ካህናት አዲሱን የሃገረ ስብከት መዋቅር እያማረሩ ነው::--ጎጠኝነትና ሙሰኝነት የሸራረፈው የፓትርያሪኩ መመሪያ

  • ·         የምዕ/አ/አ ሀ/ስብከት ሥ/አስኪያጅ በመመሪያው መሠረት ወደ ሥራቸው አልተመለሱም
  • ·         አቡነ ሕዝቅኤልን በዋ/ሥ/አስኪያጅነት ለማሾም አልያም ባሉበት ለማስቀጠል ታስቧል
  • ·         ፓትርያሪክነቱ ባይሳካ ሥራ አስኪያጅነቱ…?
  • ·         ንቡረ እድ ኤልያስ ፅልመታዊውን የዐመፅ ቡድን በማደራጀት ላይ ናቸው
ሙስናን መከላከልና መዋጋት፣ መልካም ምግባርን ማስፋፋት አገራዊ አጀንዳ በኾነበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ ሙስናን በሁሉም ገጽታዎቹ ለመከላከልና ለመዋጋት፣ መልካም ምግባርን ለማስፋፋት÷ የሥነ ምግባርን አስፈላጊነት በሞራል ልዕልና ማስተማር፣ በተግባርም ከተወገዘው የሙስና ድርጊት ተጠብቆና አርኣያ ኾኖ መገኘት ይገባል፡፡ ይህም ማኅበራዊ ተአማኒነትንና ተቀባይነትን ለመጎናጸፍ፣ ማኅበረሰቡን ለመለወጥ የሚያስችል ጉልበት እንዲኖረን ያደርጋል፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን ካላት ምእመናን ብዛት፣ ሙስናን በአስተሳሰብም በተግባርም ለመከላከልና ለመዋጋት ከሚያስችላት አስተምህሮዋና ካካበተችው ተቀባይነት (supreme teacher of morality) አንጻር ጉልሕ ሚና መጫወት ትችላለች፤ ይገባታልም፡፡
በቤተ ክርስቲያናችን ሙስናን መከላከልና መዋጋት ማለት÷ አገራዊ ሚናችንን ለመቀጠል የምንችልበትን ገጽታና ተቀባይነት መከባከብ ነው፤ ሐዋርያዊ አገልግሎታችንን የምናስፋፋባቸውን መዋቅሮቻችንን ጥንካሬ በዘላቂነት መጠበቅና ማስጠበቅ ነው፤ ቅርሶቻችንን፣ የሰው ኀይል ሀብታችንን፣ የፋይናንስ አቅማችንንና ሌሎች ጥሪቶቻችንን በዐይነትም በመጠንም ለይቶ ዐውቆ ለመቆጣጠር፣ በአግባቡና በቀጣይነት ለመጠቀም መቻል ነው፤ የጎሰኝነትን ነቀርሳና የኑፋቄን ሤራ መከላከልና ማስወገድ ነው፡፡
በጠቅላይ ቤተ ክህነትና በአህጉረ ስብከት የሚስተዋለው ወቅታዊ ኹኔታ ግን ከዚህ የቤተ ክርስቲያናችን ተፈላጊ ሚና ጋራ የሚጣጣም አይደለም፡፡ የቀድሞውን የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የተጧጧፈ የሙስና ገበያ አድርገው የግል ጥቅማቸውን ሲያካብቱ የቆዩት ንቡረ እድ ኤልያስ ኣብርሃ÷ የዘርና የመንደር ቡድን በማደራጀት በኖሩበት የአንጀኝነት ልማድ ሌላ የዐመፅ ቡድን ለማደራጀት እየሠሩ ነው፡፡ በርክበ ካህናት ቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ዋዜማ ‹‹በድጋፍ ፊርማ›› ማሰባሰብ እንቅስቃሴውን የጀመረው ጽልመታዊው የንቡረ እዱ የዐመፅ ቡድን÷ በፓትርያሪኩ ልዩ ጽ/ቤት እና በመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ጽ/ቤት ላይ ያተኮረ ሲኾን ፍላጎቱም የጽ/ቤቶቹን የሥራ ሓላፊዎች በማስወገድ ንቡረ እዱንና መሰሎቻቸውን መተካት፣ የውጭ ግንኙነቱን በበላይ ሓላፊነት መቆጣጠር ነው፡፡
ጽልመታዊው የንቡረ እዱ የዐመፅ ቡድን በቅርቡ በፓትርያሪኩ ልዩ ጽ/ቤት በቋሚ ቅ/ሲኖዶስ ውሳኔ የተመደቡትን ሓላፊ ጨምሮ ሌሎች የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ጽ/ቤት ሓላፊዎች የሚቃወመው ‹‹አላግባብ የተቀመጡ ናቸው›› በሚል ነው፡፡ ድንቄም! ጥያቄው አግባብነት ቢኖረው እንኳ መጀመር ያለበት ከራሳቸው ከንቡረ እዱ ነው፡፡
ከሁሉ በፊት ንቡረ እዱ÷ በቀድሞው አዲስ አበባ ሀ/ስብከት ልዩ ልዩ ጥቅምና ሹመት እያሳዩ ባሳለፏቸው የጥቅም አቀባባዮቻቸው አማካይነት ከገቢያቸው በላይ የግል ሀብት ባካበቱበት የሙስና ተግባር በጥብቅ ሊመረምሩ ይገባል፡፡ ንቡረ እዱ የዐመፅ ቡድን ለማደራጀት ምቹ ኹኔታ የፈጠረላቸው ‹‹የመንፈሳዊ ዘርፍ ምክትል ሥራ አስኪያጅነት›› ሥልጣንም በመዋቅር የሌለ/የማይታወቅ ነው፡፡ እርሱም ይኹን ከተባለ በቦታው ላይ የተቀመጡበት መንገድ በሕገ ቤተ ክርስቲያን ስለ ሥራ አስኪያጅ ሹመት እንደተደነገገው በቋሚ ቅ/ሲኖዶስ ውሳኔ የተደገፈ አይደለም፡፡
እስኪ ይህንንም እንታገሥ ቢባል እንኳ፣ ንቡረ እዱኮ በም/ሥ/አስኪያጅነትና ከዚያም በላይ ለመንበረ ፓትርያሪኩ ቅርብ ኾነው በቆዩባቸው ዓመታት የተቋማዊ ለውጥ አምካኝ እንጂ የለውጡ ደጋፊና አራማጅ እንዳልነበሩ ሌላ ማንም ሳይሆን ዛሬ ባለፈው ድርጊታቸው የሚጸጸቱ ነበር – የጥፋት አጋሮቻቸው የሚመሰክሩት እውነት ነው፡፡ እንዲያውም ዛሬ የመንበረ ፓትርያሪኩን የመዋቅርና አሠራር ለውጥ ለመደገፍ ቆርጠው የተነሡት እኒህ ወገኖች÷ ንቡረ እዱ ‹‹በጠቅላይ ቤተ ክህነት ይኹን በአህጉረ ስብከት ደረጃ ጨርሶ የሓላፊነት ቦታ ሊሰጣቸው አይገባም›› በማለት ይከራከራሉ፡፡ ቅ/ሲኖዶስም ንቡረ እዱ እና እርሳቸውን የመሰሉ ግለሰቦች ጊዜና ወቅት እያዩ በመንበረ ፓትርያሪኩ የሚደላደሉበት አካሄድ ከሥልጣንና ጥቅም ፈላጊነት ባሻገር ልዩ የጥፋት ተልእኮ እንዳለው የተገነዘበ ጥብቅ ርምጃ እንዲወስድባቸው ይጠይቃሉ፡፡
ንቡረ እዱ ራሳቸውን ከተጠያቂነት ለማዳንና ጥቅማቸውን ለመከላከል ከሚያንቀሳቅሱት የጥፋት ቡድን ጋራ በዓላማና አካሄድ የሚመጋገበው ሌላው የሙሰኞችና የጎጠኝነት ቡድን ደግሞ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤልን ‹‹በሥራ አስኪያጅነት ለማሾም ይህም ካልተሳካ በቅ/ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊነት ለማስቀጠልና የደቡብና ምዕራብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ቦታቸውንም ለማስጠበቅ ይሠራል፤›› የሚባለው ቡድን ነው፡፡
ንቡረ እዱ በያዙት የዐመፅ መንገድ ይህኛውም የጎጠኞችና ሙሰኞች ቡድን እስከ አምስት ሺሕ ፊርማዎችን ማሰባሰቡ እየተነገረለት ሲኾን ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል በደቡብና ምዕራብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት÷ በስብከተ ወንጌል ክፍል ሓላፊነት፣ በጋዜጣ አዘጋጅነት፣ በአድባራት (ጎፋ መካነ ሕያዋን ቅ/ገብርኤል፣ ቀድሞ ከርቸሌ የአሁኑ አፍሪካ ኅብረት ቅዱስ ሚካኤል፣ በደብረ ብሥራት ቅ/ገብርኤል) ያለአስተዳደር ጉባኤ ውሳኔ በእልቅና እና ዋና ጸሐፊነት ባስቀጠሯቸው፣ ባዛወሯቸውና ቦታቸውን ባስጠበቁላቸው የአካባቢ ተወላጆች እንደሚመራ ተገልጧል፡፡ ሐራዊ ምንጮች ይህ የአሁኑ የጎጠኞችና ሙሰኞች ቡድን እንቅስቃሴ የሊቀ ጳጳሱ ዕውቅናና ፈቃድ እንዳለበት ባያረጋግጡም አብዛኞቹ የቡድኑ አባላት ግን ብፁዕነታቸውን በፕትርክና ለማስመረጥ እስከ ብር 200,000 መድበው በየሆቴሉና ሬስቶራንቱ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡Ethio Mihdar News on A.A Diosces
ብፁዕነታቸው ላለፉት ሦስት ዓመታት ከቆዩበት የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊነት በተጨማሪ የከፋ ሸካ ቤንች ማጂ፣ የደቡብ እና ምዕራብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከትን በሊቀ ጳጳስነት ይመራሉ፡፡ የቅ/ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊነት÷ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች በተግባር ላይ ስለመዋላቸው ከመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ጽ/ቤትና ጉዳዩ ከሚመለከታቸው አካላት ጋራ በመተባበር ዕለታዊ ክትትልና ቁጥጥር የሚደረግበት፣ ስለአፈጻጸማቸው ሪፖርት የሚቀርብበትና በቋሚ ሲኖዶስ የሚዘጋጁ የመነጋገርያ ርእሰ ጉዳዮችን ለቅ/ሲኖዶሱ ምልአተ ጉባኤ የማቅረብ ሥራ የሚሠራበት ነው፡፡ ከዚህ ከባድ ሓላፊነት ጋራ የአራት አህጉረ ስብከትን አስተዳደር በአስተዳደር ጉባኤ ተገኝቶ በሓላፊነት መምራት፤ ለአህጉረ ስብከቱ አድባራት፣ ገዳማትና የገጠር አብያተ ክርስቲያን በቅርብ ተገኝቶ የሚጠበቀውን አባታዊ ሓላፊነት መወጣት በእጅጉ አዳጋች ነው፡፡
በቀደመው ዘገባችን ለጠቋቆምናቸውና በብፁዕነታቸው አህጉረ ስብከት ለሚታዩት አስተዳደራዊ ችግሮች ይኸው የሓላፊነት መደራረብ የራሱ አስተዋፅኦ እንዳለው አይካድም፡፡ ‹‹የሥራ አለመግባባት›› በሚል ከተገለጸው ችግር በላይ ችግሩ እንዲፈታ የሚሰጡት መመሪያዎች በበላይ ሓላፊዎች ሲሸራረፉ ማየት፣ የመሸራረፋቸው መንሥኤም ያው ጎጠኝነት መኾኑ ሲታይ ደግሞ በእጅጉ ያሳዝናል፡፡ ብፁዕነታቸው የምዕራብ አዲስ አበባ ሀ/ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ ወንድይፍራው÷ ‹‹ከሊቀ ጳጳሱ ትእዛዝ ሳይሰጥና መመሪያ ሳይቀበሉ የሠራተኛ ቅጥር፣ የደመወዝ ጭማሪ፣ ዕድገትና ዝውውር ፈጽመዋል አስፈጽመዋል፤ የተመደቡበትን ሐላፊነት በአግባቡ አልተወጡም፤ ልማት ተዳክሟል፤ አስተዳደር ተበድሏል፤ ባለጉዳይ ተጉላልቷል›› በሚል ከሓላፊነት አገዷቸው፡፡ ለእግዳቸው የሆታ ድጋፍ ለማስገኘት ደግሞ የአድባራት አስተዳዳሪዎችን፣ ጸሐፊዎችን፣ ቁጥጥሮችን፣ ሒሳብ ሹሞችንና ገንዘብ ያዦችን ስብሰባ ጠሩ፡፡
ውዝግቡ ለዘገባ በቅቶ ቁጣዎችን መቅስቀስ ሲጀምር በቀን ብር 200 ውሎ አበል ታስቦላቸው ለስብሰባ የመጡ የ33 አድባራት 5፣ 5 ልኡካን የቃል ማሳሰቢያ ብቻ ተሰጥቷቸው አንዳችም ውይይት ሳያካሂዱ ወደ አጥቢያቸው እንዲመለሱ ተደረገ፡፡ ‹‹በየትኛውም አጥቢያ ቅጥር፣ ዝውውር፣ ዕድገት እንዳይፈጸም፤ ፐርሰንት በአግባቡ ይሰብሰብ›› የሚል የቃል ማሳሰቢያ ብቻ ለመስጠት ከኾነ ስብሰባውን መጥራት ያስፈልግ ነበር? በውሎ አበል የብር33,500 አላስፈላጊ ብክነት!!
የቃል ማሳሰቢያውን የምር እንዳይወሰድ የሚያደርጉ ከፍተኛ የሙስና ተግባራት ተፈጽመዋል፤ እየተፈጸሙም ነው፡፡ የቶታል ሰፈረ ገነት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ሕንጻ ግንባታን አስመልክቶ ከተቋራጭ ጋራ በተፈጸመ ከፍተኛ ሙስና በቀረበባቸው የምእመናን አቤቱታ ማጣራት እንዲካሄድባቸው በመንበረ ፓትርያሪኩ የተወሰነባቸው የደብሩ አስተዳዳሪ አባ ዮናስ መልከ ጸዴቅ ማጣራቱ እስኪጠናቀቅ ድረስ ወደ ጅቡቲ ደ/ፀ/ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የሚያደርጉት የአስተዳዳሪነት ዝውውር ታግዶ ነበር፡፡ ይኹንና ሙስናው ሳይጣራ የአባ ዮናስ ዮናስ ዝውውር ተደርጎ ከዝውውር ጠያቂው አስተዳዳሪ ጋራ ርክክብ መፈጸሙ ነው የተሰማው፡፡
ያለጨረታ ወይም ወጪን የሚቀንሱ አግባቦች ሳይጤኑ ለተቋራጭ ተሰጥቷል በተባለው የሃያ ሚልዮን ብር የሕንጻ ግንባታ ፕሮጀክት ከሊቀ ጳጳሱ ጋራ የዋና ሥራ አስኪያጁም ተባባሪነት እንዳለበት ይጠቀሳል፤ ከእግዱ በተፃራሪ በሁለቱ አስተዳዳሪዎች ዝውውርም እየተወቀሱ ያሉት ዋና ሥራ አስኪያጁም ሊቀ ጳጳሱም ናቸው፡፡ በቀደመው ዘገባችን በጠቀስነው በሀ/ስብከቱ የግራር ደብረ ዐባይ አካባቢ ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን የደብሩን ካህናትና ሠራተኞች ቅጥር ለማጸደቅ 33 ሠራተኞች እያንዳንዳቸው ብር 1000 (በአጠቃላይ ብር 33,000) እንዲያዋጡ በጥብቅ አለቃው ታዝዘዋል፡፡ ጥብቅ አለቃው ለሊቀ ጳጳሱ ቅርበት ያላቸውና ቃለ እግዚአብሔር በዞረበት ሳይዞሩ በእልቅነት እንደተሾሙ ተተችተዋል፡፡
The Patriarchate's letter on Ab Hizkiel and Aba Hiruy row‹‹የተጣለብኝን አደራ በታማኝነትና በቅንነት እየተወጣኹ ነው›› የሚሉት በአቡነ ሕዝቅኤል የታገዱት የሀ/ስብከቱ ዋ/ሥ/አስኪያጅ መልአከ ጽዮን አባ ኅሩይ በበኩላቸው፣ የተመደቡት በቋሚ ቅ/ሲኖዶስ ውሳኔ መኾኑን በማስታወስ የብፁዕነታቸው እግድ ‹‹በሌላቸው ሥልጣንና ሓላፊነት የተላለፈ›› መኾኑን ጠቅሰው ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ አመልክተዋል፡፡ የዋና ሥራ አስኪያጁን ከሓላፊነት መታገድ የተቃወሙ ወገኖችም የእግዱ መነሻ ዋና ሥራ አስኪያጁ ሊቀ ጳጳሱ እያስፋፉት ያለውን ‹‹ሙስናና ዘረኝነት›› መከላከላቸው እንደኾነ በመጥቀስ አቤቱታቸውን ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ አሰምተዋል፡፡ ቅዱስነታቸውም ‹‹ጉዳዩ ይጣራ፤ እስኪጣራ ድረስ ግን አባ ኅሩይ ወደ ሥራ እንዲመለሱ ይደረግ›› በማለት ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በ8/9/2005 ዓ.ም መመሪያ መስጠታቸው ተዘግቧል፡፡
በብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ፊርማ ከጠ/ቤ/ክ/ጽ/ቤት በቁጥር 9531/357/2/05 በቀን 14/9/2005 በአንድ ሳምንት ያህል ዘግይቶ የወጣው ደብዳቤ እንደሚያመለክተው፣ በሊቀ ጳጳሱና በዋና ሥራ አስኪያጁ መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ የሚያጣራ ሦስት አባላት ያሉት ኮሚቴ ተቋቁሟል፡፡ ኮሚቴው ያስፈልጋሉ የተባሉ ዶኩመንቶችን በማሰባሰብ በሁለት ቀናት ውስጥ በሀ/ስብከቱ በመገኘት አጣርቶ ለጠ/ቤ/ክ/ጽ/ቤት ሪፖርት እንዲያቀርብም ታዝዟል፡፡ ይኹንና ቅዱስነታቸው ዋ/ሥ/አስኪያጁ በቋሚ ሲኖዶሱ የተመደቡ መኾኑን በማገናዘብ ጉዳዩ እስኪጣራ ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ የሰጡት መመሪያ ተፈጻሚ አልኾነም፡፡ በዚህም ሳቢያ ዋ/ሥ/አስኪያጁ ማጣራቱ ‹‹ከወገንተኝነት የጸዳ አይደለም›› በሚል ዳግመኛ በጻፉት ደብዳቤ ተቃውመውታል፡፡ በዚህም ሂደቱ ሳይጀመር እግዳት ውስጥ መግባቱ ተሰምቷል፡፡
ዘግይቶም ቢኾን ኮሚቴው ‹‹የሥራ አለመግባባቱን›› አጣርቶ በአጭር ጊዜ ሪፖርት እንዲያቀርብ መታዘዙን በመልካምነት የጠቀሱ ታዛቢዎች ከወገንተኘነት የጸዳ ሪፖርት እንደሚቀርብ ተስፋ ያደርጋሉ፡፡ ይኹንና የቅዱስነታቸው መመሪያ በተሟላ መንገድ እንዲፈጸም ባለመደረጉ ብፁዕ ዋ/ሥ/አስኪያጁን በተዘምዶ መረዳዳት ክፉኛ ይተቿቸዋል፤ ብፁዕ ዋና ጸሐፊውም ቢኾኑ የሀ/ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ምደባ በቋሚ ሲኖዶስ የተወሰነ እንደመኾኑ የተፈጠረው ‹‹የሥራ አለመግባባት›› እንደተጠበቀ ኾኖ የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ የማስከበር ብስለት እንዳልታየባቸው በመጥቀስ ይነቅፏቸዋል፡፡
የኹኔታውን አጠቃላይ ጭብጥ በስፋት ስንመለከት፣ ‹‹የሥራ አለመግባባት›› በሚል የተገለጸው ውዝግብ በተለይ እንደ ብፁዕነታቸው ከአንድ በላይ አህጉረ ስብከትን የመምራት ሓላፊነት በተደራረበባቸው ብፁዓን አባቶች (በጥቂቱ ከዐሥር ያላነሱ) ዘንድ ጎልቶ ይታያል፡፡ ‹‹የሥራ አለመግባባት›› በሚል የተወሰነው ችግር በአሠራር የሚፈታ ኾኖ፣ አህጉረ ስብከትን ደራርቦ መያዙ ጎጠኞችና ሙሰኞች ካላቸው የጥቅመኝነት ትስስርና ትስስሩ ከባዕድ እምነት አስፋፊዎች አሻጥር ጋራ በመመጋገብ የሚፈጥረው ተግዳሮት የሚጋርጠው አደጋ ግን የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ህልውና ጥያቄ ነው የሚኾነው፡፡
ድሬዳዋን ከምዕራብ ሐረርጌ ሀ/ስብከት ጋራ ደርበው በያዙት የብፁዕ አቡነ ዕንባቆም አስተዳደር፣ ‹‹እነ እገሌን (ትውልዳቸው እየተጠቀሰ) ከሀ/ስብከት እናጸዳለን›› በሚል በሊቀ ጳጳሱ ስም የሚነግዱ ጎጠኞች በሠራተኞች ምድባና ዝውውር የሚፈጽሟቸው በደሎችና በቅ/ሲኖዶስ የተወገዙ የፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ ኑፋቄ አራማጅ ማኅበራት ርዝራዦች የሚፈጥሩትን ሁከት፤ የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያን ከምሥራቅ ጎጃም ሀ/ስብከት ጋራ ደርበው የሚመሩት ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ከምእመናን ጋራ የማያባራ ግጭት ውስጥ የገቡበት ቤተሰባዊ አስተዳደርን፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንንና ክርስቲያናዊ ትውፊትን የመፃረር አካሄድ፤ የመ/ፓ/ጠ/ቤ/ክ ዋና ሥራ አስኪያጅነትን ከጋምቤላና ኢሉባቦር አህጉረ ስብከት ሊቀ ጵጵስና ጋራ ደርበው የያዙት ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ለሀ/ስብከታቸው ያላቸው ክትትል አናሳነትና በተለይ በጋምቤላ ሀ/ስብከት የሕገ ወጥ ሰባክያንና ዘማርያንን ስምሪት የሚቃወሙ ቀናዒ ኦርቶዶክሳውያን ለጥቃት መጋለጣቸው፤ መላው አፍሪቃን እንደ አንድ አህጉረ ስብከት የሚመሩት ብፁዕ አቡነ ያዕቆብ አፍቃሬ ካቶሊክ የኾነን ክርስቲያናዊ ምግባር የለሽ ግለሰብ በሀ/ስብከት ዋና ጸሐፊነት በማስቀመጣቸው ምእመናን ያነሡባቸው ጥያቄ፤ በሰሜን አሜሪካ የዋሽንግተን ዲሲና ካሊፎርኒያ አህጉረ ስብከት ሳይገባው በሥራ አስኪያጅነት በመሠየም ከአፅራረ ቤተ ክርስቲያን ጋራ አብሮ በፈበረከው የተጋነነ ሰነድ የቤተ ክርስቲያን አባቶችን የሚያዋርደው የለየለት ፕሮቴስታንት ግለሰብ አወናባጅነት፤ በሰሜን ወሎና ሰቆጣ ሀ/ስብከት ያለከልካይ በአስተዳዳሪው እየተዘረፈ ያለው የደብረ ሮሃ ቅ/ላሊበላ ደብር የቱሪዝም ገንዘብና ከተቆርቋሪ ምእመናን ጩኸት በአንጻሩ እየጠፋ ያለው ቅርስ በምሳሌነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን የምትመራበት ሕግና ቃለ ዐዋዲ ከዘመኑ ሕጎች ጋራ በተዛመደና በተገናዘበ መልኩ ተሻሽሎ እንዲዘጋጅና እንዲቀርብ በጥቅምቱ ምልአተ ጉባኤ ያዘዘው ቅዱስ ሲኖዶስ÷ አስተዳደሩንም በዘመናዊ መልክ ለማዋቀርና ዘመኑን የዋጀ ቀልጣፋ አሠራር ለመዘርጋት፣ በፀረ ሙስናና በልማት፣ በሰላምና በመልካም አስተዳደር ዙሪያ የተጠናከረ ሥራ ለመሥራት ለግንቦት የተሻገረ ቀጠሮ ይዟልና በሳምንቱ አጋማሽ በሚጀመረው የርክበ ካህናት ምልአተ ጉባኤ መደበኛ ስብሰባ ጉዳዩን አጽንዖት ሰጥቶ እንደሚመለከተውና ጠንካራ ውሳኔ እንደሚሰጥበት ተስፋ ይደረጋል፡፡
ማስታወሻ፡- ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል በአባ ኅሩይ ላይ ያሳለፉትን አወዛጋቢ የእግድ ርምጃ መነሻ በማድረግ በዘገባዎቻችን በብፁዕነታቸው አስተዳደር ላይ የተጠቆሙት ውስንነቶች፣ ብፁዕ ሊቀ ጳጳሱ በዋና ጸሐፊነታቸው ዘመን የፈጸሟቸውንና የሚታወቁባቸውን ምስጉን አቋሞች የማንኳሰስ ዓላማ የላቸውም፡፡ በሌላ በኩል፣ የእግዱን ተጨባጭ መነሻዎች ከመጠየቅና በዚያም ዐይን የሙስናውንና የጎጠኝነቱን አስከፊነት ለአብነት በፊት ለፊት ከማሳየት አንጻር በቀረቡት ተከታታይ ዘገባዎች፣ የመልአከ ጽዮን አባ ኅሩይን ይኹን የሌላ ሓላፊ ‹ተክለ ሰብእና› የሚገነቡ መስለው የተቀመጡ አገላለጾች ቢገኙበት ሥራ አስኪያጁ ያለባቸውን ድክመት ለመሸፈን በመጠንቀቅ እንዳልኾነና የዚህም መግፍኤ እንደሌለው ልናሳስብ እንወዳለን፡፡