ቋሚ ሲኖዶስ: አቡነ ጢሞቴዎስ በኮሌጁ መምህራንና ሠራተኞች ላይ ያስተላለፏቸውን ውሳኔዎች ውድቅ አደረገ

ቋሚ ቅ/ሲኖዶስ በዛሬው ዕለት ባካሄደው ሳምንታዊ መደበኛ ስብሰባው÷ ከሥልጣናቸው ተገልለው እንዲቆዩ የተወሰነባቸው ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ፣ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ መምህራንና ሠራተኞችን ከኮሌጁ መኖርያ ቤቶች የማስለቀቅ፣ ደመወዝ የማገድ፣ አዲስ ቅጥር የማካሄድ፣ ከሓላፊነት የማዘዋወርና የማሰናበት ውሳኔዎችንና መመሪያዎችን ውድቅ በማድረግ የዓመቱ የትምህርት መርሐ ግብር ቅድመ ዝግጅት ተጠናክሮ እንዲካሄድ አዘዘ፡፡Teachers of the Holy Trinity Theological College
ቋሚ ሲኖዶሱ ውሳኔውን ያስተላለፈው 11 የኮሌጁ መምህራንና ሠራተኞች ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር መጨረሻ የሊቀ ጳጳሱ ዐምባገነናዊና የግፍ አስተዳደር አስመልክቶ ባቀረቧቸው ባለሰባት ነጥብ ጥያቄዎች ላይ ከተወያየ በኋላ ነው፡፡ በውይይቱ የብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስ አስተዳደር ‹‹አጠቃላይ የሕንጻ ጥገና ለማካሄድ›› በሚል በኮሌጁ የሚኖሩ መምህራንና ሠራተኞች ከነሐሴ ፱ – ፴ ቀን ፳፻፭ ዓ.ም ድረስ የቤቶችን ቁልፍ እንዲያስረክቡ ያስተላለፉት ውሳኔና እስከተጠቀሰው ቀን የማያስረክቡ ደግሞ ደመወዛቸው እንዳይከፈላቸው ለኮሌጁ ፋይናንስ ክፍል የሰጡት ትእዛዝ አግባብነት የሌለው በሚል ውድቅ ተደርጓል፡፡
የአቡነ ጢሞቴዎስን ውሳኔና ትእዛዝ በመቃወም በኮሌጁ ቅጽር በሚገኘው መኖርያ ቤታቸው የሚገኙት መምህራንና ሠራተኞች የነሐሴ ወር ደመወዛቸው የታገደ ከመኾኑም በላይ ከነሐሴ ፴/፳፻፭ ዓ.ም ወዲህ የመብራትና ውኃ አገልግሎት ተቆርጦባቸው ቆይቷል፡፡ እስከ 18 ዓመት ድረስ በመኖርያ ቤቶቹ ለቆዩ መምህራንና ሠራተኞች በሁለት ሳምንት ውስጥ ቁልፍ አስረክበው እንዲለቁ የተላለፈውን ውሳኔ ውድቅ ያደረገው ቋሚ ሲኖዶሱ፣ መምህራኑና ሠራተኞቹ የተቆረጠባቸው የመብራትና ውኃ አገልግሎት እንዲቀጥል፣ የታገደባቸው ደመወዝ እንዲለቀቅላቸውና በቀጣይም በአግባቡ እንዲከፈላቸው፣ የዓመቱ የትምህርት መርሐ ግብር ቅድመ ዝግጅትም ተጠናክሮ እንዲካሄድ አዝዟል፡፡
ቋሚ ቅ/ሲኖዶሱ ውድቅ ያደረጋቸው የአቡነ ጢሞቴዎስ አስተዳደር ሌሎች ውሳኔዎች ውስጥ ሊቀ ጳጳሱ ከሥልጣን እንዲገለሉ ከተወሰነበት ሰኔ/፳፻፭ ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ ለኮሌጁ ቤተ መጻሕፍት ያካሄዷቸውን ቅጥሮች፣ የቤተ መጻሕፍቱን ሓላፊ መ/ር አባ ጌዴዎን ብርሃነ ከሓላፊነት በማግለልና በማሰናበት የወሰዷቸውን ርምጃዎችም እንደሚጨምር ተመልክቷል፡፡ አላደረሳቸውም እንጂ ከመምህራኑም መካከል በጡረታ እንዲገለሉ፣ ወደ ሌሎች ኮሌጆች እንዲዘዋወሩ ያሰቡባቸውም እንደነበሩ ተዘግቧል፡፡
በሌላ በኩል ባለፈው ዓመት ለሰባት ወራት የኮሌጁ ደቀ መዛሙርትና መምህራን በአቡነ ጢሞቴዎስ አስተዳደር ላይ ባነሡት ጥያቄ ላይ በተካሄደው ማጣራት፣ ከቀን መደበኛ መርሐ ግብር ሓላፊነቱ ተነሥቶ ከኮሌጁ እንዲወገድና ስለ ሃይማኖቱ ሕጸጽ እንዲጠየቅ የተወሰነበት ዘላለም ረድኤት÷ ከውሳኔው በተፃራሪ በሊቀ ጳጳሱ ድጋፍ ሲወጣና ሲገባ ከቆየ በኋላ በዚህ ሳምንት ሰኞ ለኮሌጁ አስተዳደር አቅርቦታል በተባለው የመልቀቂያ ደብዳቤ መሠረት ከሓላፊነቱ ተነሥቶ ከኮሌጁ እንደሚሰናበት ተገልጧል፡፡
የኮሌጁ አካዳሚክ ምክትል ዲን የኾኑት መ/ር ፍሥሓ ጽዮን ደመወዝ ከሓላፊነታቸው ተነሥተው በመምህርነት ተወስነው የሚቀጥሉ ሲኾን በእርሳቸው ቦታ ኮሌጁን በመምህርነትና በሬጅስትራርነት ለረጅም ጊዜ ያገለገሉት መ/ር ግርማ ባቱ መመደባቸው ታውቋል፡፡ በትምህርት ደረጃቸውና በማስተማር ብቃታቸው ምስጉን እንደኾኑ የሚነገርላቸው መ/ር ግርማ ባቱ÷ ከዚያው ከቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ በቴዎሎጂ የመጀመሪያ ዲግሪ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በኢትዮጵያ ጥናት ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው፡፡ የዜና/ነገረ አበው (Patrology)፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን (Canon Law) እና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ኮርሶችን በመንፈሳዊ ኮሌጁ የሚያስተምሩት መ/ር ግርማ፣ መንፈሳዊ ኮሌጁ ባለፈው ዓመት በድኅረ ምረቃ  ፕሮግራም የጀመረውንሲስተማቲክ ቴዎሎጂ መርሐ ግብር በመከታተል ላይ እንደሚገኙ ተዘግቧል፡፡
የአባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን ቅዱስ ፍሬምናጦስ ኮሌጅ ምሩቁና የቀድሞው የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ፊልጶስ ልዩ ጸሐፊ የነበሩት መ/ር ያሬድ ክብረት የኮሌጁ አስተዳደር ምክትል ዲን ኾነው እንዲሠሩ በፓትርያርኩና በዋና ሥራ አስኪያጁ ውሳኔ ተመድበዋል፡፡ መ/ር ግርማ ባቱ በትላንትናው ዕለት ከመ/ር ፍሥሓ ጽዮን ጋራ ርክክብ ማድረጋቸው የተገለጸ ሲኾን ምደባው ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ጢሞቴዎስ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ ባቀረቡት መነሻና ፓትርያርኩ ለብፁዕ ዋና ሥራ አስኪያጁ በሰጡት መመሪያ የተካሄደ መኾኑ ተጠቅሷል፡፡ በዛሬው የቋሚ ሲኖዶሱ ስብሰባ የሁለቱም ሓላፊዎች ምደባ አጠያይቋል፡፡
ይኸውም ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ባለፈው ዓመት በቋሚ ሲኖዶስ በተወሰነውና ከቅ/ሲኖዶስ ጽ/ቤት በተሰጠው መመሪያ መሠረት ሰባት አባላት ያሉት ኮሚቴ በማቋቋም ለመንፈሳዊ ኮሌጁ ዋና ዲን፣ አስተዳደር ምክትል ዲንና አካዳሚክ ምክትል ዲን ለመኾን የሚበቁ ሓላፊዎችን እንዲያቀርብ አዝዞ ሳለ ትእዛዙ ባልተፈጸመበትና ሊቀ ጳጳሱም ከሥልጣን ተገልለው እንዲቆዩ በተወሰነበት ኹኔታ የተካሄደ በመኾኑ ነው፡፡ ስለዚህም የአዲሱ አካዳሚክ ዲንና አስተዳደር ዲን ምደባዎች የቋሚ ሲኖዶሱ ቀጣይ እይታና አጽድቆት እንደሚያስፈልጋቸው ተመልክቷል፡፡
ይኸው ምደባ በቀረቡት ሓላፊዎች የቋሚ ሲኖዶሱን አጽድቆት የሚያገኝ ከኾነ÷ መ/ር ግርማ በአካዳሚክ ምክትል ዲን ሓላፊነታቸው የቀን መደበኛ፣ የማታ ተከታታይና የርቀት ትምህርት መርሐ ግብሮችን፣ የጥናትና ምርምር ማእከሉን እንዲሁም የቤተ መጻሕፍቱን አገልግሎት ከኮሌጁ ራእይና ተልእኮ አንጻር አቀናጅቶ መምራት፣ ማሻሻል፣ ማስፋፋትና ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል፡፡ አስተዳደር ምክትል ዲኑ የሚነሡባቸው መሠረታዊ ጥያቄዎች ያሉ ቢኾንም የኮሌጁን የሰው ኃይል፣ ፋይናንስና ንብረት እንዲሁም የደቀ መዛሙርቱን የምግብ ቤት አገልግሎት አቀናጅቶ መምራት፣ መጠበቅና ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ጉዲፈቻ የሰው ልጆች ንግድ ‹‹ከቤተሰቤ ተሰርቄ ነው የተወሰድኩት›› (SEE VIDEO)

ታሪኳ ለማ፣ በጉዲፈቻ አሜሪካ የተወሰደችው ጉብል

‹‹ከቤተሰቤ ተሰርቄ ነው የተወሰድኩት››በአሁን ጊዜ በዓለም ላይ ኢትዮጵያን በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ ከሚያስነሳት ጉዳይ አንዱ ጉዲፈቻ ነው፡፡

በተለያዩ ምክንያቶች አሳዳጊ የሌላቸው ተብለው የሚታሰቡ ኢትዮጵያውያን ሕፃናት ወደ ተለያዩ አገሮች ይሄዳሉ፡፡ ‹‹የተሻለ ሕይወት›› ይኖራቸዋልም በሚል እሳቤ ቤተሰብ ያላቸውን ሕፃናትም ሕገወጥ በሆነ ሰርቆ መስጠት እንዲሁም በደላሎች አማካይነት የሚሠሩ ሥራዎችም እንዳሉበት በርካታ ዘገባዎች ያሳያሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ አንዱ ሲኤንኤን መስከረም 6 ቀን 2006 ዓ.ም. ያወጣው ይህንኑ አስከፊ እውነታ የሚመሰክር ነው፡፡

ታሪኳ ለማ የ19 ዓመት ዕድሜ ያላት ወጣት ናት፡፡ ከዛሬ ሰባት ዓመት በፊት ነበር ከሁለት ታናናሽ እህቶቿ ጋር ትምህርታቸውን በአሜሪካ እንደሚከታተሉና  ትምህርት በማይኖርበት በማንኛውም የዕረፍት ጊዜ ወደ አገራቸው ኢትዮጵያ እየመጡ ቤተሰቦቻቸውን እንደሚያዩ ቃል ተገብቶላቸው እናት አገራቸውን የለቀቁት፡፡ 

ዛሬ ማይኒ የምትኖረው ታሪኳ ለማ የኮሌጅ ተማሪ ስትሆን፣ የሰብአዊ መብት ተከራካሪ የመሆን ህልም አላት፡፡ በጉዲፈቻ ወደ አሜሪካ ተወስደው ስላለፉት የሕይወት ውጣ ውረድ እንደሚከተለው ተርካዋለች፡፡ 

‹‹የተሸጥኩት አሥራ ሦስት ዓመቴ ላይ ነበር፡፡ ከቤተሰቤ ተሰርቄ የተወሰድኩት፡፡ እኔና እህቶቼን  ለትምህርት ወደ አሜሪካ ሊልከን እንደሚገባ አባቴን ያሳመኑት የአባቴ ጓደኞች ነበሩ፡፡ እኤአ በ2006 በተገባልን የሐሰት ቃል ኪዳን ወላጅ አባቴን አሞኝተው እንድንሄድ ተገደድን፡፡ ይህንን የሚያደርጉት የአባቴ ጓደኞች በሙስና እጃቸው የተጨማለቀና አጭበርባሪ የጉዲፈቻ ወኪል ውስጥ የሚሠሩ ነበሩ፡፡ ይህም ተቋም ኢትዮጵያ ውስጥ ይንቀሳቀስ ነበር፡፡ 

‹‹አባቴም ሆነ እኛ ስለ ጉዲፈቻ የምናውቀው ምንም ነገር አልነበረም፡፡ ወላጅ አባታችን የላከን ለትምህርት፣ እኛም ለመማር እንደመጣን ነበር የምናውቀው፡፡ እውነታው ግን የተገላቢጦሹን ሆኖ ነበር ያገኘነው፡፡ ዋሽተውናል፤ የዋሹት ግን እኛን ብቻ ሳይሆን በጉዲፈቻ የወሰዱንን አሳዳጊ ቤተሰቦቻችንን ጭምር ነበር፡፡  ያመጣንላችሁ ወላጆቻቸውን በኤድስ ያጡ ሦስት ሕፃናትን ነው፤ ትልቋ ዘጠኝ ዓመቷ ነው ብለው ነበር ሴራውን ያቀነባበሩት፡፡ ይሁንና እውነታው ግን እኔ የአሥራ ሦስት ዓመት ታዳጊ ነበርኩ፡፡ የቤተሰቤም የበኩር ልጅ ነኝ፡፡ ታናሾቼ የአሥራ አንድና የስድስት ዓመት ዕድሜ ያላቸው ታዳጊዎች ነበሩ፡፡ 

‹‹አዲሶቹ ‹ቤተሰቦቻችን› ስማችንን ቀየሩትና በአፍ መፍቻ ቋንቋችን በአማርኛና በወላይትኛ ማውራት እንደማንችልና ካወራንም ቅጣት እንደሚጠብቀን አስጠነቀቁን፡፡ እናም በስተመጨረሻ አፍ በፈታንበት ቋንቋ መናገር ተሳነን፤ እስከነ አካቴውም ረሳነው፡፡ 

‹‹በጣም ልጅ ነበርኩኝ፡፡ ከዚህ ካለሁበት የእሥር ቤት ሕይወት ጠፍቼ ብወጣ ወደ አገሬ ኢትዮጵያ ተመልሼ የምገባ ይመስለኝ ነበር፡፡ እነኚህ ቀጣፊዎች ከትውልድ አገሬ፣ ከባህሌና ከቤተሰቤ እንደነጠሉኝ ሳስበው ውስጤ በሐዘንና በምሬት ይሞላል፡፡ 

‹‹ከስምንት ወራት በኋላ ከእህቶቼ ተነጥዬ ወደ ሌላ ቤት እንድጓዝ ተደረግኩኝ፡፡ አዲሱ መኖሪያዬ የተደረገው ከአሳዳጊ እናቴ ቤተሰቦች ጋር ነበር፡፡ ያም ወደ መካከለኛው ምዕራብ ነበር፡፡ እህቶቼን ለመጐብኘት የታደልኩት በጣት ለሚቆጠሩ ጊዜያት ነበር፡፡ አሁን ባለሁበት አገር መኖር ይከብዳል፡፡ ከአገሬ ኢትዮጵያና ከእህቶቼ ተነጥያለሁ፡፡ አጋጣሚዎች ክፉ ቢሆኑብኝም እጅ መስጠት አልፈለግኩም፡፡ ያለኝን አቅም ሁሉ አሰባስቤ ከአገር ውጪ በሚደረግ ጉዲፈቻ ምን ዓይነት ብልሹ አሠራርና የሰው ልጆች ንግድ እየተካሄደ መሆኑን  ለዓለም ሕዝብ ለማሳወቅ ወሰንኩ፡፡ 

‹‹ከአገር ውጪ የሚደረግ ጉዲፈቻን የሚያበረታቱ አካላት 151 ሚሊዮን ወላጅ የሌላቸው ታዳጊዎች እንዳሉ ይጠቁማሉ፡፡ ነገር ግን ሁለቱንም ወላጅ ያጡ ሕፃናት 18 ሚሊዮን ብቻ ናቸው፡፡ ቀሪዎቹ ከእናት ወይም ከአባት ጋር የሚኖሩ ናቸው፡፡ ይህንንም ወላጅ የሌለው ብሎ መጥራት እጅግ የሚከብድ ነው፡፡ እኔ ወላጅ አልባ አይደለሁም፡፡ በእርግጥ እናቴ ሞታለች፤ ነገር ግን አባት አለኝ፣ እህቶች ወንድሞች እናም ሌሎች የሚወዱኝና የሚናፍቁኝ ቤተሰቦች አሉኝ፡፡ 

‹‹ውሸቱም  ሆነ ማጭበርበሩ ለገንዘብ መሆኑን ተረድቻለሁ፡፡ ዛሬ ዛሬ ለገንዘብ ሲሉ ወላጅ የሌላቸው ሕፃናት መፍጠር ጀምረዋል፡፡ ለዚህም የገንዘብ ክፍያ አላቸው፡፡ ክፍያውም ከአገር አገር ይለያያል፡፡ ከፍ ዝቅ ይላል፣ ነጭ ሕፃን በጉዲፈቻ ለመውሰድ የሚከፍሉት ክፍያ ከፍ ያለ ነው፡፡ በአንጻሩ ደግሞ የጥቁር ዝቅ ያለ ነው፡፡ ተመልከቱ ምን ያህል አስከፊ ሕይወት እንደሆነ፡፡ 

‹‹ዛሬ ውጣ ውረዶች ጠንካራ አድርገውኛል፡፡ ይህም በሕይወቴ አንድ ጥሩ ነገር እንድሠራ አነሳስቶኛል፡፡ በጉዲፈቻ ዙሪያ የሚሠሩ ተቋማት እየሠሩ ያሉትን ንግድ የሚያጋልጥ መጽሐፍ በመጻፍ ላይ እገኛለሁ፡፡ ወደ አገሬም ለመመለስ የሚበቃኝን ገንዘብ እያጠራቀምኩ ነው፡፡ በቅርቡም ወደ ፍርድ ቤት በመሄድም ትክክለኛ ስሜን ለማግኘት እሞክራለሁ፡፡››

አምባሳደር ቆንጂት ሥነ ጊዮርጊስ -- የ50 አመታት ድንቅ የዲፕሎማቲክ ስራ አለማቀፋዊ ስኬት

‹‹ትናንት መስከረም 2 ቀን 2006 ዓ.ም. ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ከተቀጠርኩ 51 ዓመት ሞላኝ፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በአዲስ አበባ ሲመሠረት የአንድ ዓመት የሥራ ልምድ የነበረኝ ወጣት ዲፕሎማት ነበርኩ፡፡

እ.ኤ.አ. ከግንቦት 22 እስከ 25 1963 በተካሄደው የመጀመርያው የነፃ አገሮች መሪዎችና መንግሥታት ስብሰባ ላይ ተካፋይ ነበርኩ፡፡ ሰላሳ ሁለቱ መሥራች አባቶች የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ቻርተርን ሲፈርሙ ታድሜያለሁ፡፡ በአዳራሹ የነበረውን ስሜት በግልጽ አሁንም አስታውሰዋለሁ፡፡ ተሳታፊዎቹ የነበራቸውን ደስታና የተስፈኝነት ስሜት ባሳያችሁ ደስ ይለኝ ነበር፡፡››

ይህን የተናገሩት አምባሳደር ቆንጂት ሥነ ጊዮርጊስ    ሲሆኑ፣ ታዳሚዎቻቸው ደግሞ በአብዛኛው ከዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ከተለያዩ ኤምባሲዎች፣ የጥናትና ምርምር ተቋማት የተጋበዙ እንግዶችና የስብሰባውን አዘጋጅ ጨምሮ በተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ ትምህርት እየተከታተሉ ያሉ ወጣቶች ነበሩ፡፡ በዕለተ ዓርብ መስከረም 3 ቀን 2006 ዓ.ም. ከ11 ሰዓት ጀምሮ በጎተ ኢንስቲትዩት አዳራሽ በተካሄደው ስብሰባ በአፍሪካ ኅብረትና በተመድ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን የኢትዮጵያ ቋሚ ተወካይና የአፍሪካ ኅብረት ቋሚ ተወካዮች ሰብሳቢ የሆኑት አምባሳደር ቆንጂት፣ “OAU-AU 50 Year Anniversary: Origins, Achievements, Limitations and Future Role” በሚል ርዕስ ለውይይት መነሻ የሆነ ጽሑፍም አቅርበው ነበር፡፡ 

የኢትዮጵያ ሚና
አምባሳደር ቆንጂት በአፍሪካ አንድነት ድርጅት መሥራች ጉባዔ ላይ ከተበተኑት የመሪዎች ንግግሮች ውሰጥ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን፣ የቱኒዚያውን ቤን ቤላንና የታንዛኒያውን ጁሊየስ ኔሬሬን ንግግሮች በከፊል ያነበቡ ሲሆን፣ ለአኅጉራዊው ድርጅት ስኬት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና የቅርብ አለቃቸውና በወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ከተማ ይፍሩ ጉልህ ሚና መጫወታቸውን ገልጸዋል፡፡ 
ኢትዮጵያ በካዛብላንካና በሞንሮቪያ ቡድኖች መካከል የነበረውን ሰፊ ልዩነት ነፃ ሆና በማስታረቋ ብቻ ሳይሆን፣ አኅጉራዊው ድርጅት የተቋቋመለትን ዓላማ እንዲያሳካ ትልቅ አስተዋጽኦ ማድረጓንም አምባሳደር ቆንጂት አስታውሰዋል፡፡ የካዛብላንካ ቡድን እንደ አልጄሪያ፣ ግብፅ፣ ጋናና ሞሮኮ ያሉ አገሮችን ያቀፈና የአፍሪካ ውህደት በፍጥነት እንዲመጣ ይፈልግ የነበረ ቡድን ሲሆን፣ የሞንሮቪያ ቡድን በተቃራኒ እንደ ናይጄሪያና ላይቤሪያ ያሉ አገሮችን ያቀፈ የውህደቱ ጥያቄ በሒደት መምጣት አለበት የሚል ለዘብተኛ ቡድን ነበር፡፡ የኢትዮጵያ አስታራቂነት ሊሳካ የቻለው የሁለቱም ቡድን አባል ባለመሆኗ መሆኑን አምባሳደር ቆንጂት ጠቁመዋል፡፡ 
የአፍሪካ ኅብረት ከግንቦት 2005 ዓ.ም. እስከ ግንቦት 2006 ዓ.ም. ያለው አንድ ዓመት በሙሉ በተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች እንደሚከበር በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ድላሚኒ ዙማ ከተገለጸ ወራት ቢያስቆጥሩም፣ በኅብረቱ መቀመጫ አዲስ አበባ ከዚህ የበዓል ስሜትና መንፈስ ጋር የተገናኘ ዝግጅት አልተደረገም፡፡ አምባሳደር ቆንጂት ይህን ስሜት ለመፍጠርና የኅብረቱ አጀንዳ የዜጎች አጀንዳና ትኩረት እንዲሆን ለማድረግ ኢትዮጵያ ትልቅ ሚና ልትጫወት እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ በትምህርት ተቋማት የሚደረጉ መሰል የውይይት መድረኮችም ከዚህ አኳያ ሊበረታቱ እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡ 
ያልተሳካ ኅብረት?
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት 25ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን ሲያከብር አቶ አማረ ተክሌ “The Organization of African Unity at Twenty Five Years: Retrospect acd Prospect” በተሰኘ ሥራቸው ድርጅቱ ለአፍሪካ ሸክም እንደሆነና ለአኅጉሪቱ የውርደት መገለጫ ተደርጎ በብዙዎች እንደሚቆጠር ገልጸው ነበር፡፡ ‹‹ድርጅቱ ሁልጊዜም በደረሱና በሚታሰቡ ውድቀቶች፣ ስህተቶችና ድክመቶች ይተቻል፡፡ ዛሬ ድርጅቱ በከባድ የራስ መተማመን ቀውስ፣ በተዓማኒነትና በተፈላጊነቱ ላይ ጥያቄ ይነሳበታል፡፡ በአንዳንድ ወገኖች የድርጅቱ ሚና ፍትሐዊ ላልሆኑና ሙሰኛ ለሆኑ መንግሥታት ዕውቅና ከመስጠት ያልዘለለ እንደሆነም ይታመናል፤›› ሲሉም አቶ አማረ ያክላሉ፡፡ 
ከላይ የገለጸውን ዓይነት ትችትና ወቀሳ የአፍሪካ ኅብረት 50ኛ ዓመቱን ሲያከብር መጠኑን ጨምሮ ካልሆነ አሁንም እየቀረበ ይገኛል፡፡ አምባሳደር ቆንጂት ግን ትችቶቹና ወቀሳዎቹ ድርጅቱ የተቋቋመበትን ዓላማ በብዛት ያገናዘቡ እንዳልሆኑ ይከራከራሉ፡፡ ‹‹የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አምስት ዋነኛ ዓላማዎች ነው የነበሩት፡፡ አንደኛው የአንድነትና የወንድምነት ስሜትን መፍጠር ነው፡፡ ሁለተኛው አኅጉራዊ የትብብር ሥርዓትን ማደራጀት ነው፡፡ ሦስተኛው የአባል አገሮችን ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት እንዲሁም ነፃነት መጠበቅ ነው፡፡ አራተኛው ቅኝ ግዛትን ማስወገድ ነው፡፡ አምስተኛው ደግሞ ዓለም አቀፍ ትብብር መፍጠር ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ዋነኛ ዓላማው የሆነውን የነፃነትን ጥያቄ በሚገባ አሳክቷል፡፡ በአኅጉራዊ መድረክነቱም የአባል አገሮችን የጋራ አጀንዳና ትብብር ለማሳካት በርካታ ስኬታማ ሥራዎችን አሳክቷል፤›› ይላሉ፡፡ 
በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አፍሪካ አዳራሽ ውስጥ የሚገኘው በወንድማማቾቹ አሰፋና የማነ ሰርቀብርሃን የተሳለው የመሥራች አባቶች ሥዕል መካከል አንዱ ባዶ ነው፡፡ አምባሳደር ቆንጂት ባዶው ቦታ ላይ ሊቀመጥ የሚገባው ሥዕል የቶጎ መሪ ቢሆንም፣ አገሪቱ በስብሰባው ሰሞን መፈንቅለ መንግሥት ተፈጽሞባት ስለነበር ከምሥረታው ሒደት ውጪ መደረጓን ያስታውሳሉ፡፡ ‹‹የአኅጉሩ መሪ ድርጅት ሰላምና መረጋጋትን ከማስፈን፣ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትና ውህደት ከመፍጠር፣ መልካም አስተዳደር ከማስፈንና ሙስናን ከመዋጋት፣ መፈንቅለ መንግሥትንና የአንድ ሰውን አመራር ከማስወገድ፣ በአገሮች መካከል የሚደረግ ጦርነትንና የእርስ በርስ ጦርነትን ከማስቀረት፣ የኢኮኖሚ መላሸቅንና የብድር ጫናን ከማስወገድ፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚ በዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ተፅዕኖ ሥር እንዳይወድቅ ከመከላከል አኳያ መጠነ ሰፊ ተግዳሮቶች እንደነበሩበት ግልጽ ነው፡፡ ይሁንና የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት ሠራተኞች ባለፉት አምስት አሥርት ዓመታት ነገሮችን ለመቀየር እንዴት ጠንክረው እንደሠሩና ለውጡ አዝጋሚ ቢሆንም ለውጥ ለማምጣት ከፍተኛ ጥረት እንዳደረጉ ልነግራችሁ እወዳለሁ፡፡ የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሉት እንደነበረው ‹‹አፍሪካ እየተነሳች ነው›› ዛሬ፡፡ በኢኮኖሚውም ሆነ በፖለቲካው ዘርፍ በርካታ መሻሻሎች አሉ፤›› ብለዋል
የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን እንዲተካው የተደረገው አንዳንድ ድክመቶቹን ከግምት ውስጥ አስገብቶ እንደነበርም አምባሳደር ቆንጂት ያስረዳሉ፡፡ ‹‹የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ጥሰት በሚፈጽሙ አገሮች የውስጥ ጉዳይ አይገባም ነበር፡፡ ሰፊ የተሳትፎ መሠረት ያልነበረውና የልሂቃኑን ሚና አግዝፎ የሚያይ ነበር፡፡ ይህን ለማረም የአፍሪካ ኅብረት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በሚፈጽሙ አገሮች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ሊገባ የሚችልበት የሕግ መሠረት ተቀርጿል፡፡ እርግጥ በተግባር ላይ እስካሁን አልዋለም፡፡ በሊቢያ የደረሰውን ሁሉም ያውቀዋል፡፡ ኅብረቱ ከስህተቱ የተማረ በመሆኑ መሰል ችግሮች ዳግም አይፈጠሩም፡፡ ሕዝባዊ ተሳትፎም የኅብረቱ አንዱ ዋነኛ መርህ ሆኗል፡፡ ኅብረቱ ከልሂቃን ሚና ይልቅ ተቋማዊ አደረጃጀቱ ላይ እንዲቆምም ተደርጓል፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡ 
አፍሪካ ኅብረት የኢኮኖሚና የፖለቲካ ለውጥ ዘላቂነት ላይ የሚያተኩሩ እንደ ኔፓድና የአፍሪካ የአቻ ለአቻ ግምገማ ፕሮግራሞችን መቅረፁም ለአምባሳደር ቆንጂት እንደ ስኬት የሚቆጠር ነው፡፡ ሰላምና መረጋጋትን በአፍሪካ አውድ ለማምጣትም በተቀየረው የአፍሪካ የሰላምና ደኅንነት ‹‹አርክቴክቸር›› ሥር ያሉት የሰላምና ደኅንነት ካውንስል፣ የአፍሪካ በተጠንቀቅ የቆመ ኃይል፣ የግጭት ቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓት፣ የሽማግሌዎች ቡድንና የሰላም ፈንድ ተጨባጭ ለውጥ በማምጣት ላይ እንደሚገኙም አስረድተዋል፡፡ በአኅጉሪቱ የሚገኙት ስምንት አካባቢያዊ የኢኮኖሚ ማኅበረሰቦችም ከነችግራቸው አዎንታዊ ለውጥ እያመጡ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ 
በተለይ በአፍሪካ ኅብረት የሚመሩ የሰላም አስከባሪ ተልዕኮዎች ውጤታማ መሆን፣ በአጠቃላይ በአፍሪካ የግጭት ቁጥር መቀነስ፣ የኔፓድ ውጤታማ ሥራ፣ አፍሪካ በአንድ ድምፅ መናገር መጀመሯ፣ ከቀረው ዓለም ጋር የተጠናከረ የሁለትዮሽ ግንኙነት በመፍጠር፣ በተለይ ከቻይና፣ ከህንድ፣ ከኮሪያና ከቱርክ ጋር የተፈጠረው ጠንካራ ግንኙነት፣ የአፍሪካ መንግሥታት ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ያላቸው ቁርጠኝነት ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመሩ የመጪውን ጊዜ ተስፋ ከተግዳሮቶቹ በላይ እንዲያዩት እንዳደረጋቸው አምባሳደር ቆንጂት አስገንዝበዋል፡፡ 
ድኅረ ጋዳፊ አፍሪካ ኅብረት
አምባሳደር ቆንጂት አገራቸውን በዲፕሎማትነት ባገለገሉባት 51 ዓመታት ትልቁ ፈተና ከቀድሞው የሊቢያ ፕሬዚዳንት ሙአመር ጋዳፊ ጋር አብሮ መሥራት እንደነበር የገለጹበት መንገድ ብዙዎቹን ተሳታፊዎች ፈገግ ያሰኘ ነበር፡፡ ‹‹አሁን ሥራ ሲሰጠኝ ተግባሬ ሥራውን በጊዜ ማጠናቀቅ ብቻ ነው፡፡ ጋዳፊ እያለ ሥራዬን ከጨረስኩ በኋላ ያለኝ ሌላው ጭንቀት ጋዳፊ ሥራውን እንዳያበላሸው እንዴት መከላከል ይቻላል የሚል ነበር፡፡›› 
ጋዳፊ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ወደ አፍሪካ ኅብረት እንዲቀየር ከፍተኛ ተነሳሽነት እንደነበራቸው ያስታወሱት አምባሳደር ቆንጂት፣ ይህ ማለት ግን ከግለሰባዊ የሥልጣን ፍላጎት የዘለለ እውነተኛ አፍሪካዊ ስሜት ነበራቸው ማለት እንዳልሆነ አስገንዝበዋል፡፡ በሎከርቢው የአውሮፕላን አደጋ የተነሳ ሊቢያ ላይ ተጥሎ የነበረው ጫና እንዲነሳ ከዓረብ ሊግ አስቀድሞ አፍሪካ ኅብረት በመጠየቁ ደስተኛ የሆኑት ጋዳፊ፣ ዓረቦችን አኩርፈው የአፍሪካውያንን አንድነት ማቀንቀን መጀመራቸውን አምባሳደር ቆንጂት ያስረዳሉ፡፡ 
‹‹የአፍሪካ ኅብረት ገና ሲመሠረት መቀመጫው ወደ ትሪፖሊ መሄድ አለበት አሉ፡፡ ቻርተሩ ሲፀድቅም ስለ ዋና መቀመጫ የሚያወሳው አንቀጽ 24 እንዳይፀድቅ በእጅ አዙርም ቢሆን ተፅዕኖ ያሳደሩት ጋዳፊ ነበሩ፡፡ ቻርተሩ ከፀደቀም በኋላ በየዓመቱ ቢያንስ አንድ የማሻሻያ ሐሳብ ይዘው ይቀርቡ ነበር፡፡ ለማሻሻያ ሐሳቡ ድጋፍና ድምፅ የሚሰጡ አገሮችን በገንዘብ ለመግዛት ያላደረጉት ጥረት የለም፡፡ ደግነቱ ማሻሻያ ሐሳቦቹ በ2/3ኛ ድምፅ ድጋፍ መፅደቅ ስለነበረባቸው ያን ያህል ድምፅ መግዛት አልቻሉም፡፡ ነገር ግን በማሻሻያ ሐሳቦቹ ላይ ይደረጉ የነበሩ ውይይቶችና አንዳንድ ጭቅጭቆች የኅብረቱን ውድ የሥራ ጊዜያት አባክነዋል፡፡ አሁን ያ ችግር የለም፡፡ ከጋዳፊ ሞት በኋላ የአፍሪካ ኅብረት በሚገባ እየሠራ ነው፤›› ብለዋል፡፡
አፍሪካ ኅብረትና መጪው ጊዜ
ብሩህ መጪ ጊዜን ለማረጋገጥ ኅብረቱ በዋነኛነት በገንዘብ ራሱን ሊችል፣ ተቋማዊ አቅሙን ሊያዳብር፣ የሰላምና የፀጥታ ተግዳሮቶችን በሚገባ ሊወጣ፣ በአባል አገሮቹ መካከል በተለያዩ ምክንያቶች ያሉትን የመከፋፈል አደጋዎች ሊያስወግድ፣ በአካባቢያዊ የኢኮኖሚ ማኅበረሰቦች መካከል ያለውን ተደራራቢ አባልነትን ሊያስወግድ፣ ደካማውን ኢኮኖሚያዊና የመሠረተ ልማት ውህደት ማጠናከር የሚገባው መሆኑን የጠቆሙት አምባሳደር ቆንጂት፣ ወጣቱ ትውልድ ሰላማዊ፣ የበለፀገችና የተባበረች አፍሪካን ለማረጋገጥ የተሻለ ጊዜ ላይ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ 
‹‹51 ዓመታት በሠራሁት ሥራና ለአገሬ ብሎም ለአኅጉሩ ባደረግኩት አስተዋጽኦ እኮራለሁ፡፡ የግል ሕይወቴንና የቤተሰቦቼን ፍላጎት መስዋዕት አድርጌ ነው በሥራው ላይ ይኼን ያህል ዓመታት የቆየሁት፡፡ የጎደሉ ነገሮች ነገ ይሞላሉ፡፡ እኔ በቅርቡ ጡረታ እወጣለሁ፡፡ ወደ ኋላ ተመልሼ ሥራዎቼን ሳያቸው እርካታ ነው የሚሰማኝ እንጂ ፀፀት የለኝም፡፡ ሁሉም አፍሪካዊ የኅብረቱን ሥራ ለማገዝና ለመለወጥ ሚና እንዳለው ሊገነዘብ ይገባል፡፡ እዚህ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ተመራማሪዎች አላችሁ፡፡ የኅብረቱን ሥራ የሚያቃኑ በርካታ የምርምር ሥራዎች መሥራት ትችላላችሁ፡፡ ከእኔ የምትፈልጉት ዕርዳታ ካለ ቢሮዬ ምንጊዜም ክፍት ነው፡፡ እባካችሁ ባገኛችሁት አጋጣሚ አፍሪካ ኅብረትን አጀንዳ አድርጉት፤›› የሚለው የአምባሳደር ቆንጂት ምክር ነበር፡፡ 
‹‹ከጋዳፊ ሞት በኋላ አፍሪካ ኅብረት በሚገባ እየሠራ ነው››  አምባሳደር ቆንጂት ሥነ ጊዮርጊስአምባሳደር ቆንጂት በውይይት መድረኩ ላይ በርካታ ጥያቄዎች የቀረቡላቸው ሲሆን፣ ኅብረቱ ራሱን በገንዘብ ሊችል የሚችልበት መንገድን በተመለከተ ለቀረበው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ኅብረቱ ከአባላት የሚያገኘው ገቢ በመጨመሩ አሁን 50 በመቶ ራሱን መቻሉን ጠቅሰው፣ ድርሻውን ለመጨመር ኮሚቴ ተቋቁሞ የተለያዩ የገቢ መሰብሰቢያ ፕሮግራሞች መዘጋጀታቸውን ጠቁመዋል፡፡ 
ከብራዚል ኤምባሲ ተወክሎ ስብሰባው ላይ የተገኘ አንድ ወጣት አፍሪካ ከላቲን አሜሪካ ጋር ያላት የሁለትዮሽ ግንኙነት እንዴት ስኬታማ ሊሆን እንዳልቻለ ላቀረበው ጥያቄ፣ አምባሳደር ቆንጂት የግንኙነት ክፍተትና ቸልተኝነት በላቲን አሜሪካ ዘንድ መስተዋሉን ገልጸው ችግሩን ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ 
አንድ ጠያቂ አፍሪካ ኅብረትን ከፍሪካ አንድነት ድርጅት ጋር ከማነፃፀር ለምን ከአውሮፓ ኅብረት ጋር እንደማይነፃፀር ለቀረበው ጥያቄ፣ አምባሳደር ቆንጂት በሰጡት መልስ ሁለቱ ተቋማት ካላቸው የታሪክ፣ የፖለቲካና የስኬት ተሞክሮ አኳያ ለንፅፅር ለማቅረብ እንደማይቻል አስረድተዋል፡፡ 
ሕዝባዊ ተሳትፎን በተመለከተ ለቀረበው ጥያቄም፣ ኅብረቱ ራሱን ለሕዝባዊ ተሳትፎ ክፍት በማድረግ ተወዳዳሪ የሌለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ተደራራቢ የአካባቢ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ አባልነትም ከውጤታማነትና ከታማኝነት አኳያ ትልቅ ችግር መሆኑን አስረድተዋል፡፡ 
የዲሞክራሲ ግንባታን በተመለከተ ለቀረበው ጥያቄ በሒደት ዘላቂ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በአፍሪካ ለመገንባት እየተሠራ ያለው ሥራ አበረታች መሆኑን ጠቁመው፣ መጪው 50 ዓመት ካለፈው 50 ዓመት ፈጽሞ የተለየ እንደሚሆንም ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2014 እስከ 2017 የሚቆየው የኅብረቱ ስትራቴጂካዊ ዕቅድና አጀንዳ 2063 የተሰኘው የአፍሪካ ኅብረት ታላቁ ራዕይ ዲሞክራሲ የተረጋገጠባትና ኢኮኖሚው በተፋጠነ ሁኔታ የሚያድግባት አፍሪካን እንደሚፈጥርም ተስፋ አድርገዋል፡፡ 

አሳሳቢና የወደቀ እንጂ አበረታች የኢኮኖሚ እድገት የለንም!! ያልተጠና ተደራራቢ የልማት ጉዞ መንግስትን ቀውስ ውስጥ ከቶታል::

አሳሳቢና የወደቀ እንጂ አበረታች የኢኮኖሚ እድገት የለንም!!
ያልተጠና ተደራራቢ የልማት ጉዞ መንግስትን ቀውስ ውስጥ ከቶታል::

ምንሊክ ሳልሳዊ
ባለፈው ሰሞን እንዳየነው ወያኔው በተጭበረበረ ፖለቲካ ላይ እየገነባ ያለው ኢኮኖሚ እየተንኮታኮተ መሆኑን ነው:: ይህንን ተከትሎ ከፍተኛ የሆኑ የገንዘብ ተቋማት ብሄራዊ ባንክን ጨምሮ ሙስናው በፈጠረው የኢኮኖሚ እብደት አጣብቂኝ ውስጥ መሆናቸው ተረጋግጧል::ተነሳሽነት ካለ በሃገሪቱ ውስጥ ያሉ ችግሮች የሚፈቱ እና አስቸጋሪ ያልሆኑ ናቸው:: ሆኖም ከፍተኛ የሆኑ የሕወሓት ባለስልጣናት በሙስና እና በፖለቲካ ማጭበርበር የህዝብ ችግሮች እንዳይፈቱ እያደረጉ ነው:: ገስት ሃውስ፣ ጫት ቤት፣ ሺሻ ቤት፣ማሳጅ ቤት፣... በየቦታው መስፋፋት የሃገሪቱ ኢኮኖሚ እድገት ሳይሆን ውድቀት እና የትውልድን ዝቅጠት ያመለክታል::

የኢኮኖሚው መንኮታኮት እና የንግዱ እንቅስቃሴ ዝምታ ምንም አይነት ኤክስፐርት መቅጠር ወያንም በጉዳዩ ላይ ተቋም አዋቅሮ ምርምር እና ጥናት ማድረግ አያስፈለገውም በገሃድ እየታየ ያለ ነው:: የመንግስት ሚዲያዎች የሃሰት ፕሮፓጋንዳ እና የበለጸጉት ሃገራት ብሄራዊ ጥቅምን ተመርኩዞ የሚወጣ የእድገት ቁጥር ቁልል ይህንን ለመደበቅ አልቻሉም::በአደባባይ በይፋ እያየነው ነው::በሃገሪቷ ላይ የተፈጠረው ሙስናን መሰረቱ ያደረገው የዋጋ ግሽበት እና የውጪ ምንዛሪ አቅርቦት ባዶ መሆን ሌተር ኦፍ ክሬዲት ለመክፈትም አለመቻሉ የፋብሪካ ውጠቶችን ለማምረት የሃገር ውስጥ ማኑፋክቸሮች ለምርቶቻቸው የሚያስፈልጓቸውን በወቅቱ በቦታል አለማግኘት የውጪ ምንዛሬ አቅርቦት ባዶነት ለስራቸው መኮላሸት ምክንያት እየሆኑ ሲሆን የባንክ ብድሮች ሙስናን መሰረት አድርገው መስራታቸው የመንግስት ድርጅቶች አስፈላጊውን ክፍያዎች በገንዘብ እጥረት አለማድረጋቸው የንግዱን እንቅስቃሴ እያንኮታኮተው ሲሆን ይህ ደግሞ የሰራተኛ መፈናቀልን እና ሰርቶ የመኖር መብት ማጣትን ውጤታማ እያደረገ ነው::

በወያኔ መንግስት ነጋዴውን እና ንግዱን እንመራለን በሚሉ ባለስልጣናት እና ሰራተኞቻቸው ዙሪአ እንዱም ከነጋዴው ጋር በመካከላቸው መተማመት የጠፋ ሲሆን የሙስናው ገመድ ሊያንቀኝ ይችላል በሚል ስልጣናቸው ሆኖ ያሉ ሰዎች ማንኛውንም ስራዎች ለመስራት የበላይና የበላይ ትእዛዝ የሚጠብቁበት በተጨማሪም ቀላል የሆኑ ፍቃድን የማውጣት እና የመመለስ ስራዎች ችግር እየፈጠሩ መሆኑ ሲታወቅ የግል ጥቅመኝነትን እንደ ዋነኛ መዘውር ማድረጋቸው ቢሮክራሲውን ተብትበውት ለኢኮኖሚው መንኮታኮት የፖለቲካው ድርሻ ጭነት ዋነኛው መሆኑን በገሃድ እየታየ እና ለሃገር እና ለህዝብ ደንታ የሌላቸው ከፍተኛ ባለስልጣናት ለራሳቸው ሙስና እና ማጭበርበር ያመቻቸው ዘንድ በፈጠሩት ሰንሰለት ኢኮኖሚውን በባዶ አስቀርተውታል::

ፖለቲካው የወለደው ጭካኔ የፈጠረው የኢኮኖሚ መዛባት ህዝቦች የሚያገኙትን መረጃ በስራት እንዳያገኙ የህትመት ውጤቶችን እየጎዳ ነው::ይህ ከወያኔ ባለስልጣናት የሚተላለፉ መመሪያዎች ውጤት የሆነው እና ሀገሪቷን ለድቀት የዳረጋት የስልክ ትእዛዝ የህዝቦችን መረጃ የማግኘት መብት ከመጉዳቱም በላይ ወረቀት እና ቀለም የለም፣ ማሽን ተበላሽቷል፣ ...በሚል ምክንያት ፕሬሱ የሕትመት ችግር እያጋጠመው ነው፡፡ ከምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴ አኳያ ሲታይ እጅግ አስቸጋሪ ስለሆነ ኢኮኖሚውን አንገላቶት ገደል ጨምሮታል::
ኢኮኖሚውን ያጠናክራሉ በሚባሉ የንግድ ተቋማት የሚሰማውን አቤቱታ እና ቅሬታ የሚያዳምጥ በመጥፋቱና ቅሬታ ሰምቶም መፍትሄ ና ውሳኔ የሚሰጥ አካል ባለመኖሩ መተማመኖች በመስፋታቸው መዋእለ ንዋዬን አፍስሼ በኋላ ቢያስቆሙኝስ ቢነጥቁኝስ በማለት የሚሰጋው ነጋዴ ጨምሯል ፡፡ ለችግሮቻችን መፍትሄ ስጡንየሚለው መብዛቱ አዳማጭ መንግስት በመጥፋቱ ሥራ ለማቆም የሚገደዱ እየበዙ ነው፡፡ በባንክ ዕዳ ተወጥረው የሠራተኛ ደመወዝ እየከፈሉ፣ ለቢሮ፣ ለመጋዘን፣ ለኤሌክትሪክና ለተለያዩ ወጪዎች በመዳረግ ገቢ የማያውቁ በርካታ የሥራ ዓይነቶች አሉ፡፡ ድርጅታቸው እንዳይዘጋ አንድ ቀን ችግሩ ይፈታል በሚል ተስፋ፣ እንዳይቀጥሉ ደግሞ የወጪ መብዛት እያስጨነቃቸው ጭንቅ ውስጥ የገቡ በርካታ ናቸው፡፡ ሥራቸውን ያቆሙም አሉ፡፡

በሃገሪቱ የተፈጠረው ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ግዥበት እና የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት ዜሮ መሆን የገንዘብ ምንጭ ይሆናሉ የተባሉትን ሁሉ በባዶ አባዝቶ ከየባንኩ ግድግዳ እያላጋቸው ነው::ወያኔ ምእራባውያንን ለማታለል ለፖለቲካው ፍጆታ ለመበልጸግ ሲል የጀመራቸው ስማቸው ልማት የተባሉት የሃገሪቷን የገቢ አቅም ያላመዛዘኑ እና የግሉን የገንዘብ ተቋማት የተፈታተኑ ከመሆኑም በላይ ባንኮች በየቦታው ያላቸውን አክሲዮኖች እስከመሸጥ እንዲደርሱ አድርጓቸዋል::
ፖለቲካን ተገን አድርገው የተቋቋሙ የንግድ ድርጅቶች ሌላውን የንግድ ክፍል አላሰራ ከማለታቸውም አስፈላጊውን የግብር እና የቀረጥ ገቢዎች አላመክፈላቸው እና ትልልቅ የንግድ ገቢዎችን በሞኖፖል ገዢውን ፓርቲ ተንተርሰው ማንቀሳቀሳቸው ለሃገሪቱ የኢኮኖሚ መውደቅ ሌላው ምክንያት ነው::
በአጠቃላይ ያለው የወያኔ ጁንታ በፖለቲካው ላይ ተመርኩዞ የፈጠረው ኢኮኖሚ ምንም ውጤት አለማምጣቱን መመልከት ስለተሳነው ኢትዮጵያውያን ሁሉ በጋራ ይህንን አጭበርባሪ ስርኣት ገርሲሰን መጣል የዜግነት ግዴታችን መሆኑን ለማሳሰብ እወዳለሁ::