ቻይናዊያን ኢትዮጵያን ሊያለሟት ወይንስ ቅኝ ሊገዟት…?

ቻይናውያን ለስራ የተንቀሳቀሱባቸውና ጊዜያዊ የመጠለያ ካምፕ ገንብተው የሰፈሩባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች ሁሉ ሰላምና መረጋጋት የላቸውም፡፡ በተለይም የችግሩ ዋነኛ ገፈት ቀማሽ ደግሞ ድሃው ገበሬ ነው፡፡

ከራሳቸው ከዜጎቿ አንደበት ወጥቶ አንደተረጋገጠው ኮምዩኒስቷ ቻይና በዋነኝነት ለኮንስትራክሽን ስራ ወደ አፍሪካ አገሮች በተለይም ወደ ኢትዮጵያ የምትልካቸው ወጣቶች ከአስራ አምስት ዓመት እስከ እድሜ ይፍታሽ እስር የተፈረደባቸው ከባድ ጥፋት የፈፀሙ ወንጀለኞችና ወሮበሎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ድሃዋ አገራችን ኢትዮጵያ ለሀብታሟ ቻይና በእስር ቤትነት እያገለገለች ነው ማለት ነው፡፡

 
 ጣሊያን ቅኝ ሊገዛን በመጣበት ዘመን ለፍርፋሪ ያደሩ የንጉሱ ሹማምንት የሆኑ መኳንት፣ የኃይማኖት፣ የዘመናዊ ትምህርትና የስነ-ጽሁፍ ልሂቃን የፋሽስት ጉዳይ አስፈፃሚና ተላላኪ በመሆን በገዛ አገራቸውና ድሃ ወገናቸው ላይ መቸም ቢሆን ታሪክ የማይረሳው ክህደት ፈፅመዋል፡፡ ከጻኅፍት አፈወርቅ ገ/ኢየሱስንና ብርሃኑ ድንቄን ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

ዛሬም በዚህ ዘመን በተመሳሳይ ሁኔታ የወያኔ ኢህአዴግ ካድሬዎች ከቻይናዊያን ጋር በመመሳጠር የአገራቸውን ብሄራዊ ማንነትና ጥቅም አሳልፈው በገንዘብ በመሸጥና የጎስቋላ ወገናቸውን ሰብአዊ መብት በማስረገጥ ባቋራጭ እየበለጸጉ ይገኛሉ፡፡

ከጎንደር ባህር ዳር ያለው ጎዳና የአስፋልት ግንባታ ሲሰራ በጎንደር ማክሰኝት ከተማ ውስጥ ይገኙ የነበሩት የወያኔ ኢህአዴግ ካድሬዎች ከአካባቢው ህብረተሰብ ሲነፃፀር ያማረና የዘነጠ መኖሪያ ቤት ከመስራት አልፈው ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ በባንክ እስከማከማቸት ደርሰው ነበር፡፡ አንዳንዶቹማ ጭራሽ ሃፍረታቸውን ሽጠው በልተው በአየር ባየር የሲሚንቶ፣ የብረታብረት፣ የድንጋይ፣ የአሸዋና የነዳጅ ንግድ ላይ ተሰማርተው ነበር፡፡ በዚያ ዓይን ያወጣ ስርቆትና ዝርፊያ ጥልፍልፎሽ መረብ ውስጥ የነበሩ ጥቂት የማይባሉ ግለሰቦችም ለጥቅም ሲሉ አርስበርሳቸው በጥይት ተገዳድለዋል፤ በጩቤ ተራርደዋል፡፡ በተጨማሪም የማክሰኝትና አካባቢዋ ህብረተሰብ የዕለት ከዕለት ኑሮ መንገዱ ተገንብቶ እስኪያልቅ ድረስ መረጋጋት ያልሰፈነበትና ስጋት የተጋረጠበት ሆኖ ቆይቷል፡፡

በጎጃም መርጦ ለማርያም አከባቢ የሚገኙ የወያኔ ኢህአዴግ ካድሬዎች ደግሞ ከቻይናዊያን መሃንዲሶች ጋር በስውር በመዋዋል የጥራት ደረጃው በእጅጉ የወረደ የአስፋልት መንገድ አንዲገነባ ሲያደርጉ ስራው በሚመለከተው ኢትዮጵያዊ መሃንዲስ ተደርሶባቸው ኢትዮጵያዊዩ መሃንዲስ ሴራውን በማጋለጥ አስፋልቱን ለማስፈረስ ሞክሮ በካድሬዎቹ ዛቻና ማስፈራሪያ አገሩን ኢትዮጵያን ጥሎ ለመሰደድ በቅቷል፡፡

አሁንም በዚያው በጎጃም አዴት ዙሪያ በኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ቻይናዊያን እሳት በውስጡ በቋጠረ የኤሌክትሪክ ሽቦ አንገቷን አንቀው በማንጠልጠል አንዲትን ሴት ህይወቷን በመቅጠፋቸው የአካባቢ ገበሬ ለተቃውሞ ሲወጣ በካራቴ እየዘረሩ ጨርሰውታል፡፡

ባጠቃላይ ቻይናዊያን ለግንባታ ስራ ተሰማርተው ወንጀል ያልፈፀሙባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሉም፡፡ አሁንም በነቀምቴ ባኮ መንገድ ስራ ሳይት አካባቢ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን የዚሁ እጣ ነው እየደረሰባቸው የሚገኙት፡፡ የአሰላና አካባቢዋ ነዋሪዎችም በተመሳሳይ ችግር ውስጥ ይገኛሉ፡፡ መቼም ጉድ ሳይሰማ መስከረም አይጠባም አንድ ቻይናዊ የገልባጭ መኪና ሾፌር የጫናቸውን ኢትዮጵያዊ የቀን ሰራተኞች ልክ አንደማይጠቅም ቆሻሻ መንገድ ዳር ላይ ገልብጦ እንደደፋቸውም ተሰምቷል፡፡ ቻይናዊያን በኢትዮጵያዊያን ላይ ግፍ የሚፈፅሙት በጥቅማጥቅም ያሰሯቸውን “የመንግስት” ካድሬዎች መከታና ከለላ በማድረግ ነው፡፡ በመሆኑም ምንም አይነት ወንጀል በህብረተሰቡ ላይ ፈፅመው ይከሰሱ ወንወጀላቸው ተድበስብሶ ይቀራል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ህብረተሰቡ ጥቃቱን በራሱ መንገድ እንዳይከላከል በጥቅም ምክንያት ከቻይናዊያን ጋር ባበሩ ፌደራል ፖሊሶችና የአካባቢው ታጣቂ ሚሊሻዎች የሚደርስበትን አፀፋ ይፈራል፡፡ 
ደግነቱ ዘውዱ ታድያ ይህ ሁሉ ልማት ወይንስ ቅኝ ግዛት…?

የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት በመንበረ ፓትርያሪኩ ቅጽር ላይ የተቃውሞ ትዕይንት እያካሄዱ ነው፡፡

 • ፖሊስ የጠቅላይ ቤተ ክህነቱን ዋና ሥራ አስኪያጅ አነጋግሯ
 • ‹‹ከሣሾቼን እንዳታነጋግሩ›› ያሉት አቡነ ጢሞቴዎስ ቋሚ ሲኖዶሱ በጉዳዩ ላይ እንዳይወያይ ማከላከላቸው ተሰምቷል
 • በተቃውሞው የተበሳጩት ሊቀ ጳጳሱ ራሳቸውን ስተው እንደነበር ተጠቁሟል
 • ‹‹አልፈው በመቃብራቸው ላይ መሣቅ እንፈልጋለን›› – የጥላቻው ምሬት
 • ‹‹በተራዘመው መርሐ ግብር ሳቢያ የተጨመረው በጀት ለብክነት እየተዳረገ ነው›› /ደቀ መዛሙርቱ/
 ዛሬ ጠዋት ወደ መንበረ ፓትርያሪክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ያመሩት የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት በመንበረ ፓትርያሪኩ ቅጽር ላይ የተቃውሞ ትዕይንት እያካሄዱ ነው፡፡
ጥቁር የአገልግሎት ቀሚሳቸውንና መጽሐፍ ቅዱስ በመያዝ ወደ መንበረ ፓትርያሪኩ በሰልፍ ያመሩት ደቀ መዛሙርቱ፣ ወደ ቅጽሩ እንዳይዘልቁ በጥበቃ ሓላፊው በታገዱበት ነው የተቃውሞ ትዕይንታቸውን በማካሄድ ላይ ያሉት፡፡
ወደ መንበረ ፓትርያሪኩ ለመግባት የተፈቀደላቸው የደቀ መዛሙርቱ መማክርት መሪዎች/ተወካዮች ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ሓላፊዎች ጋራ እየተነጋገሩ እንዳሉ የተመለከተ ሲኾን ቋሚ ሲኖዶሱም በጉዳዩ ላይ እየመከረበት ስለመኾኑ፣ ‹‹በግቢው ጥበቃ ሓላፊ አቶ ብርሃኔ ኀይሉ ተነግሮናል፤›› ብለዋል፡፡

ሌሎች የመንበረ ፓትርያሪኩ ምንጮች በበኩላቸው፣ የኮሌጁ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ ቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ድረስ በአካል በመሄድ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪክ አቡነ ማትያስን ‹‹ከሣሾቼን እንዳታነጋግሩ›› ብለው በማከላከላቸው ውዝግቡን ያጣራው ኮሚቴ ባቀረበው ሪፖርት ላይ ቋሚ ሲኖዶሱ ያደረገውም ይኹን እያደረገ ያለው ውይይት አለመኖሩን በማረጋገጥ በጥበቃ ሓላፊው የተሰጠውን መረጃና በቀደመው የሐራ ዘተዋሕዶ ዜና የቀረበውን ዘገባ አስተባብለዋል፡፡
 Board members of the college
ይህም ኾኖ ደቀ መዛሙርቱ የአቡነ ጢሞቴዎስ ፈቃድ ፈጻሚና የችግሩ አካል አድርገው የሚጠቅሱት የኮሌጁ ቦርድ፣ በፓትርያሪኩ ተመርቶለታል በተባለው የአጣሪ ኮሚቴ ሪፖርት ላይ ሰኞ ዕለት እንደመከረበትና ከሦስትና አራት የቦርዱ አባላት በቀር የሚበዙቱ የአጣሪ ኮሚቴው የውሳኔ ሐሳቦች በቀረቡበት አኳኋን ተፈጻሚ እንዲኾን መስማማታቸውን አስታውሰዋል፤ ምንጮቹ አያይዘውም ቦርዱ እስከአሁን ጉዳዩን ከማየት የዘገየውም የኮሌጁ ሊቀ ጳጳስ ባላቸው ሓላፊነት መሠረት የሚሰጡትን ውሳኔ መነሻ ለማድረግ ነው ብለው እንደሚገምቱ ገልጸዋል፡፡

‹‹ቅ/ሲኖዶስ ሙስናንና ብልሹ አሠራርን በመግለጫ ብቻ ሳይኾን በተግባርም መቃወም ይገባዋል፤ ኮሌጁ የትምህርት ተቋም እንጂ የንግድ ማእከል አይደለም፤ ኮሌጁ የግለሰቦች ሳይኾን የሕዝብ ነው፤ የምእመናንን ገንዘብ የት አደረሳችኹት? ሕገ መንግሥቱንና ፍትሐ ነገሥቱን ባታከብሩ ለመጽሐፍ ቅዱሱ ተገ!›› በሚሉ ኀይለ ቃሎች ተቃውሟቸውን በማሰማት ላይ የሚገኙት ደቀ መዛሙርቱ፣ ለመንፈቅ ዓመት ያህል ሲያቀርቡ የቆዩዋቸው የትምህርት አመራሩንና አስተዳደሩን የተመለከቱ ጥያቄዎቻቸው በአጣሪ ኮሚቴው የቀረቡትን የመፍትሔ ሐሳቦች ተፈጻሚ በማድረግ እልባት እንዲሰጠው የማስገደጃ ርምጃዎችን በመውሰድ ላይ መኾናቸውን አስታውቀዋል፡፡
የአራዳ ክፍለ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ሐምሌ ፩ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁን ብፁዕ አቡነ ማቴዎስን፣ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የኮሌጁን ውዝግብ ለመፍታት በሚከተለው አካሄድ ላይ እንዳነጋገራቸው ታውቋል፡፡ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ አሳሳቢነትና ከቋሚ ሲኖዶስ በተሰጠ መመሪያ÷ ከጠቅላይ ቤተ ክህነቱ፣ ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴርና ከፖሊስ ተውጣጥቶ የተቋቋመውና አምስት አባላት የሚገኙበት አጣሪ ኮሚቴ ያቀረበው ባለሦስት ነጥብ የመፍትሔ ሐሳብ አለመተግበሩን የጠቀሱት የፖሊስ አዛዡ፣ የደቀ መዛሙርቱ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ መቀጠሉን በማሳሰብ ውዝግቡ አስቸኳይ እልባት እንዲሰጠው ብፁዕነታቸውን መጠየቃቸው ተነግሯል፡፡
ከሐምሌ ፩ ‐ ፭ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም ለመስጠት የታቀደው የመንፈቅ ዓመቱ የማጠቃለያ የፈተና መርሐ ግብር የማስገደጃ ርምጃዎችን መውሰድ የቀጠሉት ደቀ መዛሙርቱ ለፈተናው ላለመቀመጥ በመወሰናቸው እስከ አሁን አልተካሄደም፡፡
ከሐምሌ ፩ ቀን ጀምሮ በደቀ መዛሙርቱ ተከቦ በተያዘው የአስተዳደሩ ሕንጻ፣ የበላይ ሓላፊውን ሊቀ ጳጳስ ጨምሮ ሠራተኞችና መምህራን ለመግባት እንደተከለከሉ መኾናቸው ተገልጧል፡፡ ከበባውና ቁጥጥሩ ደቀ መዛሙርቱ በመንበረ ፓትርያሪክ ቅጽር በተሰለፉበት በዛሬ ዕለትም በኮሌጁ ግቢ እንዲቆዩ በተደረጉ ደቀ መዛሙርት መቀጠሉ ተዘግቧል፡፡
ደቀ መዛሙርቱ የአስተዳደር ሕንጻውን መተላለፊያና መግቢያ በሮች በመክበብና በመዝጋት ሓላፊዎች፣ መምህራንና ሠራተኞች ወደ ቢሮ እንዳይገቡ በማገድ የማስገደጃ ርምጃዎቻቸውን ማጠናከራቸው የወትሮ እልካቸውን ያናረባቸው ሊቀ ጳጳሱ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ በብስጭት ራሳቸውን ስተው ወደ ቤተ ዛታ ሆስፒታል ተወስደው እንደነበር የኮሌጁ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ ‹‹እርሳቸው አልፈው በመቃብራቸው ላይ መሣቅ እንፈልጋለን፤›› እስከማለት የተደረሰበት ከፍተኛ ምሬትም ከደቀ መዛሙርቱ መሰማቱ ተገልጧል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩን ፊት ለፊት ለማነጋገር እንደሚሹ የገለጹት ደቀ መዛሙርቱ፣ በተቃውሞው እንቅስቃሴ ሳቢያ ለአንድ ወር ለተራዘመው የትምህርት መርሐ ግብር ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የፈቀደው የሦስት መቶ ሺሕ ብር ተጨማሪ በጀት፣ ከታቀደለት ዓላማ ውጭ አስተዳደሩ ለውድ የቢሮ የምቾት ዕቃዎች ግዥ እያዋለው በመኾኑ ለብክነት እየተዳረገ እንዳለ አጋልጠዋል፡፡
ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ፣ ሰኔ ፳፱ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ በቀን መደበኛ እና በማታ ተከታታይ መርሐ ግብሮች ያሠለጠናቸውን 202 ደቀ መዛሙርት ባስመረቀበት ወቅት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያሪኩ ለምሩቃኑ ሲናገሩ፡-
‹‹ቤተ ክርስቲያን እናንተ ተከብራችኹ፣ ተሻሽላችኹ እንድትኖሩ አቅም በፈቀደ የምታደርገው ይኖራታል፡፡ እናንተም የምትሰጠውን ሥልጠና አቅም በፈቀደ ልታመሰግኑ ይገባል፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ኮሌጆቹን ማበረታታት፣ ማስፋፋት ይገባታል፡፡ ለእናንተ ያልኾነ፣ ከስብከተ ወንጌል የበለጠ ምን ሥራ አላት?››
ብለዋል፡፡
ቅዱስነትዎ÷ ሐምሌ ፳፪ ቀን እንደሚመረቁ የሚጠበቁት 54 ያህል የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የዓመቱ መደበኛ ዕጩ ተመራቂዎችና ሌሎች የቅድመ ምረቃ ደቀ መዛሙርትም የጠየቁትኮ ‹‹አቅም በፈቀደ›› መጠን ሊደረግ የሚችለውንና የሚገባውን ነው፡፡
 • በሌላቸው የትምህርት ማስረጃ ሳይገባቸው የአስተዳደር ሓላፊነት የያዙ ግለሰቦችን አንሥቶ የሚገባቸው ቦታ መስጠት ከአቅም በላይ አይደለም፡
 • ቤተ ክርስቲያናችን የሌላን ሳይኾን የራስዋን አስተምህሮ ለማስፋፋትና ለማጠናከር ካቋቋመችው የትምህርት ተቋም መናፍቁንና ነገረ ሠሪውን ዘላለም ረድኤትን አስወግዶ ለጥያቄ ማቅረብ ለአንጋፋው ኮሌጅ እቆረቆራለኹ ከሚል አባት የሚጠበቅ አነስተኛው ተግባር ነው፡
 • መምህራኑና ደቀ መዛሙርቱ ስለ ትምህርት አመራሩ ያቀረቧቸው ማስረጃዎችኮ ኮሌጁን የሚያስወቅሱ እንጂ የሚያስመሰግኑ አይደሉም፡፡
 • የኮሌጁ ሊቀ ጳጳስ ለግንባታቸው ብር 350,000  እንዳወጡባቸው የገለጹትን ሁለት የመማርያ ክፍሎችኮ እየተማሩባቸው ያሉት ይዞታቸው በተዳከሙ የመማርያ ክፍሎች ያሉት የኮሌጁ ደቀ መዛሙርት ሳይኾኑ ለአዲሶቹ ክፍሎች ኪራይ የሚከፍሉ ሌሎች ኮሌጆች የሚያስተምሯቸው ተማሪዎች ናቸው፡
 • ደቀ መዛሙርቱም ይላሉ÷ ‹‹የሚመዘበረው ገንዘብስ ቢኾን የሚመጣው እኛ በሰበክነው /በእኛው ጉሮሮ/፣ ካህኑ በቀደሰው አይደለምን?›› ምሩቃኑ በዲግሪ ደረጃ የሚያገኙት ደመወዝ ግን ከ900 በላይ አልጨመረም፡፡ በየዓመቱ ለ10 የኮሌጁ ምሩቃን ይመጣል ሚባለው የውጭ ትምህርት ዕድልም በጎጠኝነትና አድልዎ መጠቃቀሚያ መኾኑ ደቀ መዛሙርቱ የሚያማርሩበት ጉዳይ ነው
 • ቅዱስነትዎ በበዓለ ትንሣኤ በኮሌጁ ተገኝተው ደቀ መዛሙርቱን ‹‹ቢቸግራችኹ እንዳልተቸገራችኹ፣ ቢጠማችኹ እንዳልተጠማችኹ ኹኑ›› ብለው የጥያቄያቸውን ምላሽ በትዕግሥት እንዲጠባበቁ ካሳሰቧቸው ወዲህ እንኳ እነኾ ሁለት ድፍን ወራት ተቆጠሩ፡፡ ነገር ግን፣ በሕገ ቤተ ክርስቲያን የቤተ ክርስቲያኒቱን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በበላይነት ለመከታተልና ለመቆጣጠር ሥልጣን ላላቸው ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጅና ለጽ/ቤታቸው አልታዘዝ ከማለት አልፈው የቋሚ ሲኖዶሱን ውሳኔ በተግባር የሻሩትን አቡነ ጢሞቴዎስን ከሚገባው በላይ ማስታመሙን፣ መከባከቡን መርጠዋል፤ ለምን?
ቅዱስነትዎ÷ በዘመነ ፕትርክናዎ ማለዳ የተባባሰው ውዝግብ አያያዝዎ፣ ከአቡነ ጢሞቴዎስ ጋራ ካለዎት የቆየ ወዳጅነትና በፓትርያሪክ ምርጫው ወቅት ከተጫወቱት ሚና ጋራ በተገናኘ ለብዙ ሐሜት እያጋለጥዎት ነውና ከዚህ በላይ ሳያዘገዩ በአጣሪ ኮሚቴው በቀረቡትና ቅዱስነትዎም በተስማማበት የመፍትሔ ሐሳብ መሠረት እልባት እንዲሰጡት ተጠይቀዋል፡፡

በዋልድባ ገዳም ግፉ እና እንግልቱ እንደቀጠለ ነው፥ አረማውያን የግፍ በትራቸውን በገዳማውያን አባቶች ላይ እየሰነዘሩ ነው!

07/12/2013 by savewaldba
ያለበደላቸው ግፍ እየደረሰባቸው ያሉት አባቶቻችን ረደኤት በረከት ይደርብን አሜን
ያለበደላቸው ግፍ እየደረሰባቸው ያሉት አባቶቻችን ረደኤት በረከት ይደርብን አሜን

ገዳማውያኑ ያለበደላቸው ለምን ይንገላቱ?
ከትናንት በስቲያ በደረሰን ሪፖርት እንደሚያመለክተው ላለፉት ጥቂት ወራቶች ሲደረግ እንደነበረው ታጣቂዎች በመነኮሳቱ ላይ ድብደባ፣ እንግልት፣ ስድብ እና እስራት እየፈጸሙባቸው ይገኛሉ። መንግሥት በዋልድባ ገዳም ላይ የሥኳር ፋብሪካ፣ የወርቅ ማዕድን ማውጫ፣ የፖርክ ይዞታን እከልላለው ብሎ በመነሳት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ካሏት በርካታ ገዳማት በጥንታዊነቱ እና በታሪካዊነቱ የሚታወቀውን የዋልድባ (ዋሊ) ገዳም ለማፍረስ እና ገዳማውያኑን ለማሰደድ አረማውያን ደፋ ቀና ማለት ከጀመሩ ውለው አድረዋል። ይህ ሁሉ ግፍ እና በደል በገዳማውያኑ ላይ ሲደርስ በሰዎች ዘንድ ምንም ጥያቄ እና የመከላከል እርምጃ ባይደረግም ነገር ግን የቤተክርስቲያኒቱ መስራች መድኅኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተለያየ ጊዜ የተለያየ ተዓምራትን እያሳየ በርካታ እንቅፋቶችን ቢፈጥርባቸውም፥ ነገርግን በእምቢተኛነት ተግዳሮቱን እንደቀጠለ ነው፥ ነገር ግን የልብሳቸውን አዳፋነት፣ የሰውነታቸውን ክሳት አይቶ ሳይፈራ ስቃይንና መከራን ያበዛባቸውን አረማዊ እንዳይፈሩ በትንቢተ ኢሳያስ ፶፩ ፥ ፯ ላይ የሰፈረውን ቃል መመልከት በቂ ነው፤ እንዲህ ይላል “ጽድቅን የምታውቁ ሕጌም በልባችሁ ያለ ሕዝብ ሆይ፥ ስሙኝ የሰውን ተግዳሮት አትፍሩ፥ በስድባቸውም አትደንግጡ።” ኢሳ. ፶፩ ፥ ፯


በላፉት ጥቂት ወራቶች ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ መነኮሳት እና መነኮሳይት በግፍ ከገዳማቸው ተባረዋል፣ ተብድበዋል፣ ተግዘዋል ታዲያ ይሄ ሁሉ በደል እና የልብ መደንደን ለምን በገዛ ሃገራቸው እንዲህ አይነት በደል ይፈጸምባቸዋል ብለን ብንጠይቅ፥ መልስ እንኳን መስጠት የማይችሉ ሰዎች እነኝህ ለሃገር እና ለወገን ደከመን ሰለቸን ሳይሉ ቀን ከሌሊት ሥብሃተ እግዚአብሔርን ሳያጓድሉ የሚያደርሱትን አባቶች እና እናቶች እንደ ጠላት በየጊዜው አንድና ሁለት እያሉ ይልቁንም የትግራይ ተወላጅ ያልሆኑትን መነኮሳይት እና መነኮሳት በመደብደብ ማስወጣታቸውን ተያይዘውታል፥ ለዚህም ነው በዚህ ባሳለፍነው ሳምንት ውስጥ አምስት መነኮሳት በአውራጃው ፖሊስ ታጣቂዎች (አንጋቾች) ክፉኛ ተደብድበው ከፊሉ ለእስር ሲዳረጉ ከፊሎቹ ደግሞ ለሆስፒታል መዳረጋቸውን በሰማን ጊዜ ልባችን በሃዘን ቆስሏል። እነዚህ መነኮሳት ተወልደው እትብታቸው በተቀበረበት ምድር ለመኖር የአንድ  ወረዳ ጎጠኛ አስተዳዳሪ ውሳኔ ሲጠየቅ ተመልከቱ፣ ከልጅነት እስከ እውቀታቸው በዚህ ገዳም ኖረው ነገር ግን በወንዛቸው እና በተራራቸው በሚያምኑ ጎጠኞች መከራው እየጸና፣ እንግልቱም እንደቀጠለ ነው። አባቶቻችንም ወደ እግዚአብሔር ያመለክታሉ፣ ታጣቂዎችም ለጊዜውም ቢሆን ድል የቀናቸው ይመስላል ነገር ግን ጠቢቡ እንዳለው “ወ ጊዜ ለኩሉ” ነውና ዛሬ ድል አድራጊ መስለው የታዩት፥ ነገ እጆቻቸውን ወደ አምላክ ዘርግተው እንደሚለምኑ ምንም ጥርጥር የለንም አዎ እርሱም መሃሪ የባሕሪይ ገንዘቡ ነው እና ምሕረቱን አይነፍጋቸውም።
ከጥቂት ቀናት በፊት በታጣቂዎች ድብደባ የደረሰባቸው መነኮሳት መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል
፩/ አባ ገብረማርያም [ክፉኛ ቆስለው እጃቸው ተሰብሮ በህክምና ላይ ይገኛሉ]
፪/ አባ ገብረ ዮሐንስ [ክፉኛ ተደብድበው ወደ ክልልችሁ ሂዱ ተብለው በእስር ላይ ይገኛሉ]
፫/ አባ ገብረ ሥላሴ [ክፉኛ ተደብድበው ወደ ክልልችሁ ሂዱ ተብለው በእስር ላይ ይገኛሉ]
፬/ አባ ገብረ ሚካኤል [ክፉኛ ተደብድበው ወደ ክልልችሁ ሂዱ ተብለው በእስር ላይ ይገኛሉ]
፭/ መናኝ ሠይፈ ገብርኤል [ክፉኛ ተደብድበው ወደ ክልልችሁ ሂዱ ተብለው በእስር ላይ ይገኛሉ]
በጣም የሚያሳዝነው እነኝህ ደቂቀ አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ የእግዚአብሔር ፍጡራን ሃገር እንደሌላቸው “ይሄ ክልላችሁ አይደለም” እየተባሉ ይህን ያህል ዱላ እና ስደት የሚደርስባቸው በእውነት ምን ስላደረጉ ነው? በሰው ላይ አልደረሱ፣ ቀለብ ስፈሩልን፣ ገንዘብ ቁጠሩልን ሳይሉ በበረሃ ተወስነው ለፍቅረ ክርስቶስ እራሳቸውን መስዋዕት አድረገው ለዓለም በጸለዩ እንዲህ አይነት በደል ሲደርስባቸው ማየት እጅጉን ይከብዳል። ንጹህ ህሊና ላለው ሰው፣ ለሚያገናዝብ ሰው በእውነቱ የበደል በደል ነው በገዳማውያኑ ላይ የሚደርሰው፣ ነገር ግን ሳይውል ሳያድር ብድራቱን ያገኙታል፥ እነዚህ አባቶቻችን የሚያመልኩት አምላክ ተዋጊ ነው ስሙም ቅዱስ ነው “እግዚአብሔር ተዋጊ ነው፥ ስሙም እግዚአብሔር ነው” ዘፍጥረት ፲፭ ፥ ፫ ላይ እንደተገለጸው ዛሬ ባለጊዜዎች የመከራ ቀንበር ቢያበዙብንም፣ እጅግ ለመሸከም ቢከብድም ነገር ግን የነገሥታት ንጉሥ ሁልጊዜ የድሆችን ይልቁንም ለክብሩ ዱር ለዱር፣ ፍርክታ ለፍርክታ የተንከራተቱትን ዘወትር ከጽሕረ አርያም ይመለከታል ፍርዱም አይጓደልም፥ ነገር ግን ለሰዎች የዘገየ፣ የማያይ፣ የማይሰማ ሊመስላቸው ይችላል፤ እርሱ ግን እድሜ ለንሰሐ እየሰጣቸው መሆኑን ሊገነዘቡት ይገባል መጽሐፈ ነሕምያም እንዲህ ይላል “አሁንም አምላካችን ሆይ፥ ቃል ኪዳንንና ምሕረትን የምትጠብቅ ታላቅና ኃያል የተፈራኸውም አምላክ ሆይ፥ ከአሦር ነገሥታት ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በእኛና በነገሥታቶቻችን በአለቆቻችንም በካህናቶቻችንም በነቢያቶቻችንም በአባቶቻችንም በሕዝብህ ሁሉ ላይ የደረሰው መከራ ሁሉ በፊትህ ጥቂት መስሎ አይታይህ።” ነሕምያ ፱ ፥ ፴፪
በአጠቃላይ ባለጊዜዎች የሚያደርሱት መከራ እጅግ መራራ ቢሆንም፣ የጣሉብን ቀንበር ከባድ ቢሆንም የእሥራኤል አምላክ ዝም አይልም፣  ዘወትር በድካማችን ይጎበኘናል ጠላቶቻችንም ያፍራሉ፣ በእግራችን ሥርም ይወድቃሉ። የአባቶቻችንን ግፍ እና በደል ቆጥሮ ይዘገያል እንጂ ብድራቱን ሁሉ እንደማይነሳቸው እናውቃለን በእምነት መነጽር ለምንመለከተው ሁልጊዜም እግዚአብሔር ሃያል አምላክ ነው፥ ለማያምኑት ለአረማውያኑ ፌዝና ቧልት ሊመስላቸው ይችላል ፣ በመጨረሻ ግን በግንባራቸው ተደፍተው ወደ ፈጣሪ እንደሚለምኑ እናምናለን።
የደጋጎቹ ቅዱሳን አባቶቻችን አምላክ በረደኤት ቅድስት ቤተክርስቲያንን ያስባት
ያለሃጢያታቸው እና በደላቸው የሚንገላቱትን አባቶቻችንን ድካማቸውን ድካመ ቅዱሳን አድርጎ ይቀበልልን
ወስብሃት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።
Let’s save waldba! together ዋልድባ እንታደግ!

የኢህአዴግ በደሴ ከተማ ቁማር መዘዝ ድብቅ አጀንዳ

ቅርስነታቸውን አጥተው የተገደሉት ሸህ ኑሩ እና የኢህአዴግ አመልካች ጣት!

ኢብን ተይሚያህ አል-ሐበሽይ(ምንሊክ ሳልሳዊ ብሎግ)
የኢቲቪ መስኮት የዘወትር ደንበኛ ሆነው አንድ ሰሞን ክፋኛ ጥላቻን ያተረፉትና እራሳቸውን የቀጥተኛዋ መንገድ ናሙና አድርገው ሲስሉልን የነበሩት ግለሰብ ትላንት ሰኔ 27 ምሽት ባልታወቁ ሰዎች መገደላቸውን መስማታችን ያሳዝናል፡፡ የዚህች ቁማር መዘዝም ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል መገመት አያዳግትም፡፡ ግለሰቡ በኢቲቪ መስኮት ብቅ እያሉ የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ሲያውኩ እና ፊትና ላይ ሲጥሉ የነበሩ ሲሆን በተለይ በደሴ ከተማ ውስጥ አሳዛኝ ተግባሮችን ሲፈፅሙ እንደነበር ዘወትር የፌስቡክ ገፆች የዘገቡት ሐቅ ነው፡፡ በእርግጥ ግለሰቡ ይህች የኢህአዴግ-አህባሽ አመጣሽ ንፋስ ከመንፈሷም በፊት እጅጉን አስቸጋሪና ዑለማዕ የማይወዱ እንደነበሩ አንድ ታላቅ አዛውንት አውግተውኛል፡፡ እኔም “የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ጭቆና በፀረ-ሽብርተኝነት ሽፋን” በተሰኘው መፅሀፌ ውሥጥም አካትቻቸው ነበር፡፡ግለሰቡ በዚህች ሁለት ዓመታት ውሥጥ ንፋሱ አድልቧቸው፣ያሻቸውን ተናግረው፣ያሻቸውን አስደብድበው፣ያሻቸውን አድርገው ፍፃሜያቸው ይህ ሆኗል፡፡
እራሴን ወገቤን ብሎ ሣይናገር
እንዲህ ሆኖ ቀረ የወሎማ ነገር!
እንደተባለው ለወሎ የጭቃ ውስጥ እሾህ ሆነው ገርፈው ለገራፊ ዳርገውታል! ቅሉ ከእርሳቸው ጀርባ መዶሻ እንዳለ ቢገባንም የእርሳቸው ሚስማርነት ግን የደሴዎችን ልብ ያደማ ነበር፡፡ በቀጥታም ይሆን በተዘዋዋሪ በግለሰቡ እውቅናና ትዕዛዝ በርካቶች ተደብድበዋል፣በርካቶች አልቀሰዋል፣ከሚወዷቸው የአላህ ቤቶችም እንዳይደርሱ ተገድደዋል!
ከአማራ ክልል ግዛቶች ውሥጥ ወሎ ላይ የበረታው ግርፊያ መነሻው ሸህ ኑሩ ብቻ ናቸው ብለን ባናምንም እጃቸው እንደነበረበት ግን የወሎየዎቹ እምባና የዘወትር ስሞታ ሁነኛ ማስረጃ ነው፡፡የሐይማኖ አባቶች ታስረዋል፣ተዋክበዋል፣መስጅዶች ተነጥቀዋል፣ ምዕምናኑ በመስጅድ ውሥጥ ሳሉ በፓሊስ ይደበደቡ ዘንድ ሟች ባደረጉት ግብዣ መሳጅዶች በፓሊስ ቤት ጫማ ተደፍረዋል! ኢስላምን የማጥፋት ዘመቻው በተለይ በወሎ ጠርዙን የረገጠበት ምክንያት ነገ በታሪክ የሚመመርና ከሰቆቃው ጀርባ ያሉ አካላትም በህግ መጠየቃቸው የማይቀር ነው፣ በታሪክም መወቀሳቸው አይቀሬ ነው፡፡የዚህ ፅሁፍ ዓላማ ሟችን መውቀስ ባለመሆኑ ወደ ነጥቤ ልለፍ፡፡
የትላንትናው የኢቲቪ ዜና ጠርጥር መጠርጠር አይከፋም ብሎኛል! ግለሰቡን እንደ ሀገራዊ አርበኛና ባለውለታ አድርጎ ማቅረብ አልመሰለኝም የኢቲቪ አለቆች አካሔድ ይልቁንስ ያች ሁለት አመት ስንጨቀጭቃችሁ የነበረው የአክራሪዎች ሽብር በተግባር እየተረጋገጠ ነው የሚል አንድምታን ማስተላለፍ ነው የተፈለገው! የሞቱን ዜና መዘገብ ያስፈለገበት ዋናው ድብቅ አጀንዳ ይህ ነው! ሞታቸውን ለሰማን ሁሉ ካዘንበትም ምክንያቶች አንዱና ዋናው ይህ መሆኑ አልቀረም! የኢህአዴግ አመራሮች በተንኮልና በድራማ አቻ የሚገኝላቸው አይደሉም! ይህች ግድያ ለኢህአዴግ የተመቻቸች ኳስ ናት!
የነዚያ ታሳሪ ፋኖዎች ልፋትና ትጋት ይህ እንዳይሆን ነበር፡፡ መስጅዶቻችን የ እውቀት፣የኢባዳ፣የሙስሊሙ ማህበረሰብ ችግሮች ማቀለያና የሹራ ቦታወች እንዲሆኑ እንጅ የደም አበላ የሚያጥባቸው፣የሙስሊሙ የግፍ እንባ የሚጎርፍባቸው እንዳይሆኑ ነበር፡፡ዛሬ ግን ይሔው መስጅድ አካባቢ ሰው ይገደላል፡፡በግድያው ላይ የህዝበ ሙስሊሙ እጅ እንዳለበት ለማሳበቅና ለመቀሰር በማለምም ኢቲቪ ይህን የመርዶ ዜና ባወጀበት ወቅት ያስተጋባው ሲሆን አዲሱ መጅሊስም ግለሰቡ በአክራሪዎች ነው የተገደሉትና ህብረተሰቡ ይህን ሊሸከም አይገባም የሚል አንድምታ ያለው መግለጫ ሰጥቷል፡፡ጥያቄው እዚህ ላይ ነው! በእርግጥ ህዝበ-ሙስሊሙ የ70 ዓመት አዛውንትን በመግደል መፍትሔ ማግኘት ይቻላል ብሎ ያምናል ወይ? ብለን ስንጠይቅ በፍፁም! የሚል መለስ እናገኛለን! ለምን ካሉ እኔ እንዲህ እላለሁ፡
1. የኢህአዴግ መንግስት ህዝበ ሙስሊሙን በአሸባሪነትና በአክራሪነት እየፈረጀና እየከሰሰ አልፎም የከብት ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ዶክመንተሪዎችን በመድረስ ኢትዮጵያ በአክራሪ ኃይሎች ተፅዕኖና ስጋት ውሥጥ ናት የሚል ክስ ያቀርባል፡፡ህዝበ ሙስሊሙ ደግሞ እኛ አሸባሪ አክራሪ አይደለንም! በሐገራችንም ላይ የኢኮኖሚ፣የዘር፣የፓለቲካ አክራሪነት እንጅ የሐይማኖት አክራሪነት መገለጫዎች የሉም! ፓለቲካ ወለድ የሽብር ተግባር እንጅ ሐይማኖት ወለድ የሽብር ሁከትም የለብንም! ብሎ ከመሞገት አልፎ ሠላማዊ መሆኑን ለማሳየትና ለማስረዳት ጠጠር ያልተወረወረበት፣አቧራ ያልተበተነበት ረጅም የሠላማዊ ትግል ስረዓትን ለኢትዮጵያችን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያኑም ጭምር አስተዋውቀዋል፡፡ የዚህ እልህ አስጨራሽ ረጅም ሠላማዊ ትግል አካሔድ አላማ በመንግስት የሚነሱ ክሶች መሰረተ ቢስ መሆናቸውን በተግባር በማሳየት የኢህአዴግን ክስ እርቃን ማስቀረት ነው፡፡ለዚህም ሲባል ኮሚቴዎቹን እንደ በግ አሳልፎ ከመስጠትም ባሻገር በርካታ ወንድሞቹን በተቀነባበር የኢህአዴግ መራሹ ኦፕሬሽን በሞት ሲያጣ እልሁን ውጦ፣ሀዘኑን በሆዱ አፍኖ ከማንባትና ስሞታ ከማሰማት ውጪ አንዳችም ግብረ-መልስ ለመስጠት የሞከረበት ጊዜ የለም፡፡ታዲያ ይህን ከፍተኛ መሰዋዕትነት የሚጠይቅ ሠላማዊ ትግልን እያደረገ ባለበት ሁኔታ እንዴትስ ከዚህ ግብ በተቃራኒ የሚውል ተግባርን ሊፈፅም ይችላል? በፍፁም! ከላይ በጠቀስኩት ዓላማ ላይ የረገጠ ህዝብ ይህን ተግባር ይፈፅማል ማለት አሳማኝ አይሆንም!
2. የህዝበ ሙስሊሙ ኮሚቴዎችን መገበርን፣የህዝበ ሙስሊሙን መገፋትና የበርካታ ሙስሊም ዜጎችን ህይዎትና ንብረት ዋጋ ያስከፈለው ትግል ዋና ዓላማ ከዚህ የግድያ ተግባር ግብ ጋር የሚጋጭ ነው፡፡ የዚህ ትውልድ ጥያቄ ሙስሊሞችን አንድ የሚያደርግ፣አንዱ በሌላው ላይ እጁን የማይቀስርበት፣መንደር ወለድ ስያሜዎችና ታፔላዎችን መሰረት ያላደረገ እንደ አባትም እንደ እናትም ሆኖ ለሁሉም ቡድንና ጀመዓ ተጠሪ ሊሆን የሚችል፡፡ መወቃቀስን ሳይሆን መመካከርን፣ጣት መቀሳሰርና መነቋቆርን ሳይሆን መቻቻልና መተሳሰብን፣ አሳልፎ መሰጣጠትና አንዱ የአንዱ እንቅፋት መሆን ሳይሆን መዋዋጥና መተናነስን፣በልዩነት ውሥጥ አንድነትን፣በኢስላማዊ ጥላ ስር ሊያቅፍ የሚችል የእኔና የእንትና ብቻ ሣይሆን የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተጠሪ ሊሆን የሚችል መጅሊሳዊ ተቋም ያስፈልገናል፡፡ለዚህም ደግሞ አሁን ያሉት አረሞች ተወግደው ለዚህ ታላቅ ግብ ብቁና ትጉህ የሆኑ አመራሮችን በዴሞክራሲያዊ መንገድ እንምረጥ የሚል ነበር! ነውም! ይህን ሁሉ ዋጋ የጠየቀው ግብ! ታዲያ ይህን ትልቅ አጀንዳ (Big Picture) ይዞ የወጣ ህዝብን አንድ ግለሰብን ለዚያውም እዚህ ግባ የማይባል ትርጉም ያለውን ሠው በመግደል ሊጠረጠር ከቶ ይቻላል!
3. በእርግጥ ግለሰቡን በመግደል የህዝበ-ሙስሊሙን የመብት ትግል ምዕራፍና ጉዞ ትቂትም ቢሆን ማንፏቀቅ ይቻላልን? በፍፁም ይህ ግለሰብ ሽፈራው ተ/ማርያም፣በረከት ሰምዖን፣ኤልያስ ሬድማን፣የህውኃት ቱባ አመራር ወይም የኢህአዴግ ቁልፍ ሰው አይደለም! በእርግጥ ከላይ የተጠቀሱት ግለሰቦችን እንኳን በመግደል ቂምን መወጣት ይቻል፣እልህን ማስተንፈስ ይቻል እንደሆነ እንጅ ሕዝበ ሙስሊሙ ይዞት የተነሳውን ግብ መምታት ፈፅሞ አይቻልም! ምክንያቱም ህዝበ ሙስሊሙ ይዞት የተነሳውን የመብት ጥያቄ መመለስ የሚቻለው ሥርዓትን ባማስተካከልና በማጽዳት እንጅ ግለሰቦችን በማስወገድ ፈፅሞ ሊሣካ አይችልም! ይህ ትውልድ ደግሞ ይህን በቅጡ የተገነዘበ መሆኑን ከዚህ ረጅም ሠላማዊ ትግል ውጭ ሁነኛ ማስረጃ ማግኘት ከባድ ነው፡፡ እንዲያ ባይሆን ኖሮማ ሽፈራው ተክለማርያም ዳግማዊ ካሣ ምርጫን (አፄ ዩሐንስ 4ኛ) እንዲሆን ባልተፈቀደለት ነበር፡፡ እናም አንድን የ70 ዓመት ሽማግሌ ለዚያውም ከመንደራዊ አንበሳነት ውጭ እንደ ሐገር የጩጯን ያክል የማይመዝን ግለሰብን በማስወገድ ሐገራዊ ግብን መምታት ይቻላል ብሎ የሚታመን አይመስለኝም! ስለዚህም የኢቲቪና የመጅሊስ ጣት ቅሰራ ጉንጭ ከማልፋት ውጭ የወረወርኩት አንካሴ ተመልሶ ለራሴ መዘዝ ያለው ይመስላል!
እናም ሳጠቃልል ህዝበ ሙስሊሙ ይዞት የተነሣውን ዓላማና ፅናት የረገጠ ማንኛውም ሙስሊም ይህን ተግባር ሊፈፅም ይችላል ብሎ ማሰቡ ብዙ የሚዋጥና አሳማኝ አይመስልም! ይልቁንም ከህዝበ ሙስሊሙ ዓላማ ውጭ የተሰለፉ አካላት ለዚህ ወንጀል ቅርብ ናቸው፡፡ እንዴት ካሉኝ
1. መንግስት እጅጉን ደክሞ በበርካታ ዲራማዊ ዶክመንተሪ ፊልሞች ለማሳመን ያልቻለበትን ጉዳይ አጠናክሮና በማስረጃ አስደግፎ ለማቅረብ፣ ይበልጥ ያስረዳልኛል ያለውን መረጃ ከማፈላለግና ከመፍጠር ወደ ኋላ አይልም እናም አንዲም ለፕሮፓጋንዳ ግብዓት ሁለትም እንደ ማስረጃ ለመምዘዝ በዚህ ቁማር ሊገባ የሚችልበት እድል ሰፊ ነው፡፡
2. ግለሰቡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከዞኑ የመንግስት አመራራትና ከደህንነቶች ጋር በነበራቸው ግጭት ተገልብጠው ከህዝበ ሙስሊሙ ጎን ከተሰለፉ ኢህአዴግ ሊደርስበት የሚችለውን የፓለቲካ እና የአካሄድ ኪሳራ ለመከላከል ከወዲሁ የቤት ሥራውን ሊሰራ ይችላል! ምክንያቱም ግለሰቡ ሁነኛ የፕሮፓጋንዳ መሣሪያው ነበሩና!
3. ኢህአዴግ በተለይም ወያኔዎችና የአመለካከት ልጆቻቸው ድርሳናቸው ሲገለጥ በዚህ ዓይነቱ የገድሎ ገዳይ ፍለጋ ቁማር እጅጉን የገዘፈ ታሪክ አላቸው፣የሙሴን፣የኃየሎምን፣የኢሀአፓ ወታቶችን፣የሀውዜን፣በኦነግ ፋይል የተካተቱ ሽብሮችን መመልከቱ ሁነኛ ማስረጃ ነው፡፡
4. እራሳቸውን የዚህች አገር ልዩ ዋስትና አድርገው ከኢህአዴግ ደርብ ጋር ተጣብተው በኢህአዴግ ከለላ ስር እንደ አሜባ ሊራቡ የሚፈልጉት አህባሾችና ጀሌዎቻቸው ጠላቶቻችን ባሏቸውና በኢህአዴግ ክንድ ሊደቁሱት የሚፈልጉትን ህዝብ ላይ ነውር ለመፈለግ እና እራሳቸውን ከዚህ አይነቱ ተግባር የፀዱ የዋሆች አድርገው ለመሣል በዚህች ድራማ ላይ ሊሳተፉ የሚችሉበት ሁኔታ ሰፊ ነው፡፡
እንግዲህ ጊዜ ጥሩ ነው፤መቆየት ደግ ነው ብዙ ያሳያል! በዚህ ግድያ ሁላችንም አዝነናል! ያዘነው አንድም ሙስሊም የማይበደልበትን ሥርዓት ለመፍጠር በሚደረገው ሠላማዊ ትግል ውሥጥ ዓላማውን መረዳት ያቃታቸው፣ትልቁን ግብ (Big Picture) መመልከት ተስኗቸው ወይም መረዳት ያልፈለጉ በጎች ከጅብ መንጋጋ በመግባታቸው ነው፡፡ ስለ ኢስላም እየተጨነቅን ስለታፔላ እንቅልፍ የሚያጡትን፣ስለ ሰብአዊነት እና ስለ ኢትዮጵያች እየለፈፍን ስለ ጎጥ የሚቆዝሙት ከሁለት የወጡ ጎመኖች ስለመሆናቸው ነው የምናዝነው፡፡አላህ የዚህ ዓይነቱን ውድቀት ከማይሰሙ ያድርገን፡፡ሟች አባታችንንም አላህ በእዝነቱ ይመለከታቸው ዘንድ ዱዓችን ነው! ይህ ጊዜ አልፎ ትልቁን ግብ ማሳየት ብንችልና ይቅር ተባብለን አባታችን እያልናቸው ልጆቼ እያሉን በቅርስነታቸው ቢሞቱ ኖሮ ምን ያክል ክብራችን በሆነ ነበር! ግን አልሆነም አላህ የወደደውንና የፈቀደውን አድርጓል!