ድህነት ሲመጣ ቃላት ይበዛል። ስብሰባ፣ ንግግር፣ የማይተገበር ቃል - መግባት እንደህይወት ይወሰዳል፡፡ እንደኑሮ ይለመዳል፡፡


ምንጭ ፦አዲስ አድማስ

የህዝብን የኑሮ ደረጃ ዝቅ ብሎ ወርዶ የሚያይ መሪ፣ አለቃ፣ ኃላፊ ማግኘት መታደል ነው፡፡ ያስቀናል፡፡ የዋጋ መናርና የታክስ ማሻቀብ አንድን ማህበረሰብ የጦርነትን ያህል ያጠፋዋል፡፡ ለዚህ ነው መሪዎች ሁሉ የህዝባቸውን ኑሮ በቅርብ ያስተውሉ የሚባለው፡፡ ህዝብ የሀገር ሙቀት መለኪያ ነው፡፡ ህዝብ የሚከፍለው ግብር ከሚያገኘው አገልግሎት ጋር ካልተመጣጠነ የቀዘቀዘች አገር ውስጥ ነው የሚኖረው፡፡ ህዝብ ደሞዙ ከሚኖረው ኑሮ ጋር ካልተመጣጠነለት ኖረ አይባልም፡፡ ህዝብ ከዕለት ዕለት ህይወት እየከበደው ከሄደ ከሳቁ ምሬቱ፣ ከደስታው ሐዘኑ እየበረታ ሥርዓቱን፣ አገዛዙን፣ ገዢዎቹን፣ አስተዳዳሪዎቹን ይጠላል፡፡ ሀገሩም የእሱ አትመስለውም፡፡ ህዝብ መሰረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን ለማግኘት ነግ-ሠርክ የሚሰለፍ ከሆነ፤ አልፎ ተርፎም ከናካቴው ዕጥረት የሚከሰትበት ሁኔታ ከመጣ፣ ብሶቱ ወሰን አይኖረውም፡፡ ህዝብ በመኖሪያ ቤት ችግር የሚሰቃይ ከሆነ መሰረታዊ የኑሮ አስፈላጊ ነገር ጎሎበታል ማለት ነው፡፡

 ከዚህ ሁሉ የሚከፋው ደግሞ ይህንን የሚገልፅበት መንገድ ካጣና በፍርሃት ተሸማቆ ከተቀመጠ ነው፡፡ “አዲስ ያይጥ - ወጥመድ በሰራህ ቁጥር” አዲስ አይጥ የምትወለድ ከሆነ፣ ወይ ወጥመዷ ላይ ወይ አጥማጁ ላይ ችግር አለ ማለት ነው” ይባላል፡፡ በሙስና የተሞላ ልማት ዘርዛራ ወንፊት ነው፡፡ ዕብቁንም፤ እንክርዳዱንም፤ እያሳለፈ፤ እያዩ እህል አለን እንደሚሉት አይነት የዋህነት ይሆናል፡፡ የዚህ ሁሉ መጨረሻው ድህነት ነው፡፡ ድህነት ሲመጣ ቃላት ይበዛል። ስብሰባ፣ ንግግር፣ የማይተገበር ቃል - መግባት እንደህይወት ይወሰዳል፡፡ እንደኑሮ ይለመዳል፡፡ “አንድ መንግሥት ከሌላ መንግሥት የሚማረው ጥበብ ከህዝብ ኪስ ገንዘብ አሟጥጦ መውሰድ ነው” ይለናል፤ አዳም ስሚዝ የጥንቱ የጠዋቱ የኢኮኖሚ ሊቅ፡፡

አንድ የአሜሪካኖች አባባል አለ:- “በአንድ አገር ከዋናው ይልቅ ምክትሉ ነው ምርጥ ሥራ አለው የሚባለው፡፡ ምክንያቱም ትልቁ ሥራው ጠዋት ሲነሳ ‘ዋናው አለቃ ደህና አደሩ?’ ማለት ብቻ ነው!” ከዚህ ይሰውረን፡፡
ኑሮ እጅግ በከፋ ሁኔታ ላይ ሲገኝ፤ እንግሊዞች “ሶስት ትውልድ ሙሉ ሸሚዛችንን እንደጠቀለልን አለን” ይላሉ፡፡ ጣሊያኖች ደግሞ፤ “ከከዋክብት እስከ ጋጣ/በረት እየኖርን ነው” ይላሉ፡፡ ስፔይኖችም፤ “ሀብትን፤ የሌለው ይሠራዋል። ያለው ያላግባብ ይጫወትበታል” ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን፤ “ኑ እስኪለን መከራችንን እናያለን” ይላሉ፡፡ አምላክ አንደኛውን እስከሚጠራን ቀን ድረስ አበሳ ፍዳችንን እየቆጠርን ነው እንደማለት ነው!! ሁሉ የምሬት ቋንቋ አለው! ጊዜውና ደረጃው ይለያይ እንጂ ምሬቱ የሚፈታበትም መንገድ እንደዚያው ይለያያል፡፡ ማናቸውም ዕቅድና ስትራቴጂ ህዝብ ኑሮ ላይ ያነጣጠረ መሆን አለበት፡፡ ይሄ ማለት የእርስ በርስ ሙግትና የአዕምሮ አክሮባት ከመሥራት ይልቅ፤ የህዝቡስ ሁኔታ እንዴት ነው? ማለት ዋና ጉዳይ ነው፣ ማለት ነው፡፡ ለህዝብ ተብሎ፣ በህዝብ ስም የተቀረፀውንም አጀንዳ ለግል ጥቅም እንዳይውል ጠንክሮ መጠበቅ ይገባል፡፡

በሀገራችን “ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል” የተባለው ተረት ዕድሜው እጅግ ረጅም ነው፡፡ የሥርዓቶቻችንን ያህል አርጅቷል፡፡ በተግባር ሲተረጐም ግን ገና ዛሬ የተወለደ ነው የሚመስለው፡፡ በየቢሮው፣ በየማህበሩ፣ በየፓርቲው የምናየው ሀቅ ነው፡፡ “አዲስ እረኛ ከብት አያስተኛ”፣ “እከክልኝ ልከክልህም” አብሮ ሲተረት የኖረ ነው፡፡ እዚህ ላይ፤ ሁለት የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ሲቀያየሩ ሂያጁ ለመጪው ያለውን መጥቀስ መልካም አርአያነት ያለው ነው:-

“እኔ ይሄን ሥልጣን (ቢሮ) ለቅቄ ስወጣና ወደቤቴ ስሄድ፤ የተደሰትኩትን ያህል አንተ ወደዚህ ሥልጣን በመምጣትህ የምትደሰት ከሆነ፤ በዚች አገር የመጨረሻው ከፍተኛ ደስተኛ ሰው አንተ ነህ ማለት ነው!” (ይህን የተባሉት አብርሃም ሊንከን ናቸው) ይሄ መታደል ነው፡፡ በማናቸውም መንገድ ሥልጣን ላይ የሚወጣ ሰው፤ “ሥልጣን በሸተተው ማግስት አካሄዱ ሁሉ ይለዋወጣል፤ እንደድመት ኮርማ ይሆናል” ይባላል፡፡ ከዚህም ይሰውረን። አክብሮታችን ለመንበሩ እንጂ ለሰውዬው አይደለም፡፡ ዞሮ ዞሮ ህዝብን ማገልገያ መንበር መሆን አለበት፡፡ አንዱ ባለሥልጣን ሌላውን ባለሥልጣን የጐዳ መስሎት በሚሠነዝረው ጥቃት የዝቅተኛው ክፍል ህዝብ መጠቃቱ ትልቅ ጉዳት ነው፡፡ አፍ በሰፋ ቁጥር ተሳዳቢው ህዝብ ነው፡፡ የሚላክበት ህዝብ ነው፡፡ ጎረቤትም ቢቆስል ጦሱ ላገር ነው፡፡ የቆሰለ አውሬ ለያዥ ለገራዥ አስቸጋሪ ነው፡፡ ጣጣው ግን የህዝብ ነው፡፡  

በሁሉም አቅጣጫ የጨለመበት የኢትዮጵያ ህዝብ በሃገሩ ላይ ተስፋ ቆርጧል።


ምንሊክ ሳልሳዊ ፦ የመላው ኢትዮጵያውያን ሮሮ እና አቤቱታ የሆኑት የመብራት፣ የስልክ፣ የውኃ፣ የትራንስፖርት፣ የፍርድ ቤቶች አሰራር እና ተመሳሳይ መንግስታዊ ተብዬ ተቋማት አሰራሮች አገሪቷን አጥቁረዋታል ፤ ሕዝቡንም አድቅቀውታል፡፡ መፍታት አለማወቅ ይሁን መንግስታዊ ተንኮል አሊያም የሌላ አላማ ህዝብን የማደህየት ደባ እስካሁን ምንም አይነት መፍትሄ ሲሰጥ አልታየም። መሰረታዊ የህዝብ አገልግሎት መስጫዎች ከፍሎ በሚገለገለው ህዝብ ላይ እንደፈለጉ ሲሸኑ አለሁ የሚል መንግስትም ይሁን ባለስልጣን ሃይ ሲል አልታየም ። በፍርድ ቤቶች ደጃፍ በተደጋጋሚ ቀጠሮ ብቻ መዝገቦች ሳይፈተሹ በቀጥሮ ሂድ ና የሚባለው ህዝብ የትየለሌ ነው። የፍትህ ጥማትን የሚቀርፍ ማግኘት ባለመቻሉ ሕዝብ በፍትሕ ስርአቱ ላይ ተስፋ ቆርጧል።

በአገሪቱ የሚታዩ የወያኔ መንግስት ተቋማት ናቸው የሚባሉ በአጠቃላይ ማለት ይቻላል የሚያገለግሉትን ህዝብ የማያከብሩ የስራ ትርጉም ያልገባቸው የፖለቲካ ፍጆታቸውን ለማሳካት ሲሉ የሚሮጡ የህዝብን ሃብት እና ንብረት የሚበዘብዙ ዋልጌዎች የተሞሉ ሲሆን ከማንኛውም የመንግስት ተቋም አገልግሎት አገኛለሁ አቤቱታየ ይሰማል ብሉ ማመልከት ውጤት ያሌለው በመሆኑ ሕዝቡ በመንግስት ሰራተኛው ላይ ተስፋ ቆርጥዋል።የወያኔ መንግስት ባለስልጣናት አትኩሮታቸው ለህዝቡ ሳይሆን ወደ ፖለቲካው ብዝበዛው የግል ቢዝነሱ እና የፓርቲ ስብሰባ ነው።

ወያኔ ህገመንግስት ያለው የወረቀት ላይ ማር የሰብዓዊና የዲሞክራሲያዊ መብቶችን ድንጋጌዎች ይተነትናል ፡፡ እነዚህ ከተ.መ.ድ. የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ ተገልብጠው የሰፈሩ ህጎች ወሬ ሆነዋል በተግባር የሚተረጉማቸው የሚያከብራቸው የሉም፡፡ ለስብሰባና ለመፈክር ማድመቂያ ካልሆነ በስተቀር ዜጎች እነዚህን መብቶች ሲጠይቁ የሚያገኙት ምላሽ ተቃራኒውን ነው፡፡ በሕግ ጥበቃ ሥር ናቸው የተባሉ ከፍተኛ የሆነ የስቃይ የቶርች እና የሰቆቃ ግርፋት ይፈጸምባቸዋል የሚል ሪፖርት በአለም አቀፍ የሰብ አዊ መብት ወኪሎች እንዲሁም የወያኔ መንግሥት ባዘጋጃቸው ስብሰባዎች ላይ እንዲሁም በታሳሪዎች አንደበት ሲነገር ተደምጧል፡፡ መብታቸውን በመጠየቃቸው ብቻ ከሥራቸው ተባረው ለመከራ የተዳረጉ ዜጎች ቤቱ ይቁጠራቸው ፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት መብታቸውን የሚጠይቁ እንደ ጠላት ይፈረጃሉ፡፡

ሃገራችን እና ወገናችን በጨለማ ውስጥ እየዳከረ ባለበት በዚህ የወያኔ አገዛዝ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በመረባረብ የዜግነት ግዴታውን አውቆ ለህዝቦች መብት እና ነጻነት መታገል አለበን። ሃገሪቷ በዚህ አደጋ ውስጥ ባለችበት ሰአት ላይ ህዝብ አጣብቂኝ ውስጥ ገብቶ ለኑሮ ውድነት ለሞት ለስደት እየተዳረገ ኢትዮጵያዊነት እየተዋረደ ከመሆኑም ባሻገር ሃገሪቷን ወደ ፍርስራሽነት ለመቀየር የሚሮጡ ጥቂት ሆዳሞች ባሉበት ልንቀብራቸው ይገባል። በአስተሳሰባቸው የላሸቁ በሰለጠነው አለም እየኖሩ በድህነት የተዘፈቀውን ህዝብ በጎሳ ለማፋጀት ሆን ብለው የሚሯሯጡ የባዶ ፖለቲካ ኢንተርሃሞዮችን መዋጋት ግድ ይለናል። ያልሰለጠነውን ማሰልተን የህዝብን እድገት መመኘት ለነጻነት እና ለመብት መታገል እና ከጭቆና ነጻ መውጣት ሲገባን የጋራ ክንዳችንን ማስተባበር ባለብን ወቅት ኢትዮጵያን ሩዋንዳ ለማድረግ ደፋ ቀና የሚሉ ባሉበት እንዲሞቱ ማድረግ የጋራ ግዴታን ነው።ምንሊክሳልሳዊ