እነሱን ተከትለው ደሞ አስመሳዮች ቅጥረኞች አዛኝ ቅቤ አንጓች መስለው ሊዘባርቁ ስለሚችሉ ጥንቃቄ መወሰድ ያለበት ከለውጥ ሃይሎች ጉያ መሆን ይገባዋል::በአሁኑ ወቅት ትኩረት የሚገባቸው ጉዳዮች በለውጥ ሂደቱ ላይ የሚድረጉ ትግሎችን አጠናቅረን በየቦታው የሚደረጉ የትግል ስራዎችን በማቀናጀት ወደፊት ልንገሰግስ ይገባል::ለወያኔ እና ተላላኪዎቹ የቤት ስራ ትኩረት ሳንሰጥ ለለውጥ ትግሉ ስኬት የዜግነት ድርሻችንን ልናበረክት ይገባል::‪#‎ምንሊክሳልሳዊ‬

ለእኛ የሚበጀን በትግላችን ነጻነታችንን ማረጋገጥ እንጂ የኦባማ መግባት እና መውጣት አይደለም::
Minilik Salsawi የባራክ ኦባማ ምስራቅ አፍሪካ ላይ ኬንያን እና ኢትዮጵያን መጎብኘት የሰሞነኛ አዲስ ዜና ሲሆን ባራክ ኦባማ የሃያላኗ አገር መሪ በመሆናቸው የጉዞው ዜና ሰፊ ሽፋን አግኝቶ አለምን እያስተጋባ ይገኛል::ባራክ ኦባማ በርግጥ ከአፍሪካዊ አባት መገኘታቸው እንዲሁም የሃያላኗ አሜሪካ የመጀመሪያው ጥቁር መሪ መሆናቸው ለየት ሊያደርጋቸው የሚችል ቢሆንም የሚከተሉት የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ በተለይ አፍሪካን በተመለከት የሚያራምዱት አቋም አምባገነኖችን ፈልፍሎ ከማበረታታት ውጪ ምንም የፈየደው ነገር የለም::

ኦባማ ወደ ስልጣን ሲመጡ እንደማንኛውም ተወዳዳሪ ለመመረጥ የሚያስችላቸውን ድምጽ ለማግነት አፍሪካን በተመለከተ ቃልኪዳኖችን በማሽጎድጎዳቸው በተለይ ለውጥ ፈላጊ ሃይሎች የሆኑ ኢትዮጵያውያን በአሜሪካ ምድር ለመመረጣቸው ስኬት ጉልህ ሚና ተጫውተዋል::ኦባማ ግን ወደ ስልጣን ወንበሩ ከተዋሃዱ በኋላ የአፍሪካ አምባገነኖችን በነጩ ቤተመንግስታቸው ሰብስበው በከፍተኛ ማበረታታት የአሜሪካንን ጥቅም በልዩ መልኩ በሚጠብቅ ሁኔታ ደም መጣጭ የአፍሪካ አምባገነን መሪዎችን አጓጉል በማሞገስ ለአፍሪካውያን ትልቅ አደጋ የሆኑ ወንጀሎች እንዲሰሩ እና መንግስታዊ ሽብርተኝነት እንዲስፋፋ አድርገዋል::

በርግጥ ምእራባውያን አፍሪካ ውስጥ ለብሄራዊ ጥቅማቸው እንደሚሰሩ የታወቀ ነው:: የሃይል ሚዛንም ባለበት ሆነው ጥቅማቸው እስካልተነካ ድረስ አምባገነኖችን በመደገፍ እንደሚያበረታቱ ሃቅ ነው::ኦባማ የውጪ ፖሊሲያቸው እንደሚያሳየው የአሜሪካን ጥቅሞች እስካልተነኩ ድረስ ማንኛውም አፍሪካዊ መሪ በሃገሩ ውስጥ የሚፈጽመውን የፖለቲካ ግፍ እንደማይመለከታቸው እና ጣልቃ መግባት እንደማይፈልጉ በተለያዩ ጊዜያት አጋጣሚዎችን ተጠቅመው ተናግረዋል::ሕዝቦች በኑሮ ውድነት መግቢያ መውጫ እንዳጡ በርካታ ድሆች ጥቂት በሙስና የከበሩ ቱጃሮች እንዳሉ በገሃድ እየታየ በዋጋ ግሽበት እና በተለያዩ የኢኮኖሚ ውድቀቶች ሃገራት እየሞቱ እያዩ በሃሰት የቁጥር ቁልሎች የኢኮኖሚ እድገት እየታየ እንደሆነ በመጥቀስ ከባልደረቦቻቸው እና ተቋሞቻቸው ጋር እየተቀባበሉ ሲናገሩ ተሰምቷል::ለዚህም በሞት አፋፍ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ አገራችንን ገነት እያደረጉ በመሳል ስህተቶች ሲፈጥሩ ማየት የተለመደ ተግባር ነው::ወታደሮቹን በሽብርተኝነት መዋጋት ሰበብ እየሸተ የሚገነውን ወያኔ መራሹን መንግስት በማቆለጳጰስ መንግስታዊ ሽብርተኝነት ኢትዮጵያን እንዲወር በሩን ከፍተዋል::

ባራክ ኦባማ ለአሜሪካ እና ለአሜሪካውያን ምናልባት ጥሩ መሪ ሊሆኑ ይችሉ ይሆናል::እርሳቸው ወደ ስልጣን ክመጡ በኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት ግድያ እስር እና የሰብአዊ መብት ጥሰት መፈጸሙ እንዲሁም አለምን ያስደመመ እና ያሳዘነ ስደት መከሰቱ እሙን ነው::እርግጥ ነጻነታችንን እና መብታችን የሚያስከብሩልን ኦባማ አይደሉም::እኛ ራሳችን መሆናችንን መዘንጋት የለብንም::የኦባማ የምስራቅ አፍሪካ ጉብኝት ለኛ ምም የሚጠቅመን ነገር የለም::ለሽፋን ጥቂት እስረኞች ቢፈቱ በርካቶች መታሰራቸው እና መገደላቸው ቀጥሏል::ይህንን ልንፈታ የምንችለው በጋራ ቆመን በመታገል በአንድነት ሃይላችንን አጠናክረን የወያኔን ማፊያ መንግስት ስንደመሥ ብቻ እና ብቻ ነው::ምናልባት ኦባማ እንደተለመደው ፍሪደም ኦፍ ምናም የሚል የአንደበት አየር ባየር ንግግሮች ቢናገሩም በዋናነት የሚመለከቱት ግን የሃይል ሚዛኑን እና የሃገራቸውን ጥቅም እንደሆነ ጠንቅቀን ልናውቅ ይገባል::ለኛ የሚበጀን በትግላችን ነጻነታችንን ማረጋገጥ እንጂ የኦባማ መግባት እና መውጣት አይደለም::ድል በሕዝብ ለሕዝብ የሕዝብ ነው::‪#‎ምንሊክሳልሳዊ‬

የሕግ የበላይነት አለመከበሩን ካወቅን የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ወገባችንን አጥብቀን እንታገል::

Minilik Salsawi (ምንሊክ ሳልሳዊ) ፍትህ ካለ ሰላም አለ::ፍትህ ካለ እድገት አለ:;ፍትህ ካለ እስር ቤቶች በንጹሃን አይሞሉም:: ፍትህ ካለ ነጻነት እና መብት አለ:; ፍትህ ካለ የሚሸማቀቅ አይኖርም::ፍትህ ከተረጋገጠ ሕጎች ሁሉ በበላይነት የሕዝብ ይሆናሉ::ይህ ሁሉ የሚረጋገጠው በኛ ለኛ ከኛ ነው::እኛ አዎ እኛ በአሁን ወቅት እና ጊዜ ላይ ቆም ብለን ካሰብን የሚያስፈልገን ነገር ቢኖር በራሳችን ትግል ነጻነታችንን እና መብቶቻችንን ታግለን ማረጋግጥ እንዲሁም አምባገነኖችን ላንዴና ላያዳግም መደምሰስ ነው::

በኢትዮጵያችን የሰብ አዊ መብት ጥሰት የመብቶችና የነጻነቶእ ገፈፋ የፍትህ ድንቁርና መንሰራፋቱን እናውቃለን ደጋግመን ብናወራው ለቀባሪው ጆሮ ፍሰት መፍጠር ካልሆነ በስተቀር ምንም አይፈይድም የሚፈይድልን ነገር ቢኖር እነዚህን እኩይ ተግባራት ታግለን በማስወገድ የሕግ የበላይነትን እና የራሳችንን ነጻነት እና መብት ማስከበር ነው:: አሁን ማወቅ ያለብን ይህንን ብቻ ነው::
ፍትህ ፈላጊ የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ እስከፈለግን ድረስ ማንም ሰው ወይም አካል ከህግ በላይ ሊሆን አይችልም:: ህገ ወጥነትን መታገስም በራሱ ወንጀልን ማበረታታት ነው:: ስለዚህ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ የማድረገ ትግላችን ተጠናክሮ መቀጠል አለበት:;ለሕግ የበላይነት የምናደርገው ትግል በተግባራዊ ስራዎች እና ግንዛቤን ከበፊቱ በበለጠ በመፍጠር ሕዝባዊ ሰቆቃዎችን ለማስቀረት ታላቁን ስኔት ከግብ ለማድረስ ከጀመርነው ጉዞ ማፈግፈግ አያስፈልግም ::ሕዝቡ በሃገሪቱ ላይ የሚካሄደውን እና እየተካሄደ ያለውን የወያኔዎች አምባገነን አገዛዝ የፈጠረውን ጸረ ፍትህ አካሄድ አብጠርጥሮ ያውቃል ::ይህ ማለት ደሞ የለውጥ ሃይሎች የሚጠበቅባቸውን የለውጥ ስራዎች በመስራት ትግሉን ከግብ ለማድረስ አስፈላጊዉን የትግል መንገዶችን በመጠቀም ሕዝብን ከጎን በማሰለፍ ድሉን ማረጋገጥ ይጠበቅብናል::

በሃገራችን የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የምእራባውያንን አሳሳቢ በሚል የታጀበ መግለጫ አሊያም ድጋፍ መጠበቅ ለኛ ምንም አይፈይድም::እና ጠንክረን ከታገልን በአምባገነኖች ጫና ስር የወደቀውን ሕዝባችንን ነጻ ለማውጣት በምንገፋው ትግል ላይ የምናሳየው የትግል ታማኝነት እና ስኬት ምእራባውያንን ራሳቸውን ልንማርክ እና ሳንጠይቃቸው እርዳታውንን ለብሄራዊ ጥቅማቸው ሲሉ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ሳይታለም የተፈታ ነው:: ስለዚህ እኛ ራሳችን በጋራ ሆነን ይህንን አምባገነን ስርአት ለመጣል ወደፊት መገስገስ ያለብን እኛው በኛ ሲሆን የሕግ የበላይነት አለመከበሩን ካወቅን የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ወገባችንን አጥብቀን እንታገል::

በሕወሓት የበላይነት የብአዴንና ኦሕዴድ አስረሽ ምችው - ፈንጠዝያ ባርነት እስከመቼ ?

Minilik Salsawi (ምንሊክ ሳልሳዊ): የቀድሞውን ወታደራዊ ስርኣት ለመጣል የአሁኑን የሽምቅ ሽብራዊ መንግስት ለማንገስ በበረሃ ትግል የተሳተፉት የኢሕኣዴግ ድርጅቶች በሃገሪቱ የትግል ታሪክ ውስጥ ጉልህ ድርሻ አላቸው::በኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ስራትን ለማስፈን እጅ ለእጅ ተያይዘን በጋራ ታግለን ህዝባዊ ነጻነትን እናረጋግጣለን በማለት ጫካ የተደባለቁት ድርጅቶች የትግራይን ህዝብ ነጻ በማውጣት ታላቋን ትግራይን እፈጥራለሁ ያለውን ሕወሓት የትግሉ ስኬት ሲከሽፍበት ኢሕዴንን እና ኦሆዴድን በመንተራስ ተረማምዶ ለስልጣን ከበቃ 24 ድፍን አመታትን አስቆተረ::
በ24 አመት የስልጣን ቆይታው የኢሕዴንን እና የኦሕዴድን የትግል አስታውጾ ላማኮላሸት እና ከታሪክ ሂደት መስመር ለማሳት የተጠቀመባቸው ዘዴዎች እና ወታደራዊውን እና የደህንነቱን ተቋም በአንድ ብሄር በማጠር አባል ድርጅቶቹ እና አባላቱ መላወሻ እንዲያጡ ሲሰራ በአደባባይ ታይቷል::ከአቶ ታምራት ላይኔ የፖለቲካ ጠለፋ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ቁጥራቸው ይህ ነው የማይባሉ የኢሕዴን ታጋዮች እና ካድሬዎች በተለያዩ የወንጀል ልጣፎች ከያሉበት ተጠልፈው ወደ ሞት እስር እና ስደት ተግዘዋል:: የኦህዼድ አባላትንም እንዲሁ በመጥለፍ በፖለቲካዊ የኦነግ ታርጋ በማሰር በመግደል እና በተለያዩ ጥቅማጥቅሞች በማሸት አንደበታቸውን አሽጎታል:: ይህ የሕወሓት ስራ ማንም የሚያውቀው እና ጸሃይ የሞቀው ሃቅ ነው:: ቢተነተን የማያልቀው የሕወሓት የውስጥ እና የውጭ ሽብር የሚጋለጥበት ቀን መድረሱት የብኣዴን እና የኦህዴድ አባላት ተግተው በመስራት ላይ መሆናቸውን ሌሎችንም ካድሬዎች እንዲንቀሳቀሱ አድርጓል::
የኦሮሞ እና የአማራ ህዝቦች ኦሕዴድ እና ብአዴንን የመሰለ አሳፋሪ ድርጅት በታሪካቸው ተጋርጠውባቸው አሊያም ባንዳ ሆነው አስፈጅተዋቸው አያውቁም። በጣሊያን ወረራ ጊዜ ለቅኝ ገዢዎች ያደሩ ባንዶች እንኳን ከዛሬዎቹ ኦሕዴዾችና ብአዴኖች የተሻለ ክብር ነበራቸው። ከዛሬዎቹም በተሻለ የድሮ ባንዶች በጌቶቻቸው ጣሊያኖች የሚሉት ይደመጥ ነበር። ኦሕዴድ እና ብአዴን ግን ራሳቸውን ከባንዳነትም አውርደው ባርነት ደረጃ ላይ የጣሉ ከመሆንም አልፎ ባሪያ ሆነው ተለጎመው በመነዳታቸው የሚደሰቱ ሆዳም ሰዎችን የሰበሰቡ ድርጅቶች ናቸው። ኦሕደዽ እና ብአዴን አለቃቸው ሕወሓት ያዘዘውን በመፈጸም የሚረኩ ጥርቅሞች ናቸው። አጉርሱኝ ሲላቸው ያጎርሳሉ፤ጉረሱ ሲላቸው በደስታና በችኮላ ተስገብግበው ይጎርሳሉ።
የብኣዴን እና የኦህዴድ አመራሮች እና ካድሬዎቻቸው ራሳቸውን ከሕወሓት የበላይነት የማላቀቅ ግዴታ አለባቸው::የሕወሓት የበላይነት ከምን የመጣ ነው? ትግል ከሆነ ሁሉን እኩል ድርሻ ያለውን ትግል በጋር ታግለው ነው ወታደራዊውን ስርኣት ያስወገዱት ለሕወሓት ብቻ ማን ይህን እድል ሰጠው? ሕወሓት ብቻውን አልታገለም ብኣዴንም የራሱ ድርሻ ኦሕዴድም የራሱ ድርሻ አለው:; የአማራውና የኦሮሞው ህዝብ ኢሕዴን/ብኣዴንን አይተው ኦሕዴድን አይተው እንጂ ለሕወሓት ሲሉ የእትዮጵያን መሬት በመምራት አልተባበሩም ስለዚህ የብኣዴን እና የኦሕዴድ አመራሮች እና ካድሬዎች ሊገነዘቡት የሚገባው ጉዳይ ትግሉ ሕወሓት ብቻ የመራው ያደራጀው ያሸነፈው አለመሆን እና የድርጅቶቹም ድርሻ እኩል መሆኑን ነው::
በመከላከያው እና በደህንነቱ ዘርፍ ከፍተኛውን ቦታ በመቆጣጠር ሌላውን የእንጀራ ልጅ ያደረጉት ሕወሓቶች የበረሃውን ዳገት እና ቁልቁለት እነሱ ብቻ የተወጡት አድርገው በማቅረብ የቀሪውን ታጋይ ደም እና ድካም ጥላሸት እየቀቡት ነው::የሕወሓት የበላይነት እንዲያበቃ በመከላከያው እና በደህንነት ተቋማት ውስጥ ያሉ የብኣዴን እና የኦሕዴድ ታጋዮች የራሳቸውን አስታውጾ ሊያበረክቱ ይገባል::የፖለቲካ ባርነት እንዲቆም ትግሉን የማቀጣጠል ሃላፊነት አለባቸው:: ‪#‎ምንሊክሳልሳዊ‬

ለትግል ጽናት ቃላችንን እናጥብቅ::ከጉዳይ ሁሉ ቀዳሚው በራስ መተማመን አንድነትን ማጠንከር በጋራ መቆም ነው፡፡

ቃል ስንገባ በስሜታዊነት አይሁን! ቃል ስንገባ በአድር-ባይነት አይሁን! ቃል ስንገባ ለይስሙላ አይሁን! ቃል ስንገባ በእርግጥ አደርገዋለሁ ወይ? ብለን ከልባችን ጠይቀን፣ በአዎንታዊነት እራሳችንን አሳምነን፣ በቁርጠኝነታችን ተማምነን እንጂ እንደው በሞቅ ሞቅና በሰሞነኛ መንገኝነት ተገፋፍተን እንዳይሆን እንጠንቀቅ፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ቃል የምንገባበትን ጉዳይ ጠንቅቀን እንወቅ፡፡ደጋግመን መፈክር ስላሰገርንና፣ ደጋግመን በቃል ቃል ስለገባን ግባችንን በተግባር እንመታለን ማለት አይደለም፡፡ የምንጓዘው ዓላማችንን አንጥረንና አነጣጥረን መሆን አለበት፡፡ ተግባሩን እንጂ ተደጋጋሚ ወሬውን እንተው፡፡

ለትግል ጽናት በራስ ለመተማመን ቢያንስ በሌሎች መፈራት ሳይሆን መወደድ፣ መጠርጠር ሳይሆን መከበር፤ ይቆይብኛል ብሎ መስጋት ሳይሆን ይሄድብኛል ብሎ መጨነቅ የሚፈጥር መሪ መሆንን ይጠይቃል፡፡ በራስ ለመተማመን ለሁሉም የሀገራችን ችግሮች መፍትሄ ለመስጠት መፍጨርጨር ሳይሆን ሌሎች የሚሰጧቸውን አማራጮች ለማዳመጥ መትጋትም ግድ ይላል።ይህ የሚከሰተው ከአለማወቅ ወይም ግንዛቤ ከማጣት ሊሆን ይችላል፡፡የአገሪቱ አምባገነን ገዢዎች ያሉት ሁሉ ልክ ነው ከሚል የሎሌያዊነት አመለካከት ሊሆን ይችላል፡፡ ጎረቤቴ ካደረገው ልክ ቢሆን ነው ብሎ ከማሰብም ሊሆን ይችላል፡፡ ሆነ ብሎ ስህተትም ቢሆን ልከተለውና ገደል ሲገባ ልየው ከሚል እኩይ ሀሳብም ሊሆን ይችላል፡፡ የድርጅትንም ኢ ዴሞክራሲያዊ አካሄድ ቆም ብሎ መቃኘትም ያስፈልጋል።መንገኝነት ወረተኝነት በራስ አለመተማመንን ይፈጥራል።

አላዋቂ እጅ መውደቅ እርግማን ነው፡፡ ነብሴ በእጅህ ናት ብሎ የአላዋቂ ተገዢ መሆን የከፋ መርገምት ነው፡፡ አንዱ ስላረገው ብቻ ሌላው የሚከተልበት፣ እንደ መንጋ ተከታትሎ የሚነዱበት ሥርዓት በኢትዮጵያ ተንሰራፍቷል፡፡ ቆም ብሎ የምሄድበት መንገድ ትክክል ነወይ? ከተለመደው መንገድ ውጪ ሌላ አማራጭ አጥቼ ነወይ? ማሰብ ያስፈልጋል ። እንደ መንጋ ተከታትሎ የሚነዱበት ሥርዓት በኢትዮጵያ ተንሰራፍቷል፡፡ ለመንገኝነት አስተሳሰብ ወይም ለወረተኝነት አካሄድ ወይም እንደ አዲስ የትግል ስትራቴጂ፣ ዕቅድ፣ መመሪያ፣ ሲወጣ እንደፋሽን መከተልና ሳይመረምሩ መቀበል፣ ከተለመደ ቆይቷል፡፡ ለመጠፋፋት ጊዜ የማይፈጅብን፤ ለመፋቀር ረዥም ዘመን የማይበቃን አያሌ ነን፡፡ ቀድሞም ሆነ ዛሬ እርስ በርስ፣ በፖለቲካ ድርጅትና ድርጅት ውስጥ ያለውን መናቆር፤ ትላንት ገዢዎች ያደርጉ ከነበረው ፍትጊያ ተነስቶ ማየት ቀላል ነው፡፡በኢትዮጵያ ወቅታዊ ምህዳሮች ውስጥ ከጉዳይ ሁሉ ቀዳሚው በፖለቲካም፣ በኢኮኖሚም፤ በማህበራዊም መልኩ በራስ መተማመን አንድነትን ማጥበቅ በጋራ መቆም ነው፡፡ለትግል ጽናት ቃላችንን እናጥብቅ::ከጉዳይ ሁሉ ቀዳሚው በራስ መተማመን አንድነትን ማጠንከር በጋራ መቆም ነው፡፡ ‪#‎ምንሊክሳልሳዊ‬

ከገባን !!! ለትግሉ ስኬት በአንድነት ለመቆም አሁንም ጊዜው አረፈደም:: ምንሊክ ሳልሳዊ‬

የሃይል ሚዛኑ ያጋደለለት የሃይል ሚዛኑ ያላጋደለለት በፕሮፓጋንዳ የተወጠረው በአጉል የፖለቲካ ድቀት የሚዋዥቀው በጡዘት የሚሾረውን ጨምሮ በሰከረው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የማናየው የማንሰማው ጉድ የለም::እኔ አውቅልሃለሁ ካለኔ ታጋይ ላሳር እኔ ካሌለሁ ኢትዮጵያ አበቃላት ወዘተ የሚለውን አካቶ ከተሳዳቢ እና ዘርጣጭ ጥሬ የፖለቲካ ከበሮ ማዜም የማይችለው ሁሉ ተነስቶ ባልዋለበት ኩበቱን ለመልቀም አጓጉል ይንከራተታል::ይህ ሁሉ እርግማን ነው::በራሳችን ችግር ተተብትበት ተይዘን እኛው እጅ መፍትሄው እያለ እኛው በኛው ራሳችንን የምንበላ የምሶሶ አብዮት አፍራሽ ለራሳችን ያልበጀን የማንታረም በሃገር ወዳድ ሽፋን የሃገር እና የሕዝብ በታኝ ሃይሎች ለራሳችን አሊያም ለሌላው ሻማ ሆነን በጋራ አብርተን በጋራ ቀልጠን ለመስዋትነት ያልተዘጋጀን የፖለቲካ ዲስኩራም ብኩኖች ነን::ከገባን !!!

ከጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ጀምሮ እስከ ተመስገን ደሳለኝ ከአንዱአለም አራጌ ጀምሮ እስከ አንዳርጋቸው ጽጌ ከጦማርያኑ እስከ የሃይማኖት ኡስታዞቻችን ድረስ ለሕዝብ መብት እና ነጻነት ትርጉም ያለው ስራ ሲሰሩ እኛ ግን ራሳችን በራሳችን ተሥለን ለመተራረድ የምናቆበቁብ አንዱ ላንዱ የማይተኛ ከተሰዉልን ታጋዮችና እስር ቤት ከታጎሩብን ታላላቅ አስተማሪዎቻችን መማር ያቃተን የራሳችን ጠላቶች ሆነን በትግል ሽሚያ ውስጥ እየዋዥቅን የምንገኝና ልንነቃ ያልቻልን ነን::በዚህ ሂደት ውስጥ ላለማለፍ ስንል ስንቶቻችን ከሰከረው ፖለቲካ እና በጡዘት ከተሞላው የውሸት ፕሮፓጋንዳ እንደራቅን ምስክሮች ነን::በትንሽ ድል የምንወጣጠር በትንሽ ሽንፈት አንገታችንን የምንደፋ መማር ያቃተን በነፈሰበት የምንነፍስ በአንድ ሰሞን ወሬ ሆያሆዬ የምንል እንደ ቆርቆሮ የምንጮህ የንፋስ ፖለቲካ ውላጆች ነንእኛ::ለሃገር እና ለህዝብ የሚበጁ የዳበሩ ሃሳቦችን የይዙ አካላትን እና ግለሰቦችን በማግለል ራሴ ብቻ ልወስን በሚል አባዜ መጠናዎት ስንቱን ገደል ጨምረናል::በቀና የፖለቲካ ሂደት ትራክ ላይ ከመሮጥ ይልቅ በአሻጥርና የግለሰቦች ስም በማጥፋት ስንቱ ታይቷል ታልፏል::ከባለፈው ለምን እንደማንማር እና የመቻቻል እና የመተሳሰብ ባህል አዳብረን እንደማንጓዝ የማይገባን ወደ ገደል ሽምጥ ጋላቢ ሆነናል::

ከባለፈው መማር ከቻልን የመቻቻል እና የመተሳሰብ ቀናነት የተሞላው ሽፍጥ ያልተላበሰ ለአገር እና ለሕዝብ ነጻነት ለመታገል ለራሳችን ቃል ከገባን አንድነታችን የማይጠናከርበት አንዳችም ምክንያት የለም::ከሃሜት ፖለቲካ ከፖለቲካ ምቀኝነት እና ቅናት ወጥተን በጋራ ለትግሉ ስኬት በመመካከር እና በመተማመን ላይ የተመሰረተ አብዮት ካራመድን ለውጥ የማናመጣበት ምንም ምክንያት የለም::እኔ ብቻ አዋቂ ከኔ በላይ ታጋይ ለአሳር ከሚል አጉል መኮፈስ ራሳችንን አውጥተን ከሌላው ጋር በአንድነት መስራት ከቻልን ከትግል ሽሚያ ተላቀን ነገ ትዝብት ላይ ከሚጥለን ፕሮፓጋንዳ ወጥተን በጋራ መስራት ከቻልን ድል የማይገኝበት ምክንያት የለም::ከማግለል እና ከመፈረጅ ከማጣጣል እና ከመርመስመስ መንገኝነት የወረት ፖለቲካ መላቀቅ ግድ ይለናል:: ራሳችን ራሳችንን ልንመክር እና ልናርመው ልናሻሽለውና ልንተቸው ይገባል::ይህ ሁሉ እና ሌሎች የአንድነት እና የመቻቻል መንፈሶች በቀናንት ለአገር እና ለወገን ተደማምረው ለትግሉ ስኬት በአንድነት ለመቆም አሁንም ጊዜው አረፈደም::‪#‎ምንሊክሳልሳዊ‬