በፍትህ እና በፍትህ አካላት ላይ የተጫኑ የፖለቲካ ደባዎች ይውረዱ::

Minilik Salsawi (ምንሊክ ሳልሳዊ) - የወያኔ ጉጅሌ አገዛዝ በሚያመቸው መንገድ ሃይማኖታዊ የፖለቲካ አደረጃጀት በመፍጠር ለዘመናት የቆየውን የሃይማኖት ቀኖና ትላንትና እንደ አይሁድ ባሉ መርዘኛ መንግስታት በተፈጠሩ ዘመን አመጣሽ የአሕበሽ እምነቶች ለመተካት እና የኢትዮጵያውያንን የሰላም እና የፍቅር ተምሳሌት የሆነውን እስልምናን ለማደፍረስ ደፋ ቀና በማለት ትላንት እውቅና ለሰጣቸው የሙስሊም ምሁራን ወገኖቻችን የአሸባሪነት ታርጋ በመለጠፍ በጠፍ ጨረቃ መኖሪያቸውን በመስበር በከፍተኛ ስቃይ እና እንግልት ወደ እስር ቤት አግዞ ካለምንም ማስረጃ እና ካለበቂ ሰነድ አግቶ በማንገላታት ላይ ነው።ወንጀለኞች በንፁሃን ላይ የሚፈርዱበት ችሎት ሊሰየም 2 ቀናት ቀርተውታል!

በአሁን ወቅት የወያኔ ጉጅሌ በፍትህ አካላት ክለላ የሚፈጸመው የፖለቲካ ደባ የሙስሊሙን ጉዳይ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ላይ የተደረገ ያለው ኢ ፍትሃዊ እና የዜግነት ንጽሕናቸውን የሻረ ፖለቲካዊ ብይን/ውሳኔ ማናችንም የማንቀበለው ከመሆኑም በላይ የትግሉን ብርታት እና ወኔ የማያጥፈው የበለጠ የሚያጠናክረው መሆኑ መዘንጋት የለበትም::የወንድሞቻችን የኮሜቴው ጉዳይ የሙስሊም ሃይማኖት ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያውያን የፍትሕ ጉዳይ ነው::የወያኔ ስርአት ራሳቸውን አክብረው እና ሃይማኖታቸውን ጠብቀው ከፖለቲካ እድፍ ነጻ ነን ያሉ ምሁራንን እንደ ተቃዋሚ;ሕገመንግስታዊ ጥያቄ ያቀረቡ ዜጎችን እንደ አሸባሪ ;በነጻነት ማምለክ መጸለይ እንፈልጋለን ያሉ ትን እንደ አክራሪ ወዘተ ... በመፈርጅ የፍትሕ ስርአቱን ለፖለቲካ ግብኣት በማዋል የዜጎችን መብት ገፎ በየእስር ቤቱ በማጎር ኢትዮጵያ ለብዙሃን ሕዝቦቿ አንገት መድፊያ ለጥቂት ጉጀሌዎች መውደቂያቸው እስኪደርስ መንቀባረሪያ በማድረግ የፍትህ ስርአቱን ለፖለቲካ አላማቸው አውለው የሕግ የበላይነትን ቀብረውታል::

እጅግ አስደንጋጭ እና አሳዛኝ የሰው ልጆች በገዛ አገራቸው ዜጋ አይደለንም እንዲሉ በፍርሃት ተሸብበው እንዲኖሩ ለማድረግ የተቀናጁ አሰቃቂ ወንጀሎች በኢትዮጵያውያኑ ሙስሊም ምሁራኖች ላይ ተፈጽሟል። ታሪክ ይቅር የማይለው ከባድ መንግስታዊ ወንጀል ማንንም ከተጠያቂነት እንደማይመልስ ትውልድ በተግባር ያሳያል።ትግሉን እየመራ የሚገኘው "ድምጻችን ይሰማ" ባስተላለፈው መልእክት ህዝበ ሙስሊሙን ለረጅም ጊዜ መብቱን ገፍፎና ጨቁኖ በመያዝ እቅድና ሂደት ላይ መገኘቱ እኛም ዓመታትን አሻግረን ተመልክተን የትግላችንን አድማስ በማሳደግ ለመብታችን መከበር የምናደርገውን እንቅስቃሴአጠናክረን እንድንቀጥል ያስገድደናል፡፡ የትግላችንን ህዝባዊ መሰረት አጠናክረን የጀመርናቸውንና ሌሎች መሰል ግፊት የሚያሳድሩ የትግል አቅጣጫዎችን በመከተል ዘርፈ ብዙ ችግሮቻችን ለመፍታት በምንጥርበት መልኩ ተግባራዊ እናደርጋለን::

በውድ ኮሚቴዎቻችን ላይ የሚተላለፈው የግፍ ብይን በዳዮቻችን እንደሚያስቡት ወኔና ብርታታችንን የሚሰብር ሳይሆን እስካሁን ከከፈልነው በተጨማሪ መስዋእትነቶችን ለመክፈል የምንዘጋጅበትን ቁርጠኝነትን የሚለግሰን ይሆናል፤ የጥፋተኝነት ብይኑ በተላለፈበት ችሎት ውድ ኮሚቴዎቻችን ያሳዩት ጀግንነት ለዚህ ምስክር፣ ለእኛም የሞራል ስንቅ ነውና!እኛም ከድምጻችን ይሰማ ጎን በመቆም ከሕዝበ ሙስሊሙ የሕግ የበላይነት ይከበር ጥያቄዎች ጋር እጅ ለ እጅ ተያይዘን ‹‹የትግል ወኔ እና ብርታታችን በፖለቲካዊ ውሳኔ አይታጠፍም!›› በማለት የጋራነት የአብሮነት የወንድማማችነት ትግላችን እስከድል ደጃፎች ድረስ ይቀጥላል::የአብሮነታችን ተምሳሌት ለአለም ያስተማረውን የአያቶቻችንን የአንድነት ፍቅር ደግመን በዚህ ትውልድም ማሳየት አለብን ። አምባገነኖች ጠንክረን ከታገልናቸው ቀዳዳው ሁሉ ስለሚጠብባቸው ተፍረክርከው ይጠፋሉ። በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎች ላይ የደረሰው ግርፍት እና መከራ ቁስሉ የኔም ነው። ‪#‎ምንሊክሳልሳዊ‬

በጭፍን ስሜት የመነዳት ልማድ ለስህተት ይዳርጋል::

የዘንድሮ ፖለቲካ፣ ብዙዎች ከሚገምቱት ውጭ፣... በግራ በኩል ሲጠብቁት በቀኝ በኩል የሚነጉደው ለምንድነው? “ግራ መጋባት” ይሉሃል ይሄ ነው። እንዲህ የምንሆነው፣ ሳናስተውል ስለቀረን ወይም ሚዛን ስለጠፋብን ይሆን? እንደዚያ ከሆነ፣ ጥፋቱ የኛ ነው። ግን፣  ሌላውስ ዓለም መች ከግራ መጋባት ዳነ! “ለየትኛውም አገር ቢሆን፣ የዘመኑ ፖለቲካ መላ የለውም’ኮ” ሊባል ይችላል። በእርግጥም፣ ብዙ ሰዎች ከሚጠብቁት ውጭ፣ ዓለማችን ከዳር ዳር እየተናጠች ነው። ግራ መጋባት የተበራከተው፣ በኢትዮጵያውያን ላይ ብቻ አይደለም። ቢሆንም ግን፣ ኢትዮጵያ ላይ በዛ፣ ተደጋገመ፣ ተደራረበ።በተለይ በተለይ፣ ኢትዮጵያን በሚመለከት፣ የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ አቋምና ጉብኝት በፍፁም ድንገተኛ ሊሆንብን አይገባም፡፡ “የአሜሪካ እጅ ረዝሟል፤ ማሳጠር አለብን” ብለው የሚያምኑት ባራክ ኦባማ፤ አሜሪካ በየአገሩ ጣልቃ ገብታ “የግለሰብ መብት አክብሩ፤ የፖለቲካ ምርጫ አካሂዱ፤ የነፃ ገበያ አሰራር አስፋፉ” እያለች ተፅእኖ ማሳረፍ እንደሌለባት ደጋግመው ተናግረዋል። ይሄ፣ ከዋና ዋና የኦባማ መርሆች መካከል አንዱ ነው። ሳይመረጡ በፊትም ሲናገሩት የነበረ፣ ከተመረጡ በኋላም በተግባር የገፉበት የውጭ ግንኙነት መርህ ነው። ከስድስት ዓመት በላይ ካላንቀላፋን በስተቀር፣ የኦባማ አስተሳሰብና አዝማሚያ ገና ድሮ ፍንትው ብሎ ሊታየን ይገባ ነበር። ለምን?

አውሮፓና አሜሪካ “በአለም ዙሪያ የግለሰብ ነፃነትን፣ የፖለቲካ ምርጫዎችንና የነፃ ገበያ አሰራርን የሚያስፋፋ የፖለቲካ ለውጥ ለማምጣት፣ ተፅእኖ ማድረግ ዋጋ የለውም። እንዲያውም ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል” ወደሚል አስተሳሰብ አዘንብለዋል።እንደ አፍሪካ ቀንድ በመሳሰሉ የውጥረት አገራት ውስጥ፣ የተረጋጋ መንግስትና የኢኮኖሚ እድገት ከተገኘ በቂ ነው” ወደሚል ተስፋ ቢስነት እየወረዱ ነው።አውሮፓና አሜሪካ፣ በኢትዮጵያ ለሚካሄድ የፖለቲካ ምርጫ ሲሰጡት የነበረ ትኩረት ምን ያህል እንደቀነሰ በዘንድሮው ምርጫ በግልፅ ታይቶ የለ!!የኢትዮጵያ መንግስት፣ ለአካባቢው አገራት መረጋጋት እስካገዘ ድረስ፣ ከአውሮፓና ከአሜሪካ የወዳጅነት እርዳታ ማግኘቱ የማይቀር ነገር ነው - በዛሬ አለማቀፍ የትርምስና የሽብር ዘመን።ይህንን ማስተዋልና ማገናዘብ ከቻልን፣ የኦባማ ጉብኝት በጭራሽ ድንገተኛ ተዓምር ወይም ዱብዳ አይሆንብንም፡፡

ባራክ ኦባማ፣ ለኢትዮጵያ መንግስት የሚያሳዩት የወዳጅነት አቋም ግን፣ ከዚህም ያለፈ፣ ከዚህም የቀደመ ነው። ገና ሳይመረጡ በፊት የያዙት አቋም ነው።“የአሜሪካ እጅ ረዝሟል፤ ማሳጠር አለብን” ብለው የሚያምኑት ባራክ ኦባማ፤ አሜሪካ በየአገሩ ጣልቃ ገብታ “የግለሰብ መብት አክብሩ፤ የፖለቲካ ምርጫ አካሂዱ፤ የነፃ ገበያ አሰራር አስፋፉ” እያለች ተፅእኖ ማሳረፍ እንደሌለባት ደጋግመው ተናግረዋል። ይሄ፣ ከዋና ዋና የኦባማ መርሆች መካከል አንዱ ነው። ሳይመረጡ በፊትም ሲናገሩት የነበረ፣ ከተመረጡ በኋላም በተግባር የገፉበት የውጭ ግንኙነት መርህ ነው።“ከሁሉም ከሁሉም በፊት፣ የኢኮኖሚ ጉዳይ ይቀድማል” ማለትም የአሜሪካ ድርሻ፣ “የግለሰብ መብት፣ የፖለቲካ ምርጫና ነፃ ገበያ” የሚሉ ቅድመ ሁኔታዎችን ትታ፣ እርዳታ መስጠት ብቻ ይሆናል። ኦባማ ይህንን በተደጋጋሚ ተናግረዋል፤ በተግባርም እየሰሩበት ይሄውና ስድስት አመታት ተቆጥረዋል።ታዲያ፣ ይህንን ሁሉ ሰምተንና አይተን፣ ባራክ ኦባማ በኢትዮጵያ ላይ ምን አይነት አቋም እንደሚከተሉ መገመት ያቅተናል? ቢያንስ ቢያንስ፣ ፖለቲካን እንጀራቸው ወይም ፖለቲካን ሙያቸው ያደረጉ ሰዎች፣ ይህንን መሳት አልነበረባቸውም።ግን ስተውታል፤ በረዥም ርቀት ስተውታል። በቃ፣ የባራክ ኦባማ አቋምና የኢትዮጵያ ጉብኝት፣ ለአገራችን ፖለቲከኞች ግራ የሚያጋባ ድንገተኛ ተዓምር ወይም ዱብዳ ሆኖባቸዋል።በአንድ በኩል፣ ኢህአዴግ፣ በተለመደው የሶሻሊስቶች ፈሊጥ “ኒዮሊበራል” እያለ ከሚያጣጥላት አገር... ካልጠበቀው አቅጣጫ... ከአሜሪካ፣ ለዚያውም ዝነኛው ባራክ ኦባማን የመሰለ አድናቂ ማግኘቱ ያስገርመዋል። 

ያኔ በ2001 ዓ.ም፣ “ባራክ ኦባማ ከተመረጡ፣ በኢህአዴግ ላይ ጫና በማሳረፍ የፖለቲካ ለውጥ እንዲመጣ ይረዱናል” በማለት፣ ኮሚቴ አቋቋመው ቅስቀሳ ሲያካሂዱ የነበሩ የዲያስፖራ ፖለቲከኞችስ? በነሱ ቅስቀሳ ባይሆንም፣ ኦባማ ተመርጠው በፕሬዚዳንትነት ሲሰሩ ስድስት ዓመታት ተቆጥረዋል። ይሄን ሁሉ አመት የኦባማን አስተሳሰብና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ሳይገነዘቡ የቆዩ የአገራችን የዲያስፖራ ፖለቲከኞች፣ በኦባማ አቋም ተበሳጭተው ለተቃውሞ ሰልፍ የወጡት አሁን ነው - የኦባማ ጉብኝት፣ ድንገተኛ ክህደት ሆኖባቸው።
ላለፉት ስድስት አመታት፣ ኢህአዴግና ተቃዋሚዎች፣ የባራክ ኦባማን የውጭ ፖሊሲ ለማወቅ ትንሽ ጥረት ቢያደርጉ ኖሮ፣ ይሄ ሁሉ ግራ መጋባት ባልተፈጠረ ነበር። ለኢህአዴግ፣ ድንገተኛ አድናቆት አይሆንበትም ነበር። ለዳያስፖራ ተቃዋሚዎችም፣ የኦባማ ጉብኝት ድንገተኛ ክህደት ሆኖ ባልታያቸው!

ኢህአዴግና የዲያስፖራ ተቃዋሚዎች ለአመታት ያህል እንዲህ ግራ የተጋቡት ለምንድነው?በእርግጥ፣ ነገሩ ከተፈፀመ በኋላ፤ የጉብኝት ዜናው ከዳርዳር ከተወራ በኋላ… “ነገሩን መሳት አልነበረባችሁም፣ ኦባማ ለኢህአዴግ እንደሚመቹ ማወቅ ነበረባችሁ፤ መገመት ነበረባችሁ” ብሎ መናገር ቀላል ነው። የአገራችን ፓርቲዎችና ፖለቲከኞች ተጨባጭ መረጃን በማገናዘብ፣ ያኔ ድሮ የኦባማ አስተሳሰብንና አዝማሚያን ማወቅ ይችሉ እንደነበር ለማሳየት ነው የፈለግኩት። ለማወቅ ያልቻሉት፣ ነገሩ ከባድ ስለሆነ አይደለም። በጭፍን ስሜት የመነዳት ልማድ ነው እንዲህ ለስህተት የሚዳርጋቸው።

ትኩረት ለሚገባቸው ጉዳዮች ትኩረት እንስጥ::መዘናጋት እና አቅጣጫ መሳት ይቁም::

Minilik Salsawi (ምንሊክ ሳልሳዊ) ለውጥ የሚጠላ ማንኛውም ሰው የለም:; ለውጥ የማይፈልግ ካለ አንድም ከአምባገነን ስርአቶች ይተዳቀለ አሊያም የጥቅሞችን ማግበስበስ የለመደ ስግብግብ የሕዝብ ጠላት ብቻ ነው::በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ያስፈልጋል;ይህ ደግሞ ሳይታለም የተፈታ ነው::በስልጣን ላይ ያለው አመራር አስተዳደሩ ይተበላሸ ስለሆነ ለውጥ ለማምጣት የማይችልበት ደረጃ ላይ ከመድረሱም አልፎ ተኮላሽቷል::ስለዚህ ለውጥ ማምጣት የሚቻለው ይህንን የተኮላሸ አምባገነን ስርአት በማስወገድ አዲስ ስርአት መፍጠር ሲቻል ብቻ ነው::ይህንን የማስወገድ እርምጃ መውሰድ የሚቻለው ደግሞ ትኩረት ለሚሰጣቸው ጉዳዮች ትኩረት ስንሰጥ ብቻ መሆኑን ማወቅ ያስፈልገናል::

እስካሁን ባለው የትግል ሂደት ውስጥ ራሳችን እያገዘፍን ራሳችን እያደባየን ከፍ ስንል እየተንቀባረርን ዝቅ ስንል ደሞ እየተኮማተርን ለአምባገነኡ እድሜ መርዘም ራሳችን አስታውጾ ማድረጋችን መካድ የለብንም::ጥፋቱን ያመነ መፍትሄ ስሌማያጣ ለትግሉ አትኩሮት ሰጥተን ከመታገል ይልቅ እርስ በርስ መጠላለፍ ጆሮ ዳባ ልበስ ማለት ያልበሰሉ ካድሬዎችን ተጠቅመን በስድብ እና በዝርጠጣ ስም በማጥፋት እና በትንኮሳ ላይ መሰማራት የወያኔ አቅጣጫ ማስቀየሻ ስልቶችን ተቀብሎ እንደ ገደል ማሚቶ ማስተጋባት ወያኔን ለመደምሰስ ከተነሱ የለውጥ ሃይሎች ላይ ተቻችሎ አለመቀጠል ወያኔ በሚሰጠ የቤት ስራ ላይ በጋራ ሆነን እየተቀባበልን ማዛጋት እና መዘናጋታችን ትኩርት ለሚገባቸው ጉዳዮች ትኩረት እንዳንሰጥ መንገዱን ቀርቅረን ይዘናል::

ወደ መፍትሄ እና እንደ ሕዝብ የውሳኔ ሰኚነት መስመር ውስጥ ለመግባት አንድነት ሰላም እና ፍቅር መቻቻል መመካከር እና መድማመጥ ይፈለግብናል::በአሁን ወቅት የሚያስፈልገው ምንድነው የሚለውን ማወቅ ያስፈልጋል::ወያኔን ለመደምሰስ ለትግሉ አትኩሮት መስጠት አስፈላጊ ወቅት ላይ ነውን::ለየትኛው ትግል? እያንዳንዳችን ላመንነበት ትግል አስፈላጊዉን ትብብር እና ድጋፍ ማድረግ ከቻልን ከሌሎች ወያኔን ለመደምሰስ ከተሰማሩ ሃይሎች ጋርአብሮ መስራት ባይሆንልን እንኳን በመቻቻል እያለፍን አስፈላጊውን የአቅም መስዋትነታችንን ወደ ተግባር ማሳደግ እችላለን::ሌላው ስድብ ስም ማጥፋተና ዝርጠጣ ሊቆሙ የሚገባቸው የትግል ስልቶች ናቸው::በስድብ ስም በማጥፋት እና በዝርጣጣ ምንም የምናመጣው ለውጥ የለም::ያልበሰሉ ካድሬዎች በባዶ ሜዳ ያወቁ መስሏቸው ሊፈራገጥኡ ይችሉ ይሆናል::እነሱን ተከትለው ደሞ አስመሳዮች ቅጥረኞች አዛኝ ቅቤ አንጓች መስለው ሊዘባርቁ ስለሚችሉ ጥንቃቄ መወሰድ ያለበት ከለውጥ ሃይሎች ጉያ መሆን ይገባዋል::በአሁኑ ወቅት ትኩረት የሚገባቸው ጉዳዮች በለውጥ ሂደቱ ላይ የሚድረጉ ትግሎችን አጠናቅረን በየቦታው የሚደረጉ የትግል ስራዎችን በማቀናጀት ወደፊት ልንገሰግስ ይገባል::ለወያኔ እና ተላላኪዎቹ የቤት ስራ ትኩረት ሳንሰጥ ለለውጥ ትግሉ ስኬት የዜግነት ድርሻችንን ልናበረክት ይገባል::‪#‎ምንሊክሳልሳዊ‬

ለእኛ የሚበጀን በትግላችን ነጻነታችንን ማረጋገጥ እንጂ የኦባማ መግባት እና መውጣት አይደለም::
Minilik Salsawi የባራክ ኦባማ ምስራቅ አፍሪካ ላይ ኬንያን እና ኢትዮጵያን መጎብኘት የሰሞነኛ አዲስ ዜና ሲሆን ባራክ ኦባማ የሃያላኗ አገር መሪ በመሆናቸው የጉዞው ዜና ሰፊ ሽፋን አግኝቶ አለምን እያስተጋባ ይገኛል::ባራክ ኦባማ በርግጥ ከአፍሪካዊ አባት መገኘታቸው እንዲሁም የሃያላኗ አሜሪካ የመጀመሪያው ጥቁር መሪ መሆናቸው ለየት ሊያደርጋቸው የሚችል ቢሆንም የሚከተሉት የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ በተለይ አፍሪካን በተመለከት የሚያራምዱት አቋም አምባገነኖችን ፈልፍሎ ከማበረታታት ውጪ ምንም የፈየደው ነገር የለም::

ኦባማ ወደ ስልጣን ሲመጡ እንደማንኛውም ተወዳዳሪ ለመመረጥ የሚያስችላቸውን ድምጽ ለማግነት አፍሪካን በተመለከተ ቃልኪዳኖችን በማሽጎድጎዳቸው በተለይ ለውጥ ፈላጊ ሃይሎች የሆኑ ኢትዮጵያውያን በአሜሪካ ምድር ለመመረጣቸው ስኬት ጉልህ ሚና ተጫውተዋል::ኦባማ ግን ወደ ስልጣን ወንበሩ ከተዋሃዱ በኋላ የአፍሪካ አምባገነኖችን በነጩ ቤተመንግስታቸው ሰብስበው በከፍተኛ ማበረታታት የአሜሪካንን ጥቅም በልዩ መልኩ በሚጠብቅ ሁኔታ ደም መጣጭ የአፍሪካ አምባገነን መሪዎችን አጓጉል በማሞገስ ለአፍሪካውያን ትልቅ አደጋ የሆኑ ወንጀሎች እንዲሰሩ እና መንግስታዊ ሽብርተኝነት እንዲስፋፋ አድርገዋል::

በርግጥ ምእራባውያን አፍሪካ ውስጥ ለብሄራዊ ጥቅማቸው እንደሚሰሩ የታወቀ ነው:: የሃይል ሚዛንም ባለበት ሆነው ጥቅማቸው እስካልተነካ ድረስ አምባገነኖችን በመደገፍ እንደሚያበረታቱ ሃቅ ነው::ኦባማ የውጪ ፖሊሲያቸው እንደሚያሳየው የአሜሪካን ጥቅሞች እስካልተነኩ ድረስ ማንኛውም አፍሪካዊ መሪ በሃገሩ ውስጥ የሚፈጽመውን የፖለቲካ ግፍ እንደማይመለከታቸው እና ጣልቃ መግባት እንደማይፈልጉ በተለያዩ ጊዜያት አጋጣሚዎችን ተጠቅመው ተናግረዋል::ሕዝቦች በኑሮ ውድነት መግቢያ መውጫ እንዳጡ በርካታ ድሆች ጥቂት በሙስና የከበሩ ቱጃሮች እንዳሉ በገሃድ እየታየ በዋጋ ግሽበት እና በተለያዩ የኢኮኖሚ ውድቀቶች ሃገራት እየሞቱ እያዩ በሃሰት የቁጥር ቁልሎች የኢኮኖሚ እድገት እየታየ እንደሆነ በመጥቀስ ከባልደረቦቻቸው እና ተቋሞቻቸው ጋር እየተቀባበሉ ሲናገሩ ተሰምቷል::ለዚህም በሞት አፋፍ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ አገራችንን ገነት እያደረጉ በመሳል ስህተቶች ሲፈጥሩ ማየት የተለመደ ተግባር ነው::ወታደሮቹን በሽብርተኝነት መዋጋት ሰበብ እየሸተ የሚገነውን ወያኔ መራሹን መንግስት በማቆለጳጰስ መንግስታዊ ሽብርተኝነት ኢትዮጵያን እንዲወር በሩን ከፍተዋል::

ባራክ ኦባማ ለአሜሪካ እና ለአሜሪካውያን ምናልባት ጥሩ መሪ ሊሆኑ ይችሉ ይሆናል::እርሳቸው ወደ ስልጣን ክመጡ በኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት ግድያ እስር እና የሰብአዊ መብት ጥሰት መፈጸሙ እንዲሁም አለምን ያስደመመ እና ያሳዘነ ስደት መከሰቱ እሙን ነው::እርግጥ ነጻነታችንን እና መብታችን የሚያስከብሩልን ኦባማ አይደሉም::እኛ ራሳችን መሆናችንን መዘንጋት የለብንም::የኦባማ የምስራቅ አፍሪካ ጉብኝት ለኛ ምም የሚጠቅመን ነገር የለም::ለሽፋን ጥቂት እስረኞች ቢፈቱ በርካቶች መታሰራቸው እና መገደላቸው ቀጥሏል::ይህንን ልንፈታ የምንችለው በጋራ ቆመን በመታገል በአንድነት ሃይላችንን አጠናክረን የወያኔን ማፊያ መንግስት ስንደመሥ ብቻ እና ብቻ ነው::ምናልባት ኦባማ እንደተለመደው ፍሪደም ኦፍ ምናም የሚል የአንደበት አየር ባየር ንግግሮች ቢናገሩም በዋናነት የሚመለከቱት ግን የሃይል ሚዛኑን እና የሃገራቸውን ጥቅም እንደሆነ ጠንቅቀን ልናውቅ ይገባል::ለኛ የሚበጀን በትግላችን ነጻነታችንን ማረጋገጥ እንጂ የኦባማ መግባት እና መውጣት አይደለም::ድል በሕዝብ ለሕዝብ የሕዝብ ነው::‪#‎ምንሊክሳልሳዊ‬